በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በጥበቃ ሰራተኛ በተተኮሰ ጥይት የአንድ ተማሪ ህይዎት አለፈ፡፡

Source: https://mereja.com/amharic/v2/77832

እንደ ፖሊስ መረጃ ትናንት ምሽት 2፡40 ላይ የዩኒቨርሲቲው ጥበቃ ሰራተኛ ከግቢው ውስጥ ወደ ተሰባሰቡ ተማሪዎች ጥይት ተኩሷል፡፡ ይህን ያደረገውም ተማሪዎች ከግቢው ሊወጡ ነው በሚል ለመበተን አስቦ እንደነበር ነው ፖሊስ አገኘሁት ያለውን መረጃ ጠቅሶ የገለጸው፡፡የደቡብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ብርሃን ገላው እንደተናገሩት በዚህም የአንድ ተማሪ ህይዎት ወዲያውኑ አልፏል፤ አንድ ተማሪ ደግሞ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ በደብረታቦር ሆስፒታል የህክምና እገዛ ከተደረገለት በኋላም ለተጨማሪ ህክምና ወደ ፈለገ ህይዎት ሪፈራል ሆስፒታል ተልኳል ነው ያሉት ኮማንደር ብርሃን፡፡
እንደ ኮማንደሩ መረጃ የሟች ተማሪ አስከሬንም ወደ ቤተሰቦቹ መኖሪያ ደቡብ ጎንደር ዞን ደራ ሀሙሲት ተልኳል፡፡ ድርጊቱን የፈጸመው የጥበቃ ሰራተኛ ለጊዜው ከአካባቢው ተሰውሯል፤ ተጠርጣሪውን ለህግ ለማቅረብም እየተሰራ መሆኑን ነው ኃላፊው የተናገሩት፡፡የድርጊቱ ምክንያትም እየተጣራ ነው ብሏል ፖሊስ፡፡
የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ መሆኑንና ተማሪዎች ከስጋት ነጻ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑንም ኮማንደሩ ነግረውናል፡፡የዩኒቨርሲቲው የውጪና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌትነት መለሰ ዛሬ ረፋድ እና ቀን ላይ ተማሪዎች ድርጊቱን አውግዘው ሰልፍ ማካሄዳቸውን ለአብመድ ተናግረዋል፡፡

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.