በአፍሪካ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት የፀረ ሽብር ዘመቻውን ማጠናከር ይገባል – አምባሳደር እስማኤል ሾርጊ  

Source: https://fanabc.com/2019/02/%E1%89%A0%E1%8A%A0%E1%8D%8D%E1%88%AA%E1%8A%AB-%E1%8B%A8%E1%88%9A%E1%88%B5%E1%89%B0%E1%8B%8B%E1%88%89-%E1%8B%A8%E1%8D%80%E1%8C%A5%E1%89%B3-%E1%89%BD%E1%8C%8D%E1%88%AE%E1%89%BD%E1%8A%95-%E1%88%88/

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 4 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን ለዘለቄታው ለመፍታት የፀረ ሽብር ዘመቻውን ማጠናከርና አካታች የልማት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባ የአፍሪካ የሰላምና ፀጥታ ኮሚሽነር አምባሳደር እስማኤል ሾርጊ ተናገሩ።

ኮሚሽነሩ በአህጉሪቱ ሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በአህጉሪቱ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች እየተሻሻሉ መምጣታቸውን ጠቅሰው፥ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ለአብነት አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ማዳጋስካር የተካሄደውን ምርጫና የስልጣን ሽግግርም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የማዕከላዊ አፍሪካ ተፋላሚ ሃይሎች የደረሱትን የሰላም ስምምነትና በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሃይል እያደረገ ባለው ጥረት እየመጣ ያለውን ሰላምና መረጋጋትም አውስተዋል።

በሶማሊያ እየታየ ካለው ለውጥ ባሻገር ግን የአሸባሪው ቡድን አልሸባብ ጉዳይ አሁንም አሳሳቢ መሆኑንም ነው ያነሱት።

ከሊቢያ ጋር በተያያዘም በሃገሪቱ ያለውን ግጭት እልባት ለመስጠት ሁሉንም አሳታፊ የሰላም ድርድር ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው አልሸባብ፣ ቦኮሃራም እና በሳህል ቀጠና አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሃይሎች አሁንም ለአህጉሪቱ የፀጥታ ስጋት መሆናቸውን አስረድተዋል።

ከዚህ አንጻርም በአህጉሪቱ የሚስተዋሉ የፀጥታ ችግሮችን ለዘለቄታው ለመቅረፍ የፀረ ሽብር ዘመቻውን ማጠናከር እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከዚህ ባለፈም ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች አካታች የሆነ የልማት እንቅስቃሴን ማጠናከር ይገባልም ነው ያሉት።

በስደተኞች፣ ከስደት ተመላሾችና የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች ላይ ትኩረቱን ያደረገው 32ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ ማምሻውን የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

 

 

በስላባት ማናዬ

 

 

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.