ቤጉህዴፓ ሀገራዊ ውህድ የብልጽግና ፓርቲን ለመዋሃድ ወሰነ

Source: https://fanabc.com/2019/11/%E1%89%A4%E1%8C%89%E1%88%85%E1%8B%B4%E1%8D%93-%E1%88%80%E1%8C%88%E1%88%AB%E1%8B%8A-%E1%8B%8D%E1%88%85%E1%8B%B5-%E1%8B%A8%E1%89%A5%E1%88%8D%E1%8C%BD%E1%8C%8D%E1%8A%93-%E1%8D%93%E1%88%AD%E1%89%B2-2/

አዲስ አበባ፣ ህዳር 15፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉህዴፓ) ሀገራዊ ውህድ የብልጽግና ፓርቲን ለመዋሃድ ወሰነ፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉህዴፓ)  ዛሬ በአሶሳ ከተማ ባካሄደው አስቸኳይ ድርጅታዊ ጉባዔ የኢህአዴግ እና አጋር ድርጅቶች ውህድ የሆነውን የብልጽግና ፓርቲን እንደሚዋሃድ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

የቤጉህዴፓ ሊቀ መንበር አቶ አድጎ አምሳያ በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር ÷ “ክልሉን በመራባቸው ባለፉት ዓመታት በተደረጉ ጥረቶች ተጨባጭ ለውጦችን አስመዝግቧል” ብለዋል።

ፓርቲው እንደ ሀገር ሊያበረክት የሚገባውን አስተዋጽዖ ለማበርከትም ሆነ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በባለቤትነት ለመሳተፍና ለመወሰን ዕድል ተነፍጎት እንደቆዬ አንስተዋል።

ለውጡን ተከትሎ ኢህአዴግ እና አጋር ድርጅቶች የሚያደርጉት ውህደት ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጎልበት ሁሉም ዜጎች ያለመድሎ በሀገራቸው ጉዳይ በጋራ ለመምከርና ለመወሰን የሚያስችላቸውን ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አቶ አድጎ ተናግረዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ህዝቦች በሕብረ ብሔራዊ ጥላ ስር ሆነው ከሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች ጋር ተደምረውና ተባብረው ለላቀ የሀገር ብልጽግና እንዲተጉ የሚያስችል ስለመሆኑም አብራርተዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በበኩላቸው÷ “ውህደቱ በሀገር ጉዳይ ባይተዋር ከመሆን ይልቅ በጋራ የመምከርና የጋራ ውሳኔ ለማሳረፍ ከማስቻሉም በላይ የህዝቦችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረግጥ ነው” ብለዋል።

የክልሎችን በራስ የማስተዳደር ሕገ መንግስታዊ መብት ይበልጥ በማጠናከር ከሌሎች የሀገሪቱ ህዝቦች በባለቤትነት ስሜት በጋራ ሆነው ጠንካራ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፍጠር እንደሚያስችልም ገልፀዋል።

የቤጉህዴፖ ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይስሃቅ አብዱልቃድርም÷ ባለፉት ዓመታት ከነበሩት አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች ውጪ የሚገኙ ድርጅቶችን “አጋር” የሚለው አሰራር አግላይ በመሆኑ፤ በሀገራቸው ጉዳይ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው አድርጎ ቆይቷል ያሉት።

የብልጽግና ፓርቲ ያለፉትን ግድፈቶች በማረም ጠንካራ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ቅቡልነት ያለው ዘላቂ ሀገረ መንግስት ለመገንባት እንደሚያስችልም መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ቤጉህዴፓ በድርጅታዊ ጉባዔው የውህደቱን አስፈላጊነት ያረጋገጠ ሲሆን÷ በቀጣይም ለክልሉ ሕዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የተጀመሩ በርካታ ሥራዎችን ለማስቀጠል የጋራ ጥረቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.