በዓለ ጥምቀት በዩኔስኮ በመመዝገቡ: የምስጋና ጉባኤ ነገ በሚሌኒየም አዳራሽ ይካሔዳል፤ ኦርቶዶክሳውያን በጉባኤው ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ተላለፈ

Source: https://haratewahido.wordpress.com/2019/12/21/%E1%89%A0%E1%8B%93%E1%88%88-%E1%8C%A5%E1%88%9D%E1%89%80%E1%89%B5-%E1%89%A0%E1%8B%A9%E1%8A%94%E1%88%B5%E1%8A%AE-%E1%89%A0%E1%88%98%E1%88%98%E1%8B%9D%E1%8C%88%E1%89%A1-%E1%8B%A8%E1%88%9D%E1%88%B5/
https://haratewahido.files.wordpress.com/2019/12/79795023_2456975634412160_1814522862497693696_n.jpg
  • ለመዲናዪቱ 75 የባሕረ ጥምቀት ቦታዎች፣ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እየተሠራ ነው
  • የከተማው አስተዳደር፣ የ38 አብሕርተ ምጥምቃትን ካርታ ዛሬ ለሀ/ስብከቱ ያስረክባል፤
  • የቀሪ ቦታዎችን ካርታ ለማጠናቀቅ የጴጥሮሳውያን ኅብረት ከአስተዳደሩ ጋራ እየሠራ ነው፤
  • የቤተ ክርስቲያን ባለቤትነት መረጋገጡ የሥነ በዓሉን ትክክለኛ ገጽታ ለመጠበቅ ያግዛል፤
  • በአግባቡ እንዲለሙና ከአገልግሎታቸው ውጭ እንዳይባክኑ ሀ/ስብከቱ ሓላፊነት አለበት

***

79795023_2456975634412160_1814522862497693696_n

የጥምቀት በዓል፣ በዩኔስኮ መንፈሳዊ ቅርሶች መመዝገቡን ምክንያት በማድረግ፣ ነገ እሑድ፣ ታኅሣሥ 12 ቀን 2012 ዓ.ም.፣ የምስጋና እና የዕውቅና ጉባኤ በሚሌኒየም አዳራሽ እንደሚካሔድ የተገለጸ ሲኾን፣ አገልጋዮች እና ምእመናን እንዲሳተፉ ቤተ ክርስቲያን ጥሪ አስተላለፈች፡፡

የምስጋና እና የዕውቅና መርሐ ግብሩ፣ በአዲስ ከተማ አስተዳደር አነሣሽነት እንደተዘጋጀ ትላንት ለኢኦተቤ-ቴቪ የተናገሩት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፣ መላው ማኅበረ ካህናትና ሕዝበ ክርስቲያን እንዲገኙ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

 

79963120_2456949397748117_8176233613948354560_n

ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ

ነገ ከቀትር በኋላ ከቀኑ 7፡00 ጀምሮ በሚካሔደው በዚኹ ጉባኤ፣ ሃይማኖታዊ መሠረትና ይዘት እንዲሁም ባህላዊ ገጽታ ያለው የጥምቀት በዓል፣ በዩኔስኮ የመመዝገቡን ፋይዳ በተለያየ መንገድ የሚያስረዱ ልዩ ልዩ ክንውኖች እንደሚቀርቡ ተጠቁሟል፡፡

 

በመርሐ ግብሩ ላይ፥ ቅዱሳን ፓትርያርኮች፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የፌዴራል መንግሥቱ እና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንዲሁም ባለድርሻ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ቀደም ሲል ባወጣው መግለጫ፣ የጥምቀት – ከተራ በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡ፣ የቤተ ክርስቲያናችን፣ የሀገራችንና የሕዝባችን ስም በዓለም ደምቆና ጐልቶ እንዲታወቅ እንደሚያደርግ፤ ሀገራችን በቱሪዝም ክፍለ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንድትኾንም እንደሚያግዝ አስገንዝቧል፤ ጥያቄውን በአዎንታ በመቀበል በኢትዮጵያ ስም በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ እንዲመዘገብ የወሰነውን የዩኔስኮ ጉባኤንም አመስግኗል፡፡

በሌላ በኩል በምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ የሚመራው የከተማው አስተዳደር፣ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ለሚገኙ 75 ያህል የባሕረ ጥምቀት ቦታዎች፣ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እየሠራላቸው መኾኑን፣ ብፁዕ ዋና ጸሐፊ አቡነ ዮሴፍ በመግለጫቸው ጠቁመዋል፡፡

የባሕረ ጥምቀት ቦታዎቹ ካርታ፣ በከተማው አስተዳደር የሃይማኖት ተቋማት የቦታ ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ ቁጥር 2/2004 መሠረት፣ በውበትና መናፈሻ ኤጀንሲ ሥር ኾኖ ቆይቷል፤ ቤተ ክርስቲያንም ለክብረ በዓሉ የመጠቀም መብት ብቻ ነው የነበራት፡፡ ኾኖም፣ በዓለ ጥምቀት በዩኔስኮ መመዝገቡን ተከትሎ፣ አከባበሩንና ዕሴቱን ጠብቆ ለማቆየት፣ የአብሕርተ ምጥማቃቱ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ባለቤትነት በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥር እንዲኾን፣ በከተማው አስተዳደር የልዩ ፕሮሰስ ካውንስል መወሰኑ ታውቋል፡፡

 

images

ምክትል ከንቲባው ኢንጅነር ታከለ ዑማ

ከ75 የሀገረ ስብከቱ ጠቅላላ አብሕርተ ምጥማቃት መካከል፣ የ38ቱ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ሥራ የተጠናቀቀ ሲኾን፣ ዛሬ ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 11 ቀን 2012 ዓ.ም.፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ በሚከናወነው መርሐ ግብር ላይ፣ ምክትል ከንቲባው ኢንጅነር ታከለ ዑማ ተገኝተው፣ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታዎቹን ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ እንደሚያስረክቡ ተገልጿል፡፡

 

ብፀዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የአድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ የሰበካ ጉባኤያት ምክትል ሊቃነ መናብርት፣ ጸሐፊዎች፣ ሊቃውንት፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች በሚሳተፉበት በዚኹ የርክክብ መርሐ ግብር፣ ቤተ ክርስቲያን ለከተማ አስተዳደሩ በተለይም ለምክትል ከንቲባው ኢንጅነር ታከለ ዑማ ምስጋናዋን ታቀርባለች – “የቦታዎቹን ባለቤትነት ለቤተ ክርስቲያን በማረጋገጥ ረገድ ድርሻቸው ትልቅ ነው፤” ብለዋል ሒደቱን በቅርበት የሚከታተሉ አካላት፡፡

ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ ለቤተ ክርስቲያን ክብር እና መብት መጠበቅ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው የሰማዕተ ጽድቅ ቅዱስ ጴጥሮስ ካህናት እና ምእመናን ኅብረት(ጴጥሮሳውያን)፣ ከሰላም ጉዳዮችና ከይዞታ መብቶች ጋራ ለተያያዙ በርካታ ጥያቄዎች ውጤታማ ምላሾችን ያስገኘ ሲኾን፣ የመዲናዪቱን የአብሕርተ ምጥማቃት ባለቤትነት ለማረጋገጥ ለከተማው አስተዳደር ያቀረባቸው ጥያቄዎች፣ በዛሬው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ርክክብ መርሐ ግብር ፍሬው መታየቱ ተመልክቷል፡፡

የጴጥሮሳውያን ኅብረቱ፣ የቀሪዎቹን 37 አብሕርተ ምጥማቃት የባለቤትነት ካርታ ለማስጨርስና ሌሎች የይዞታ ችግሮችን ለመፍታት በምክትል ከንቲባው ከተወከሉ የአስተዳደሩ ሓላፊዎች ጋራ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ በመንገድ ሥራ ምክንያት የተቆረሱና በግለሰብ ይዞታ ውስጥ ያሉ መካናት መኖራቸውን ተጠቁሟል፤ ምትክ ቦታ እንዲሰጥ፣ በካሳ ሥርዐት መሠረትም ተገቢው ካሳ ተከፍሎና የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሠርቶ በቤተ ክርስቲያን ባለቤትነት እንዲያዝ እየሠራ እንደኾነ ተጠቁሟል፡፡

“በዓለ ጥምቀት በብሔራዊ ደረጃ የሚከበርበትን የጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀትን ጨምሮ ውሳኔ ያላገኙ፣ ጥያቄ ያላቸው ያልተፈቱ ብዙ ቦታዎች አሉ፤ ኅብረቱ ከከተማ አስተዳደሩ እና ከሀገረ ስብከቱ ጋራ ተባብሮ በመሥራት እየፈታ ነው፤” ብለዋል የኅብረቱ ምንጮች፡፡

ከባሕረ ጥምቀት ቦታዎች ባሻገር በገዳማት እና አድባራት አጠቃላይ የይዞታ ጉዳዮች፣ የ131 አብያተ ክርስቲያን የይዞታ ማረጋገጫ ጥያቄ ቀደም ሲል ቀርቦ እንደነበር ያወሱት ምንጮቹ፣ የ31ዱ አጥቢያዎች ካርታ ሥራ በከተማው አስተዳደር ተሠርቶ መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡ እኒህ አድባራትና ገዳማት፣ ከመስከረም ወር 1988 እስከ መስከረም 1999 ዓ.ም. ድረስ የታነፁና በመመሪያ ቁጥር 2/2004 መሠረት፣ ይዘውት በቆዩት ቦታ ልክ ካርታው የተሠራላቸው እንደኾኑ አስረድተዋል፡፡

ከመስከረም 1999 ዓ.ም. በኋላ የተሠሩ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን ግን መመሪያው ስለማይሸፍናቸው እስኪሻሻል ድረስ እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡ መመሪያ ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው ከከተማው አስተዳደር ጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ፣ ከቤተ ክርስቲያንም ከሙስሊም ተወካዮችም አስተያየት መውሰዱን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡ በአስተዳደሩ ካቢኔ ሲጸድቅ የቀሩት አብያተ ክርስቲያን ጥያቄ በዚያው ማሕቀፍ ምላሽ እንደሚያገኝ አስታውቀዋል፡፡

Share this post

One thought on “በዓለ ጥምቀት በዩኔስኮ በመመዝገቡ: የምስጋና ጉባኤ ነገ በሚሌኒየም አዳራሽ ይካሔዳል፤ ኦርቶዶክሳውያን በጉባኤው ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ተላለፈ

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.