በኦሮሚያ ለሶስት ቀናት የተጠራው አድማ ተጀመረ

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%89%A0%E1%8A%A6%E1%88%AE%E1%88%9A%E1%8B%AB-%E1%88%88%E1%88%B6%E1%88%B5%E1%89%B5-%E1%89%80%E1%8A%93%E1%89%B5-%E1%8B%A8%E1%89%B0%E1%8C%A0%E1%88%AB%E1%8B%8D-%E1%8A%A0%E1%8B%B5%E1%88%9B-%E1%89%B0/

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 5/2010)

በኦሮሚያ ክልል ለሶስት ቀናት የተጠራው በቤት ውስጥ የመቀመጥና የስራ ማቆም አድማ ዛሬ ተጀመረ።

በአብዛኞቹ የክልሉ ከተሞችና የገጠር አካባቢዎች አድማው በተሳካ ሁኔታ በመካሄድ ላይ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች አድማው ተጠናክሮ ሲካሄድ ከአዲስ አበባ የሚወጡ ሀገር አቋራጭ አውቶብሶች መንቀሳቀስ አልቻሉም።

በአምቦ በሻሸመኔ በጂማ ከአድማው ባሻገር ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፎች መደረጋቸው ታውቋል።

የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ በአስቸኳይ እንዲፈቱና የመከላከያ ሰራዊት ከአካባቢያችን ይውጣ የሚሉት ዋነኞቹ በአድማው የተላለፉ መልዕክቶች ናቸው።

ያልደረሰው አካባቢ የለም። ያልተሳተፈ መንደር፣ ከተማም እንዲሁ።

ለሶስት ቀናት የተጠራውና ዛሬ በመላው የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የተጀመረው የስራ ማቆምና በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ሁለት መልዕክቶችን ለማስተላለፍ የታለመ እንደሆነ አዘጋጆቹ ይገልጻሉ።

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች ተቃውሞው በከፍተኛ ሁኔታ ተጠናክሮ በመቀጠሉ ማንኛውም አይነት የንግድ እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ተቋርጧል።

ስራቸው በአዲስ አበባ ከተማ የሆኑ የመንግስት ሰራተኞች በትራንስፖርት ችግር ምክንያት በስራ ቦታቸው ላይ መገኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።

በካራ ቆሬ አካባቢ ረጲ እና ወመዳ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በአየር ጤና አካባቢ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እና የግል መዋለ ህጻናቶች ተዘግተዋል ውለዋል።

በወለቴ፣ በቡራዩ፣ በኮልፌ ቀራኒዮ አንፎ አካባቢ ተቃውሞ ሲካሄድ ውሏል።

የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ አደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

በወለቴ አንድ የቤት መኪና የአድማ ጥሪውን ባለመቀበል ሲንቀሳቀስ በመገኘቱ እንዲቃጠል ተደርጓል።

ከወለቴ ወደ ሰበታ በሚወስደው መንገድ ላይ የመኪና ጎማዎች ተቃጥለዋል፡፡

ወደ ንግድ ባንክ አካባቢም የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። በሱልልታም እንዲሁ ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ ሲካሄድ ውሏል።

በሻሸመኔ፣ በባሌ፣ ወሊሶ፣ መቱ፣ ቢሾፍቱ፣ ጅማ፣ አለምገና  እንዲሁ  የአድማ ጥሪው ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ከሆነባቸው ከተሞች መካከል ይገኙበታል።

በምስራቅ ሃረርጌ፣ ሃረር ከተማን ጨምሮ በ20 ወረዳዎች እንዲሁም ዋና ዋና በሚባሉት  ከተሞች  አድማው ተግባራዊ እየሆነ ነው።

በኮምቦልቻ ተማሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ የታሰሩ የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ  ጠይቀዋል። የትራንስፖርትም ሆነ የንግድ እንቅስቃሴ ተቋርጧል።

ከአዲስ አበባ ወደ ደቡብ ክልል የሚወስዱት ሁለቱ ዋና ዋና መንገዶች በመዘጋታቸው የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል።

በሻሸመኔ በኩል ወደ አርባምንጭ የሚወስደው መንገድ እንዲሁም በቡታጅራ በኩል ወደ ወላይታ የሚወስደው መንገድ ከጧት ጀምሮ መቋረጡን እና ከአርባምንጭና ወላይታ አካባቢዎች የተነሱ ተሽከርካሪዎች መመለሳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስና ፌደራል ፖሊሶች ወለቴ ድልድይ ላይ ተፋጠው ታይተዋል።

ዘግይቶ በደረሰን ዜናም በደቡብ ክልል በከምባታ ጠምባሮ ዞን በሃዴሮ ዱራሜ ሺንሺቾ አካባቢ ከፍተኛ ተቃውሞ ተጀምሯል።

ህዝቡ ወያኔ ይውደም እያለ መፈክር በማሰማት ላይ ነው።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.