በዘንድሮው የልደት በዓል በከንሳስ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የቀረበ ዓመታዊ መልዕክት በቀሲስ አስተርዓየ ጽጌ

Source: http://www.mereja.com/amharic/562262

እግዚአብሔር የመፍጠሩን ስራ በሰማይንና በምድር ጀምሮ፤ የቀረውን ፍጥረት በየመልኩና በየዘሩ  ከፈጠረ በኋላ፤ ሰውን የፍጥረቱ መደምደሚያ ቁንጮና ጉልላት አድርጎ  በአርያውና በመልኩ በእለተ  ዓርብ አጠናቆ አረፈ (ዘፍ 2፡2 ) ።  ከዚያ በኋላ ግን ፍጥረታት በየመልካቸውና በየዘራቸው በቅብብሎሽ በውርስ እንዲራቡ አደረጋቸው። ከኦሪቱ ሳይሻገሩ በኦሪቱ ተወስነው የቀሩት ህዝቦች፤ በዚህ  ሀሳብ ላይ ቆመው ቀርተዋል። እኛ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስቲያኖች በሀሳቡ እየተስማማን፤ ግን እንደሌሎቹ በኦሪቱ ሀሳብ ላይ ቆመን ሳንቀር፤ እኛ በስራነው ሳይሆን ክርስቶስ በጸጋው አዳነን ከሚሉት ክርስቲያኖችም ጋራ እንስማማለን። 

በዓለም ላይ ያለው ሰው በክርስቶስ የማዳን ስራ በበርካታ ምክንያቶቹ ተከፋፍሎበታል። ለምሳሌ ከአርዮስ ዘመን በፊት የነበሩ መርቅያን የሚባሉ ቡድኖች ”ክርስቶስ እሩቅ ብእሲ (ፍጡር) ነው። የለበሰውንም ሥጋ ሌላ ፈጣሪ አዘጋጀለት“ ይሉ ስለነበረ፤ በዚያው ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች “እራሱ ክርስቶስ በዕሪና በባህርይ በሥልጣን በመለኮት በፈጣሪነት ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ አንድ ነው ”    (አሐዱ አምላክ)ለማለት “ለሊሁ ሀነጸ  ሥጋሁ ውስተ ክርሰ ድንግል ወኢተሳተፎ መኑሂ  በፈጢረ ሥጋሁ። አላ ለሊሁ ባህቲቶ ፈጠረ”(ሃይ 44; 3)።  አሉ። ይህም ማለት “በድንግል ማህጸን የለበሰውን ሥጋ እሱ ራሱ ሰራው። በክንውኑ ማንም አልተሳተፈበትም። ራሱ ብቻውን ፈጠረው” መርቅያን ከፈጣሪነቱ ባህርይ አውጥተው የለበሰውን ሥጋ ሌላ ፈጣሪ ፈጠረለት እያሉ ያስተጋቡት ባስከተለባቸው ተጽእኖ፤  ክርስቶስን ከፈጣሪነቱ ባህርይ ላለማውጣትና ሌላ ሰው በዚህ መንገድ ወደ ዓለም ተወልዶ  እንዳልመጣ ለማሳየት ሥጋውን ፈጠረው አሉ እንጅ፤ ክርስቶስ ከእመቤታቸው ስለተወለደበት ለመግለጽ ግን የሚስማማ ወረሰው የሚለው ቃል ነው። የለበሰው ሥጋ ፍጡርነት የተፈጸመውማ የአዳም አካል በተፈጠረበት እለት ነው። ስለዚህ የክርስቶስ አካል ከአዳም የተወሰደ ወይም የተወረሰ ነው። ግእዙ ውርስ ለማለት “ነስአ” ይላል ዕብ 2፡16

ወረሰ የምትለው ቃል ምስጢረ ሥጋዌን መሰረተ ሀሳብ የተሸከመች ቁልፍ ቃል ስትሆን፤ ቁርባኑ ተከናውኖ የሚፈጸምባት ወረሰ በምትለው ቃል ነው።

ባጭሩ ለማየት ከተፈለገ፦  

“ በኋለኛው ዘመን ያለ ወንድ ዘር ከቅድስ ድንግል ማርያም ሥጋን ነሳ ወይም ወረሰቅ ገጽ 81 እያለ ይመጣና፤  በመጨረሻ ካህኑ ቁርባኑን ለህዝብ ሲያቀብል፦

“ሥጋሁ ወደሙ ለአማኑኤል አምላክነ ዘነሥአ እምእግዝእትነ ኩልነ” (ቅ ገጽ 110)

“ይህ ከቅድስት ድንግል የወሰደው የወረሰው የአማኑኤል ሥጋውና ደሙ ነው” (ቅ ገጽ 116) እያለ ነው። እንግዲህ ሊቃውንት አበው እንዲህ አጣጥመውና አስማምተው ያስተማሩን በገልጽ ተቀመጦ እያለ፤ ፈጠረ የሚለውን ለመሸሽ ነስአ የሚለውን ከተቱበት” ብሎ መናገር፤ የኦርቶዶክሱን ስርወ ትርጉሙን ማናጋትና ሊቃውንት አበውንም ያላገባብ መንቀፍ የተደራረበ ስህተት ነው።  ይህንን ያናጋ ካህን ቀድሶ ማቁረብ አይችልም። የበለጠ ማብራሪያ ካስፈለገ በሌላ ጊዜ ለማቅረብ ይህን በዚህ አቆይተን፤ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ  ክርስቲያናዊ ግንዛቤያችን ወደምናደንቅበት ወደ ዛሬዋ መልእክታችን እንሻገር። 

ቅዱስ ጎርጎርዮስ “ወተሳተፈነ ዳግመ በሱታፌ ዘይፈደፍድ እምቀዳሚ ቀዳሚሰ  ወሀበነ አርአያሁ ክብርተ። ወዳግመሰ ሥጋነ ህስርተ ወዝንቱስ ግብር ልዑል ወአስተዋህዶተ መለኮቱ ምስለ  ሥጋነ ይትነከር ፈድፋደ እምቀዳሚ ሀበ ዘቦቱ ልብ“         . .ም. 62፡32ብሎ በገለጸው  የኦርቶዶክሱ ክርስቲያናዊ ግንዛቤ ከሁሉም  ጠለቅ ብሎ ይሄዳል። ይህም ማለት፤ ፈጣሪ በጥንተ ተፈጥሮ ሰውን በአርያው በአምሳሉ ከፈጠረበት ጥበቡና ፍቅሩ ይልቅ ያዳነበት ፍቅሩ ይበልጣል። ቀድሞ በአርያውና በአምሳሉ ፈጠረን።  በመበላሸታችን በመርከሳችን በመዋረዳችን ተጸይፎ ሳይተወን የተዋረደውን የተበላሸውን ሰውነታችን     ”ሥጋነ ህስርተ“ ከመለኮቱ ጋራ በማዋሀድ ያዳነበት ፍቅሩ እጅግ ይገርማል!  እያልን በጾም በአንክሮ በመደነቅ እናከብራታለን።

የክርስቶስ ልደት ሁለት ሽህ ዘመን ቆጥሯልና የምንድንቀው አዲስ ክስተት በመሆኑ ብቻ  አይደለም።  ሰው ከሰውነቱ ጀምሮ በወረሰው በባህሉ በቋንቋውና በእምነቱ  ዘመን ሲያቋርጥ ፤ ከልደቱ በዓል ጋራ በሚገጥሙት  አዳዳሲ ክስተቶችም ጭምር  ነው።  ክስተቶቹ የሚገለጹባቸው  ቅኔዎች ባለ ሁለት ክፍሎች አዳዲሶች  ናቸው። የቅኔያችን መጀመሪያ ክፍል፤ ዘመናትንና ትውልድን እየተሻገረ የሚዘልቀውን በዓል የምንገልጽበት ነው። ሁለተኛው ክፍል በየዓመቱ በዓሉ ሲከበር በህዝቡ መካከል የሚከሰቱት ነገሮች ናቸው።

ለምሳሌ፦ የልደት በዓል ዓቢይ ምሥጢር  “መለኮት ከትስብእት ጋራ ተወሀደ” የሚለው ነው። ይህ ክፍል የቅኔው መንደርደሪያው ነው። በመንደርደሪያው ዙሪያ ያሉት ክስተቶች የቅኔው ሁለተኛው ክፍል ነው። አሰረ ንጉሥ ይባላል። በዚህ ክፍል የሚንጸባረቁት፤  የምንባቡን ሰፊ ሽፋን የያዙት በልደቱ ዙሪያ የተከሰቱት ናቸው። እነዚህም ክስተቶች በአሰረ ንጉሥ ስር ከዚህ በታች የተደረደሩት ናቸው ሉቃስ 2 ፡ 8᎗29 ይመልከቱ

አሰረ ንጉሥ (መናብርት) ወይም ህዝባውያን ክስተቶች  የሚነጸባርቁባቸው

1ኛ፦ክርስቶስ በቤተ ልሄም ተወልዶ  በጨርቅ ተጠቅሎ በግርም ተኝቷል።

2ኛ፦እረኞች ክርስቶስ ከተወለደበት ቦታ ራቅ ብለው በመንጋቸው መካከል ነበሩ።

3ኛ፦መላኩ በመንጋቸው መካከል ለነበሩት እረኞች ድንገተ ተከሰተ።

4ኛ፦በእረኞች መካከል የእግዚአብሔር ክብር በራ

5ኛ፦የሰማይ ሠራዊትም ድንገት ተከሰቱ

6ኛ፦“በምድር እግዚአብሄር ለሚወዳቸው በምድር ላሉ ሰዎች   ሰላም” ብለው አወጁ።

7ኛ፦እረኞችም ከመላኩ የሰሙትን በዓይናቸው አይተው ለህዝብ መሰከሩ።

በልደቱ ዙሪያ የተከናወኑትን ከዚህ በላይ  የተዘረዘሩትን ክስተቶች እንደሚዛን በመጨበጥ  መሪዎቻችን እንመዝንባቸዋለን፤ እንታዘብባቸዋለን ” በማለት በከንሳስ መድኃኔ ዓለም ዓውደ  ምህረት ላይ የቀረበውን ኦርቶዶክሳዊ መልእክት ሁሉም ቢሰማው ይጠቅማል ብለን ስለገመትን ከዚህ በታች አቀረብንላችሁ።

Share this post

Post Comment