በዋነኝነት የኢሮብ ብሄረሰብ አባላት ጥያቄዎች ይዞ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ በትግራይ ስራውን ጀመረ

Source: https://mereja.com/amharic/v2/154664

https://radiodownloaddw-a.akamaihd.net/Events/dwelle/dira/mp3/amh/DA935F84_2_dwdownload.mp3

በትግራይ ክልል ‘ዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ’ (ዓዴፓ) የተባለ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት ተመስርቶ መንቀሳቀስ ጀምሯል። የፖለቲካ ድርጅቱ በዋነኝነት የኢሮብ ብሄረሰብ አባላት በአጠቃላይ የትግራይ ህዝብ ፖለቲካ፣ ማሕበራዊና ኢኮኖምያዊ ጥያቄዎች ይዞ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ መሆኑ ገልፅዋል።


የዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አስተባባሪ አቶ ዶሪ አስገዶም ከዶቼቨለ DW ጋር ባደረጉት ቆይታ ፓርቲያቸው በተለይም በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦች ፍላጎት ለማንፀባረቅ ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡ ከኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት በኋላ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረሰው የአልጀርሱ ስምምነት ፓርቲው በፅኑ እንደሚቃወመው አቶ ዶሪ አስገዶም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ዓሲምባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሶሻል ዴሞክራሲ ርእዮተ ዓለም የሚከተል ሲሆን ፌደራላዊ የመንግስት አወቃቀርም ለኢትዮጵያ ተመራጭ ስርዓት ነው የሚል አቋም እንዳለው አስታውቋል፡፡
ዓሲንባ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከትግራይ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የፕሮግራም ልዩነት እንዳለው የሚገልፅ ሲሆን በተለይም ገዢው ፓርቲ ህወሓት ለዓመታት የህዝቡን የመልካም አስተዳደር፣ ፍትሕና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄ ባለመመለሱ ፓርቲው ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ማድረግ መጀመሩ ይገልፃል፡፡
ይኽ ፓርቲ በቅርቡ በትግራይ ከተመሰረቱ አዳዲስ ፓርቲዎች መካከል ሶስተኛ ነው፡፡ ዓሲምባ ዴሞክራስያዊ ፓርቲ በመጪው ሀገራዊ ምርጫ ለመወዳደር ዝግጅት እያደረገ መሆኑም ገልፀዋል፡፡ ‘ዓሲምባ’ የሚለው ቃል በትግራይ ምስራቃዊ ዞን የኢሮብ ብሄረሰብ አባላት በሚኖሩበት አካባቢ የሚገኝ ተራራ ስያሜ ነው፡፡ ዓሲምባ ተራራ በ1960ዎቹ መጨረሻና 1970ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በወቅቱ የትጥቅ ትግል ያደርጉ የነበሩት ኢህአፓና ህወሓት የጦር ምሽጋቸው አድርገው ይጠቀሙበት ነበር፡፡
Source – DW

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.