በወልቃይት ከፍተኛ ወከባና እስር እየተፈጸመ ነው

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%89%A0%E1%8B%88%E1%88%8D%E1%89%83%E1%8B%AD%E1%89%B5-%E1%8A%A8%E1%8D%8D%E1%89%B0%E1%8A%9B-%E1%8B%88%E1%8A%A8%E1%89%A3%E1%8A%93-%E1%8A%A5%E1%88%B5%E1%88%AD-%E1%8A%A5%E1%8B%A8%E1%89%B0%E1%8D%88/

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 22/2011) በወልቃይት ከፍተኛ ወከባና እስር እየተፈጸመ መሆኑ ተገለጸ።

ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ በወልቃይት የአማራ ተወላጆች ላይ የሚያደርሰው ወከባ ድብደባና እስር በመሸሽ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መሰደዳቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ሰሞኑን ከ100 በላይ የአማራ ተወላጆች ከወልቃይ ተፈናቅለው ዳንሻ መግባታቸውም ታውቋል።

ሌሎች ወደ 50 የሚሆኑትም ወደ አብደራፊ መሸሻቸውን ተፈናቅዮቹ ገልጸዋል።

ህወሀት ወልቃይት የትግራይ ነው፣ ወልቃይትን ለማዳን ታጠቁ የሚል ዘመቻ መጀመሩም ተሰምቷል።

በወልቃይት ሰባት የወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፖች በማቋቋም የአማራ ተወላጆችን ጭምር ስልጠና እንዲወስዱ እያስገደደ እንደሆነም ተገልጿል።

ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ህወሀት ወልቃይትን ለማዳን በሚል ውስጥ ለውስጥ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ማድረጉን በተመለከተ መረጃዎች ሲወጡ ቆይተዋል።

ወልቃይት የትግራይ ናት በሚል እንደአዲስ በተጀመረው ዘመቻ በወልቃይት የአማራ ተወላጆች ላይ ከፍተኛ መዋከብ እየተፈጸ መሆኑን ነው ለኢሳት የደረሰው መረጃ የሚያመልክተው።

ኢሳት ያነጋገራቸውና ተፈናቅለው ዳንሻ የሚገኙ የአዲረመጥ ነዋሪ እንደገለጹት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ በአማራ ተወላጆች ላይ የተጠናከረ የማዋከብ ዘመቻ እየተካሄደ ነው።

እናንተ ትግሬ ናችሁ፡ ዘፈናችሁም ቋንቋችሁም ትግርኛ ነው እያሉ ከማስጨነቅ ባለፈ ያስገድዱናል፡ ባህልና ማንነታችንን እንድናጣ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተዋከብን ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ባለፉት ሶስት ወራት ወልቃይትን ለማዳን በሚል የጦርነት የሚመስል ዝግጅት እያደረጉ ነው የሚሉት የአማራ ተወላጆቹ ለዚህም በወልቃይት ሰባት ቦታዎች ማሰልጠኛ ካምፖች ተከፍተው ወጣቱን በግድጅ እያስገቡ ናቸው ተብሏል።

እኛን የአማራ ተወላጆችን ወልቃይትን አድኑ በሚል ወደ ካምፕ ለማስገባት ቤት ለቤት ሲመጡብን ተሰደድን ይላሉ ተፈናቅለው አብደራፊና ዳንሻ የገቡ የአማራ ተወላጆች።

እስከትላንት ድርስ ከ100 በላይ የአማራ ተወላጆች የፈናቅለው ዳሻ የገቡ ሲሆን ከ50 በላይ የሚሆኑት ወደ አብደራፊ ሸሽተዋል።

የህወሀት ታጣቂዎች ውክቢያ ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል የሚሉት ተፈናቃዮች ቤት ንብረታቸው ጥለው ህይወታቸውን ለማትርፍ እንደመጡ ይናገራሉ።

ዋናው የወከባ መንስዔው ታጠቁና ወልቃይትን ከአማራ ወረራ ተከላለከሉ በሚል እንደሆነ የገለጹት ተፈናቃዮቹ የተወሰኑ የአማራ ተወላጆች ተገደው ማሰልጠኛ እንደገቡም ይገልጻሉ።

በሰፈራ ወልቃይት መኖር የጀመሩት የትግራይ ተወላጆች የህወሀት አባላት  ከህወሀት ታጣቂዎች ጋር በመሆን የአማራ ተወላጆች ላይ በሚደረገው ጥቃት መሳተፋቸውንም ተፈናቃዮቹ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት የመስቀል በዓል ሲከበር ምልክት የሌለበትን የኢትዮጵያ ሰንድቅዓላማ ይዛችኋላ ተብለው 15 የአማራ ተወላጆች ላይ ከፍተኛ ድብደባ መፈጸሙንም ተፈናቃዮቹ ይናገራሉ።

የዶክተር አብይ አህመድን ምስል የያዘ ቲሸርት መልበስ ከድብደባ ሌላ ለእስር ይዳርጋልም ብለዋል።

ህወሃቶች ወልቃይት የትግራይ ሆና መቀጠል አለባት የሚለውን አቋም በጉልበት ለመፈጸም እየተዘጋጁ እንደሆነም ተፈናቃዮቹ ገልጸዋል።

በዚህ መሃል የአማራ ተወላጆች ስቃይ ውስጥ ገብተዋል ሲሉ ተናገረዋል።

የሚመለከተው የመንግስት አካል በወልቃይት የአማራ ተወላጆች ላይ የሚፈጸመውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንዲከታተለውም ተፈናቃዮቹ ጠይቀዋል።

 

The post በወልቃይት ከፍተኛ ወከባና እስር እየተፈጸመ ነው appeared first on ESAT Amharic.

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.