ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በአዲስ አበባ በራስገዝነት ጥያቄ ዙሪያ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር አደረገ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ መስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም…

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በአዲስ አበባ በራስገዝነት ጥያቄ ዙሪያ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር አደረገ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ መስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ መስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ በራስገዝነት ጥያቄ ዙሪያ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር ማድረጉ ተገልጧል። የአማራ ሚዲያ ማዕከል ከባልደራስ ጋዜጠኛ ወግደረስ ጤናው ጋር ያደረገው ቆይታ እንዳመለከተው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ፣አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት /አብሮነት፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ/ኢዜማ፣አረና እና ተራማጅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከባልደራስ ጋር ውይይት አድርገዋል። ጋዜጠኛ ወግደረስ እንደገለፀው በመድረኩ የተሳተፉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ባልደራስ ያቀረበውን የአዲስ አበባን የራስ ገዝነት ጥያቄ እንደሚደግፋትና አብረው እንደሚሰሩም ይሁንታቸውን አሳይተዋል። ፓርቲዎቹ ባልደራስ በዋና ፅ/ቤት ያካሄደውን ምክክርን ጨምሮ ሌሎች ፓርቲው ፊት ለፊት እየታገለባቸው ያሉ ጉዳዮችን በአድናቆት እንደሚመለከቱም ተገልጧል። በጋራ ምክክሩ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የአዲስ አበባ የራስገዝነት ጥያቄን በተመለከተ የየራሳቸውን ገንቢ ሀሳብ መስጠታቸውም ታውቋል። ፓርቲዎች የአዲስ አበባ ጉዳይ እንደሚያሳስባቸውና ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተገኝተው ቢመክሩበት መልካም ነው ስለማለታቸው ጋዜጠኛ ወግደረስ አስታውቋል። ባልደራስ ከሳምንት በፊት ብልፅግናን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአዲስ አበባ የክልልነት/አድያምነት/የራስ ገዝነት ጉዳይ ዙሪያ እንመካከር በሚል ባደረገው ጥሪ መሰረት ነው በተገኙት ፓርቲዎች ውይይቱ የተካሄደው። ባልደራስ ታሪካዊ ዳራዎችንና የነዋሪዎችን ብዛት በማንሳት የአዲስ አበባ ህዝብ በምጣኔ ሀብት፣በፖለቲካም ሆነ በማህበራዊ ዘርፍ ማግኘት የነበረበትን እድገት አላገኘም በተለይም አዲስ አበባ በሞግዚት አስተዳደር እየተመራች ነው፤ ይህና የልዩ ጥቅም ፖለቲካ መቅረት አለበት በሚል በዋና አጀንዳነት ይዞ እየታገለበት መሆኑ ተጠቅሷል። አፈፃፀሙ ምን ይመሰል?፣የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ምን መሆን አለበት?ሌሎች ያልተገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ተገኝተው ሀሳብ ይስጡበት በሚል ከሶስት ሳምንታት በኋላ በድጋሜ ተገናኝተው ለመምከር መስማማታቸው ተሰምቷል። ከጋዜጠኛ ወግደረስ ጤናው ጋር የተደረገውን ውይይት በአማራ ሚዲያ ማዕከል/AMC የዩቱብ አድራሻ የምናቀርብ ይሆናል።

Source: Link to the Post

Leave a Reply