በግድቡና ለድርድር በማይቀርቡ ጉዳዮች ዙሪያ የሚሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ

Source: https://fanabc.com/2019/11/%E1%89%A0%E1%8C%8D%E1%8B%B5%E1%89%A1%E1%8A%93-%E1%88%88%E1%8B%B5%E1%88%AD%E1%8B%B5%E1%88%AD-%E1%89%A0%E1%88%9B%E1%8B%AD%E1%89%80%E1%88%AD%E1%89%A1-%E1%8C%89%E1%8B%B3%E1%8B%AE%E1%89%BD-%E1%8B%99/

አዲስ አበባ፣ ህዳር 15፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ህብረተሰቡ በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ ያለውን ተፈጥሯዊ የመጠቀም መብቱንና ለድርድር የማይቀርቡ የመንግስት አቋሞችን በግልፅ እንዲያውቅ የሚሰራው ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የ2012 ዕቅድና የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ገምግሟል።

ኮሚቴው ግብፅ በህዝቧ ዘንድም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረኮች ጫና ለማሳደር የምትሰራውን ጠንካራ ስራ በማስታወስ ኮሚቴው ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን የሚገዙ ዓለም አቀፍ ህጎች ላይ ዕውቅና ያላቸውን ሰዎች ማሳተፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል።

የግብጹ ፕሬዚዳንትና አፈ ጉባኤው በአባይ ተፋሰስ እየዞሩ አዳዲስ አስተሳሰቦችን እያስያዙ ነው ያለው ኮሚቴው፥ ይህን እየተከታተለ መለወጥ የሚያስችል ዝግጅት እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል።

ከዚህ ባለፈም በሃገር ውስጥ አስቀድሞ የመከላከል ስራ እንደሚያስፈልግም ኮሚቴው አሳስቧል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በግድቡ ዙሪያ የተቋረጠው ድርድር እንደገና መቀጠሉን ገልጸዋል።

በዚህም ግብፅ ለአሜሪካ ያስጨበጠችውን የተሳሳተ ግንዛቤ ማስለወጥ መቻሉን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን በመጠቀም መብቷ ዙሪያ ያላት አቋም ግንዛቤ እንዲያገኝ ተደርጓልም ነው ያሉት።

ውይይቱ የተጀመረውን ድርድር የማገዝና ለድርድር ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ያለፈ ሃገሪቱ ላይ የሚመጣ ተጨማሪ ጫና እንደሌለም ተገልጿል።

በግብፅ በኩል የተጋነነ ችግር በማቅረብ ህዝባቸውን ለማሳሳትና ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን ለማደናገር የሚደረጉ ሙከራዎች ትክክል እንዳልሆነ ጠቅሰው፥ ግንባታው እንደማይደናቀፍና ሊቆምም እንደማይችል አረጋግጠዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኤርትራ ጋር ስለተደረሰው ስምምነት በሰጡት ማብራሪያም፥ ስምምነቱ ስጋትን አስወግዶ ከሰላም አንፃር ጥሩ ሁኔታ መፍጠሩን በመጠቆም የሰላም ስምምነቱን ወደ መሬት አውርዶ ለመተግበር በሙሉ መተማመን ላይ ተመስርቶ የሚሰራና ጊዜ የሚጠይቅ ዝግጅት መኖሩን አንስተዋል።

ከኤርትራና ከሱዳን ጋር የሚደረጉ ድንበር የማካለል ስራዎችም የቅደም ተከተል ጉዳይ እንጂ የተተወ አይደለም ማለታቸውን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.