ቢዘገይም አዴፓ ዐማራ ሆኖ ወጥቱዋል !

Source: http://moreshinfo.com/archives/3827

የአዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሕወሓትን በተመለከተ ያወጣው መግለጫ  የድርጅቱን ምንነትና ተልዕኮ ምን እንደሆነ በዘገየ መልኩም ቢሆን ባግባቡ የተገነዘበው እንደሆነ ያሳያል:: አገራችን ለገባችበት ሁለንተናዊ ችግር ፈጣሪውና ተጠያቂው ሕወሓት መሆኑን አጋልጡዋል:: 

ሕወሓት የዐማራ ሕዝብ ጠላት መሆኑን የ1968 ዓም ፕሮግራማቸውን ዋቢ አድርጎ ለአባላቱና ለደጋፊዎቹ ብሎም ለዐማራው ሕዝብ ይፋ አድርጉዋል:: በአሁኑ ሰዓት በአገራችን ላለው የሰላም እጦት ዋናው ተጠያቂ ወያኔ መሆኑን ይፋ አድርጉዋል:: በዚህም አዴፓ እንደ ብአዴን የወያኔ/ሕወሓት ጉዳይ አስፈጻሚ ሳይሆን የዐማራው ኅልውና  ሰላም  አንድነት  እድገትና ብልጽግና ዋስ ጠበቃ መሆኑን አጽንዖት ሰጥቱዋል:: ይህም ብቻ አይደለም :: ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ከቆሙ ኃይሎች ጎን በመቆም ዐማራው በአገሪቱ ኢኮኖሚ  ፖለቲካና ማኅበራዊ ሕይዎት ተገቢ ድርሻውን እንዲያገኝ ያላሳለሰ ትግል የሚያደርግ መሆኑን ለወዳጅም ለጠላትም ግልጽ አድርጉዋል:: ይበል የሚባል ነው::

የዐማራውን የመደራጀትና በአገሩቱ ሁለንተናዊ ሀብት ባለድርሻ የመሆን ጥያቄ እያሸተ መምጣቱ ይስተዋላል:: ለዚህም አዴፓ የበኩሉን የመታገያ ሜዳ የማስፋት እና መሰል የአይዞአችሁ ድጋፍ እየዳበረ መምጣት ለዐማራው መሰባሰብ የራሱ የሆነ በጎ ተጽዕኖ ማሳደሩ እውነት ነው::  የዐማራው ፖለቲካዊ ኃይሎች ወደታላቁ ግባቸው ለመድረስ ተናቦ ለመሥራት  ዝንባሌ እያሳዩ መመጣት ዐማራው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሕይዎት ውስጥ አይበገሬ ኃይል ሆኖ ሊወጣ እንደሚችል ፍንጭ አመላካች ሆነ::  ይህም የዐማራውን አንድነትና ኅልውና አስጠብቆ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያረጋግጥ እንደሆነ ሥጋት ያሳደረባቸው ወገኖች “ይቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም” በሚል ስሌት በጊዜው ለዐማራ ኅልውና ጠንካራ መሠረት ነው ብለው ባመኑት አዴፓን  የማዳከምና ድርጅቱን መሪ የማሳጣት ደበባ ሸረቡ::

በደባውም ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓም በአዴፓ አመራር ላይ የግድያ ተግባር እንዲፈጸም አስደረጉ:: አዴፓ ባጣቸውና በግፍ በተገደሉበት አመራሮቹ ሐዘን  ቁጭት  እና ንዴት ሳያገግምና አመራሩን በቅጡ ሳይሰይም  የዐማራው ሕዝብ መሠረታዊ ጠላት የሆነው ወያኔ/ሕወሓት ዐማራውን እና ለኅልውናው የቆሙ ልጆቹን ለዳግም ብቀላ የትግራይን ሕዝብ ጃዝ ያሉበትን መግለጫ ባወጡ ባንድ ቀን ልዩነት ውስጥ  አዴፓ ቆራጥና የማያወላውል የዐማራ ልጅነቱን የሚገልጽ መግለጫ በማውጣቱ  የዐማራ ኅልውና ለኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት የናንተ ሀሳብ የእኛም ነው  ለማለት እንወዳለን::

ይህ ወቅት የዐማራው የፖለቲካ የሲቪክ የሙያና መሰል ድርጅቶችና ግለሰቦች ተናበውና ተደጋግፈው የሚንቀሳቀሱበት እንጂ  አንዱ በሌላው ላይ ጣት የሚቀሳሰሩበት አይደለም:: በመሆኑም ሁሉም ለዐማራ ኅልውና ቁመናል የሚሉ ኃይሎች አዴፓ ያወጣውን አቁዋም በመደገፍ ላቀረበው የእንተባበር ጥሪ አዎንታዊ መልስ ልንሰጥ ይገባል:: የዐማራው ጠላቶች ብዙ ናቸው:: ጠላቶቹ ታሪካዊ  ጊዜአዊ  የሩቅና የቅርብ ናቸው:: እነዚህ ደግሞ ተናበውና ተደጋግፈው ሳይሰላቹና እንቅልፍ ሳይተኙ ሌት ተቀን የሚሠሩ ናቸው:: እነዚህን ጠላቶች መመከት የምንችለው ተናበንና ተደማምጠን እንጂ ፍጭው ፈንግጭው ብለን አይደለም::

ስለሆነም ወቅታዊውንም ሆነ ዘለቄታውን የዐማራ ሕዝብ ጥያቄ ሁነኛ መልስ ለማስገኘት የዐማራው ልጆች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በግድ የለሽነትም ሆነ በማሰብ የዐማራውን ጠላቶች የልብ ልብ ከሚሰጡ  ድርጊቶች ከመቆጠብ ባሻገር  ለአዴፓ መግለጫና ጥሪ አዎንታዊ መልስ በመስጠት ጠላቶቻችን ቅስም ለመስበር ዝግጁ እንድንሆን ዐኅኢአድ ጥሪውን ያቀርባል::

የዐማራው የኅልውና ትግል በልጆቹ ተጋድሎ ዕውን ይሆናል!

July 12th 2019

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.