በኦሮሚያ ክልል በኮማንድ ፖስቱ የተያዙ ተጠርጣሪዎች በቂ ምግብና ህክምና እያገኙ አለመሆኑ ታወቀ

Source: http://www.yegnagudday.com/2018/04/16/%E1%89%A0%E1%8A%A6%E1%88%AE%E1%88%9A%E1%8B%AB-%E1%8A%AD%E1%88%8D%E1%88%8D-%E1%89%A0%E1%8A%AE%E1%88%9B%E1%8A%95%E1%8B%B5-%E1%8D%96%E1%88%B5%E1%89%B1-%E1%8B%A8%E1%89%B0%E1%8B%AB%E1%8B%99-%E1%89%B0/

በኦሮሚያ ክልል በኮማንድ ፖስቱ የተያዙ ተጠርጣሪዎች በቂ ምግብና ህክምና እያገኙ አለመሆኑ ታወቀ

በኮማንድ ፖስቱ አማካኝነት በፊቼ፣አምቦ እና ወሊሶ የተያዙ ተጠርጣሪዎች የምግብና ህክምና አገልግሎት በበቂ ሁኔታ እያገኙ አለመሆኑ ተነገረ።

እንደሚታወሰው አዋጁን በበላይነት እንደሚያስፈጽም የተነገረለትን ኮማንድ ፖስት በዋና ጸሐፊነት ይመሩታል የተባሉት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ በተደጋጋሚ መግለጫ በሰጡበት ወቅት የታሰሩ ሰዎችን አያያዝ በይፋ ለመናገር አልደፈሩም፡፡

የመከላከያ ሚኒስትሩ አ/ቶ ሲራጅ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ አባላት ናቸው ከተባሉ ሰዎች ጋር ስለተያዙ ሰዎች አያያዝ ተመካክረዋል ቢባልም፣ በውይይታቸው ወቅት ስለ ታሰሩ ሰዎች ወቅታዊ ሁኔታ በዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

አዋጁ መተግበር ከጀመረ አንስቶ ባሉት ቀናቶች ውስጥ በተለይም ከኦሮሚያ እና ከአማራ ክልሎች በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በአፈሳ መልክ መያዛቸው ሲነገር ቆይቷል፡፡

ዓለም ዓቀፍ የመብት ተሟጋቾች ጭምር ያወገዙትን አዋጅ የሚያስፈጽሙ በተለይ አጋዚ ወታደሮች በርካታ ዜጎችን ሲገድሉ፣ ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን ሰዎችንም ማሰራቸው ይታወቃል፡፡

ሴቶችን መድፈርም የኮማንድ ፖስቱ አንዱ አካል ሆኖ እንደቀጠለ ነው፡፡ ኮማንድ ፖስቱ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ሰዎች፣ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚፈጸሙባቸው የመረጃ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

እንደሚታወቀው በያዝነው ሳምንት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ በሶስት ቡድን ተከፍሎ በኮማንድ ፖስት የተያዙ ተጠርጣሪዎች ያሉበትን ሁኔታ ተዘዋውሮ እየተመለከተ እንደሚገኝ በመንግስት ሚዲያዎች ሲገለፅ ቆይቷል።

የስር ዐቱ ልሳን የሆነው የኢትዮጲያ ዜና አገልግሎት(ኢዜአ) የተገኘበት የመጀመሪያ ቡድን በሰሜን ሸዋ ንዑስ ቀጠና 4፣ በአምቦ ንዑስ ቀጠና 34፣ በወሊሶ ንዑስ ቀጠና 14 ተጠርጣሪዎች በአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስቱ ተይዘው ጉዳያቸው እየታየ ነው።

ተጠርጣሪዎቹ በኮማንድ ፖስቱ ሲያዙ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው አስረድተዋል።

ከዚህ ስቃይ በተጨማሪም ለሰው ልጅ አስፈላጊ ከሚባሉ መሰረታዊ ነገሮች መሀከል በዋነኛነት ምግብና ውሀ ናቸው።

ይሁን እንጂ ከተያዙ ቀን ጀምሮ በሚገባ የምግብና የህክምና አገልግሎት እያገኙ አለመሆኑን በአንደበታቸው ገልፀዋል።

በተለይም በኦሮሚያ ክልል በአምቦና በወሊሶ ንዑስ ቀጠናዎች በኮማንድ ፖስቱ ታፍነው የታሰሩ ወጣቶች ቁጥር ብዙ በመሆኑ የምግብ፣ የማረፊያ ቤትና የህክምና የአገልግሎት ችግር የጎላ መሆኑን ተውቋል።

የዞኖቹ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎች ስለእስረኞች ጉዳይና ስለገጠማቸው ችግሮች ተጠይቀው “ለተጠርጣሪዎቹ የሚሆን የምግብ፣ የማረፊያ ቤትና የህክምና ወጪ በፌዴራል መንግስት የሚሸፈን ቢሆንም በጀቱ አልደረሰንም” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።

በኮማንድ ፖስቱ የታሰሩ ወጣቶች እስከአሁ ጉዳያቸው ወደፍርድ ቤት ተወስዶ ፍትህን እንዳላገኙም ታውቋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ወርዶፋ በተጠርጣሪዎች አያያዝና ምርመራ ወቅት ሰብዓዊነትን የጠበቀ ነው እያሉ በሚዲያዎች ቢያወሩም እውነታው ግን ወጣቶች በስቃይና በእንግልት ላይ እንዳሉ ነው የታወቀው።

The post በኦሮሚያ ክልል በኮማንድ ፖስቱ የተያዙ ተጠርጣሪዎች በቂ ምግብና ህክምና እያገኙ አለመሆኑ ታወቀ appeared first on Yegna Gudday.

Share this post

Post Comment