ቤተ ክርስቲያንን ከጥቃት ለመታደግ: ቅዱስ ሲኖዶስ የእረኝነት፣ መንግሥት የሕግ አስጠባቂነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ደቀ መዛሙርቱ ጠየቁ፤ “ለዝምታም ኾነ ትዕግሥት መጠንና ልክ አለው!”

Source: https://haratewahido.wordpress.com/2019/04/12/%E1%89%A4%E1%89%B0-%E1%8A%AD%E1%88%AD%E1%88%B5%E1%89%B2%E1%8B%AB%E1%8A%95%E1%8A%95-%E1%8A%A8%E1%8C%A5%E1%89%83%E1%89%B5-%E1%88%88%E1%88%98%E1%89%B3%E1%8B%B0%E1%8C%8D-%E1%89%85%E1%8B%B1%E1%88%B5/
https://haratewahido.files.wordpress.com/2019/04/theo-college4.jpg

theo college7 - Copy

  • ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለቤተ ክርስቲያን ሉዓላዊነት መከበር ድምፁን አላሰማም፤ አላወገዘም፤
  • መንግሥት፣ አገር የተባለች ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናኗን ከጥቃት አልጠበቀም፤
  • የቅዱስ ሲኖዶሱ ዝምታ ይሰበር፤ ለመንጋው አለመጨነቅ ሊያበቃ ይገባል
  • መንግሥት፣ ከቃላት ባለፈ ችግሮች እንዳይደገሙ ግዴታውን ይወጣ!
  • ቋሚ ሲኖዶሱ፣ ፓትርያርኩንና ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁን በመሸምገል ላይ ነበር፤
  • ደቀ መዛሙርቱን ያነጋገረ ሓላፊም ኾነ አባት የለም
***

theo college4

በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች፣ በቤተ ክርስቲያን፣ በካህናትና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለውን አስከፊ ጥቃት፣ ግፍ፣ ሥቃይ፣ መከራና ስደት ለመከላከል፣ ቅዱስ ሲኖዶስ የእረኝነት ተግባሩን፣ መንግሥትም ሕግንና ሥርዓትን የማስጠበቅ ሓላፊነቱን እንዲወጣ፣ የኹለቱ መንፈሳውያን ኮሌጆች ደቀ መዛሙርት ጠየቁ፡፡

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ እና የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት፣ ዛሬ ዓርብ፣ ሚያዝያ 4 ቀን ረፋድ፣ ወደ መንበረ ፓትርያርኩ በመሰለፍ በልዩ ልዩ ኀይለ ቃላት ባሰሙት ድምፅ፣ አስከፊ ጥቃቶች በቤተ ክርስቲያን ላይ ሊፈጸሙ የቻሉት፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ እና በተዋረድ ያሉ የመንጋው ጠባቂዎች፣ የእረኝነት ተግባራቸውን ከመወጣት ይልቅ ለራሳቸው ክብርና ጥቅም ቅድሚያ በመስጠታቸው መኾኑን ገልጸዋል፡፡

መንግሥትም፣ አገር የተባለችውንና ባለውለታ የኾነችውን ቤተ ክርስቲያን፣ አገልጋዮችና ምእመናን ከመጠበቅ አንጻር ሓላፊነቱን በአግባቡ ሲወጣ አለመስተዋሉንና በዚህም ሳቢያ፣ በሕግ የተፈቀደ እስኪመስል ድረስ፣ ከፍተኛ የማሳደድ፣ የመግደልና የማቃጠል ግፍና በደል እየደረሰባት እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

theo college

በጅግጅጋ ከተቃጠሉት በርካታ አብያተ ክርስቲያን ጀምሮ በሰላሌ እና በአጣዬ አካባቢ እንደ ችቦ የነደዱትን አብያተ ክርስቲያን በቅርብ ምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ በዚያው ልክ፣ አገልጋዮች ካህናትና ምእመናን፣ እንደ በራክዩ ልጅ እንደ ዘካርያስ ደማቸው በመሠዊያው ፊት ፈሷል፤ ክቡር የኾነው አካለ ሥጋቸው እንኳ ሳይቀር በእሳት እንዲቃጠል ተደርጓል፤ ብለዋል፡፡

አያይዘውም፣ ነባር የቤተ ክርስቲያን ይዞታዎችን የመንጠቅ እንቅስቃሴዎች የታዩና እየታዩ መኾናቸውን፣ በአንዳንድ ዘመናዊ ት/ቤቶችም፣ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች የአንገት ማዕተባቸውን ከነመስቀሉ እንዲበጥሱ የተገደዱበት ኹኔታ ማጋጠሙን ተናግረዋል፡፡ በኦርቶዶክሳዊነታቸው ብቻ የተለያዩ ጫናዎች የሚደርሱባቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት ሠራተኞች መኖራቸውን፣ የማምለኪያ ስፍራም እንዳይኖራቸው መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

መፍትሔው በዋናነት ያለው፣ በቅዱስ ሲኖዶስ እና በአባቶች እጅ መኾኑን ነው ደቀ መዛሙርቱ የገለጹት፡፡ በቤተ ክርስቲያን፣ በአገልጋዮቿና በምእመናኗ ላይ፣ እስከ አሁን ከተፈጸመባት መከራና ስደት በላይ ስለማይደርስባት፣ ዝምታቸውና ትዕግሥታቸው መጠንና ልክ ሊኖረው ይገባል፡፡

20190412_092812

ዓላማቸውን በመሳት በባለሥልጣናቱ ፊት እውነተኛውን የእግዚአብሔርን ቃል ለመናገር መፍራታቸውን አቁመውና ዝምታቸውን ሰብረው፣ የመንጋ ጥበቃ(እረኝነት) እንዲሁም የቤተ ክርስቲያንን ሉዓላዊነት የማስከበር አባታዊ ሓላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፤ ከራሳቸው በላይ ለህልውናዋና ለክብሯ አጥብቀው ሊያስቡና ሊጨነቁ ያስፈልጋል፡፡


ከመንግሥትም፣ ከቃላት ባለፈ፣ ዜጎችን ከሞትና ከስደት የመከላከል ዝግጁነትና ርምጃ እንደሚጠበቅ ጠቅሰው፣ ችግሮቹ ዳግም እንዳይከሠቱ አስቀድሞ የማክሸፍ፣ ሕግንና ሥርዓትን የማስጠበቅ ግዴታውን በአግባቡ እንዲወጣ በአጽንዖት አሳስበዋል፡፡

በመቶዎች የሚቆጠሩት ደቀ መዛሙርቱ፣ በጠቅላይ ጽ/ቤቱ የአስተዳደር ሕንፃ ፊት ለፊት ድምፃቸውን በሚያሰሙበት ወቅት፣ በማን እንደተጠራ ያልታወቀ የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ኀይል በብዛት ወደ ግቢው በመግባት ሊያከላክላቸውና ከቅጽሩም ሊያስወጣቸው ሞክሯል፡፡ በማን ጥሪና ፈቃድ እንደመጡና እንደገቡ የጠየቋቸው ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ፣ ያለጥሪና ያለፈቃድ መግባትና ማከላከል ማድረግ እንደማይችሉ ለፖሊሶቹ ገልጸውላቸው ግቢውን ለቀው ወጥተዋል፡፡

ደቀ መዛሙርቱ ድምፃቸውን ያሰሙበት ሰዓት፣ የቋሚ ሲኖዶሱ ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባ የሚካሔድበት ቢኾንም፣ በአካል ወጥቶ ያነጋገራቸው ሓላፊ ወይም አባት አልነበረም፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊን ጨምሮ የቋሚ ሲኖዶሱ ተለዋጭ አባላትና ሌሎች ብፁዓን አባቶች፣ በቅዱስ ፓትርያርኩ እና በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ መካከል እየተካረረ የመጣውን አለመግባባት በመሸምገል ላይ እንደነበሩ ታውቋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስን፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስን፣ ብፁዕ አቡነ ዳንኤልንና ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን ያካተተው የሽምግልና ጥረት፣ ትላንት ከብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ጋራ በስፋት በመወያየት ነው የተጀመረው፤ በዛሬው ዕለት ደግሞ ቅዱስ ፓትርያርኩን አነጋግረዋል፡፡ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ፣ ዘግይቶ ከቢሯቸው ተጠርተው እንደሔዱና በመግባባት ሳይቋጭ እንዳልቀረ ተጠቁሟል፤ በደብዳቤ መወራወሩ መቆም አለበት፤ ሰላም መኾን አለበት፤ ብለዋል አነጋጋሪ ብፁዓን አባቶች፡፡

theo college11theo college12theo college13

Share this post

One thought on “ቤተ ክርስቲያንን ከጥቃት ለመታደግ: ቅዱስ ሲኖዶስ የእረኝነት፣ መንግሥት የሕግ አስጠባቂነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ደቀ መዛሙርቱ ጠየቁ፤ “ለዝምታም ኾነ ትዕግሥት መጠንና ልክ አለው!”

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.