በጥቅም የተያዙ የፌደራል መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ለአብዲ ኢሌ ሽፋን እየሰጡ ነው ተባለ

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%89%A0%E1%8C%A5%E1%89%85%E1%88%9D-%E1%8B%A8%E1%89%B0%E1%8B%AB%E1%8B%99-%E1%8B%A8%E1%8D%8C%E1%8B%B0%E1%88%AB%E1%88%8D-%E1%88%98%E1%8A%95%E1%8C%8D%E1%88%B5%E1%89%B5-%E1%8A%A8%E1%8D%8D%E1%89%B0/

በጥቅም የተያዙ የፌደራል መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ለአብዲ ኢሌ ሽፋን እየሰጡ ነው ተባለ
(ኢሳት ዜና ግንቦት 09 ቀን 2010 ዓ/ም) የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ኢሌ በክልሉ ውስጥ የሚፈጽመው የሰብአዊ መብት ጥሰት በወንጀል የሚያስጠይቀው ቢሆንም፣ በገንዘብ ጥቅም የተያዙት በርካታ የፌደራል መንግስት ባለስልጣናትና የመከላከያ አዛዦች ከለላ እየሰጡት መሆኑን ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ የክልሉ ተወላጆች ይናገራሉ።
ከጅግጅጋና የተለያዩ ቦታዎች የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችን ጉዳይ እንዲያጣሩ የተላኩ በመንግስት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በመጀመሪያ ያቀረቡትን የምርምራ ሪፖርት፣ የኮሚሽኑ ሊ/መንበር ዶ/ር አዲሱ ገብረእግዚአብሄር በመቀየር አብዲ ኢሌን ከተጠያቂነት ለማዳን ያደረጉትን ሙከራ በአብነት የሚጠቅሱት ተወላጆቹ፣ የአቶ አዲሱን ሪፖርት እንዲቀበበሉ ተጠይቀው እምቢ ያሉት የክልሉ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አቶ ጀማል መሃመድ በአብዲ አሌ ወኪሎች ድብደባና ስቃይ እንደተፈጸመባቸው ገልጸዋል።
ትናንት ዶ/ር አዲሱ ገብረእግዚአብሄር ቢሮ የተገኙት የሶማሊ ክልል የአገር ሽማገሌዎች ፣አቶ አዲሱ ከአብዲ ኢሌ ገንዘብ በመቀበል ርዕሰ መስተዳድሩ ያደረሱባቸውን ስቃይ እየሸፋፈኑላቸው መሆኑን ፊት ለፊት ነግረዋቸዋል። ዶ/ር አዲሱ የምርምራ ሪፖርቱን ለፓርላማው ተወካዮች ያቀረቡ ቢሆንም፣ ተወካዮቹ እስካሁን ለፓርላማው አባላት ሊያቀርቡት አልቻሉም። ዶ/ር አዲሱ ከአቶ አብዲ ኢሌ ከፍተኛ ገንዘብ ከሚሰጣቸው ሰዎች መካከል አንደኛው መሆናቸውን ተወላጆቹ ይገልጻሉ።
ሌላው ለአቶ አብዲ ኢሌ ድጋፍ የሚሰጡት የቀድሞው ፌዴራል ጉዳዮችና የአርብቶ አደሮች አካባቢ ልማት ሚኒስትርና አሁን በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አቶ ካሳ ተክለብርሃን ናቸው። አቶ ካሳ ተክለብርሃን- ከአብዲ አሌ የግል ካዝና በአዲስ አበባ በተለያዩ የክልሉ ከተሞች መኖሪያ ቤቶችን ስርተው እንደሚያከራዩ እነዚህ ምንጮች ገልጸዋል። አቶ ካሳ ተክለብርሃንና አቶ አዲሱ ገብረ እግዚአብሄር ከመከላከያ አመራሮች ጋር ሆነው ለአቶ አብዲ ኢሌ ሽፋን እየሰጡ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።
የአገር ሽማግሌዎቹ ለፌደራል መንግስቱ ደብዳቤ ሲልኩ፣ የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት ድብዳቤዎችን መልሰው ለአብዲ አሌ ስለሚልኩ ፣ አብዲ አሌ በሽማግሌዎቹ ላይ የበቀል እርምጃ ሲወሰድ መቆየቱንና በዚህም ሳቢያ ሽማግሌዎቹ የፌደራል ባለስልጣናትን ለማመን መቸገራቸውን ተናግረዋል።
አብዲ አሌን ይቃወማሉ የተባሉ በርካታ በክልሉ የሚገኙ ምሁራን በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ በአብዲ ኢሌ ላይ የሚታየው ተቃውሞ እየተባባሰ በመሄድ ላይ ነው።

The post በጥቅም የተያዙ የፌደራል መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ለአብዲ ኢሌ ሽፋን እየሰጡ ነው ተባለ appeared first on ESAT Amharic.

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.