በዚምባቡዌ በድርቅ ሳቢያ 55 ዝሆኖች ሞተዋል  

Source: https://fanabc.com/2019/10/%E1%89%A0%E1%8B%9A%E1%88%9D%E1%89%A3%E1%89%A1%E1%8B%8C-%E1%89%A0%E1%8B%B5%E1%88%AD%E1%89%85-%E1%88%B3%E1%89%A2%E1%8B%AB-55-%E1%8B%9D%E1%88%86%E1%8A%96%E1%89%BD-%E1%88%9E%E1%89%B0%E1%8B%8B%E1%88%8D/

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 11 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በዚምባቡዌ በድርቅ ሳቢያ በጥቂቱ 55 ዝሆኖች መሞታቸው ተነገረ።

በህዋንጌ ብሄራዊ ፓርክ የሚገኙ ዝሆኖች በድርቅ ሳቢያ በተከሰተው ርሃብ ለሞት መዳረጋቸውን የሃገሪቱ ብሄራዊ ፓርኮች እና የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ቃል አቀባይ ቲናሼ ፋራዎ ተናግረዋል።

በአካባቢው ያለው ሁኔታ አስቸጋሪ መሆኑን ያነሱት ቃል አቀባዩ በርሃብ ሳቢያ ዝሆኖቹ እየሞቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥም 55 ዝሆኖች ሲሞቱ አሁን ያለው ሁኔታም የከፋ ነው ብለዋል ቃል አቀባዩ።

ከድርቁ ባለፈ ግን ፓርኩ ከሚያስተናግደው የዝሆኖች ቁጥር በላይ መያዙ የግጦሽ እና ውሃ እጥረት እንዲከሰት አድርጓልም ነው የሚሉት።

ፓርኩ 15 ሺህ ዝሆኖችን ብቻ መያዝ ቢገባውም አሁን ላይ ከ50 ሺህ በላይ ዝሆኖች እንደሚገኙበት ይነገራል።

ዝሆኖቹ በፓርኩ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ በአቅራቢያ ወደሚገኙ መንደሮች በማቅናት በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ከፍ ያለ ጉዳት እያደረሱ መሆኑንም ገልጸዋል።

ምግብና ውሃ ለማግኘት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሳቢያም በዚህ አመት ብቻ 22 ሰዎችን ገድለዋልም ነው ያሉት።

አሁን ላይ በሃገሪቱ የተከሰተው ድርቅ በሰብል ምርት ላይ ከፍተኛ እጥረት እንዲከሰት ማድረጉ ይነገራል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም 1/3 የሚሆኑት የሃገሬው ዜጎች የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሏል።

ከዚህ ውስጥም 2 ሚሊየን ያክል ሰዎች ለርሃብ አደጋ መጋለጣቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ባለፈው ነሃሴ ወር ላይ ያወጣው ሪፖርት ያመላክታል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

 

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.