ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጅግጅጋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነው ተመደቡ፤ ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም በኢኦተቤ-ቴቪ አስተባበሉ

Source: https://haratewahido.wordpress.com/2017/05/19/%E1%89%A5%E1%8D%81%E1%8B%95-%E1%8A%A0%E1%89%A1%E1%8A%90-%E1%88%9B%E1%89%B4%E1%8B%8E%E1%88%B5-%E1%8B%A8%E1%8C%85%E1%8C%8D%E1%8C%85%E1%8C%8B-%E1%88%80%E1%8C%88%E1%88%A8-%E1%88%B5%E1%89%A5%E1%8A%A8/
http://1.gravatar.com/avatar/7f09202441ad3b4b636e88820d6a7061?s=96&d=identicon&r=G
  • የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን የገዳማት አስተዳደር መምሪያ፣ በበላይ ሓላፊነት ይመራሉ
  • የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተጠናቀቀ፤ በመጪው ሰኞ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል
  • ዶ/ር አባ ኃይለ ማርያም፣ በተነሣባቸው አቤቱታ፣ ለኢኦተቤ-ቴቪ ማስተባበያ ሰጡ

    *                      *                    *

ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ

የወላይታ እና ዳውሮ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ፣ ወደ ሶማል/ጅግጅጋ/ ሀገረ ስብከት ተዛውረው እንዲሠሩና በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የገዳማት አስተዳደር መምሪያን፣ በበላይ ሓላፊነት እንዲመሩ በምልአተ ጉባኤው ተመደቡ፡፡

በምደባው መሠረት፣ ብፁዕነታቸው በተዛወሩበት ሀገረ ስብከት ሥራቸውን የሚጀምሩት፣ የተመረጡት ኤጲስ ቆጶሳት ሢመተ ጵጵስና ከተፈጸመ በኋላ እንደሚኾንና እስከዚያው ድረስ አኹን ባሉበት ሀገረ ስብከት እንደሚቆዩ ተገልጿል፡፡

ላለፉት ዐሥራ አንድ ቀናት ሲካሔድ የቆየው፣ የ፳፻፱ ዓ.ም. የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ በዛሬው ዕለት ቃለ ጉባኤዎችን በመፈራረም ተጠናቋል፤ ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት፣ በቋሚ ሲኖዶሱ የሚሠሩ ተለዋጭ አባላትንም መርጧል፡፡

እስከ ሐምሌ 30 ቀን ባሉት ቀጣዮቹ ሦስት ወራት፣ የቋሚ ሲኖዶሱ አባል ኾነው የሚሠሩት አራት ብፁዓን አባቶች፥ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ እና ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ ሲኾኑ፤ በምልአተ ጉባኤው የጸደቁትን ሕግጋት፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና ውሳኔዎች በሥራ ላይ መተርጐማቸውን መከታተልና መቆጣጠር ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከምልአተ ጉባኤው ዐበይት ውሳኔዎች አንዱ፣ በቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ችግሮች ላይ የተጠናውና የቤተ ክህነቱን መዋቅር፣ ሕግና የአሠራር ሥርዓት መልሶ ማደራጀትና ማሻሻል እንደሚያስፈልግ የሚያመለክተው ጥናት ነው፡፡ የአጥኚ ቡድኑን ማብራሪያ በማዳመጥ በጥናታዊ ሪፖርቱ ላይ የተወያየው ምልአተ ጉባኤው፣ በተጨማሪ ባለሞያ ተመርምሮ ለቋሚ ሲኖዶሱ እንዲቀርብ በመወሰኑ፣ መልክና ቅርጽ ይዞ እንዲተገበር ኹኔታዎችን በማመቻቸት ረገድ የተጣለበትን ከፍተኛ ሓላፊነት እንደሚወጣ ተስፋ ይደረጋል፡፡

የምልአተ ጉባኤውን ሒደትና ውሳኔዎች በተመለከተ፣ በመጪው ሰኞ ረፋድ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡

በተያያዘ ዜና፣ ከ16ቱ ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት አንዱ ኾነው በዕጣ የተመረጡት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ አባ ኃይለ ማርያም መለሰ(ዶ/ር)፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ለተሠራጨባቸውና ምልአተ ጉባኤው እንዲጣራ ባዘዘው የ”መቀባባት” አቤቱታ፤ ዛሬ፣ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቴሌቭዥን(EOTC-Tv) ማስተባበያ መስጠታቸው ተሰማ፡፡

በቃለ ምልልስ መልክ በተሰጠው ማስተባበያቸው፦ የካቲት 22 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ በደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የተከናወነውን፣ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት “የጸሎት ሥነ ሥርዓት” በጋራ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንጅ የቡራኬ እንዳልነበረ፤ እርሳቸውም ቤተ ክርስቲያኒቱን ወክለው እንዲያስተባብሩ በተወከሉት መሠረት መርሐ ግብሩን መምራታቸውን፤ ውኃና እምነት ተበጥብጦ እንደቀረበና እርሱን በትእምርተ መስቀል መቀባታቸውንና እርሳቸው ግን በፍጹም እንዳልተቀቡ፤ ቅብዓ ቅዱስ እና ሜሮን እንዳልነበረ፤ ለተሿሚነትም የተመረጡት በፈቃደ እግዚአብሔር እንደኾነ፤ ማስረጃው በወቅቱ ቢቀርብ ማብራሪያ ሊሰጡበት ይችሉ እንደነበርና የሢመተ ጵጵስናው ወቅት ተጠብቆ መሠራጨቱ ተገቢ እንዳልኾነ በመጥቀስ ቅሬታቸውን መግለጻቸው ተመልክቷል፡፡

Advertisements

Share this post

Post Comment