ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ጥምቀትን በጎንደር ያከብራሉ

Source: https://haratewahido.wordpress.com/2019/01/12/%E1%89%A5%E1%8D%81%E1%8B%95-%E1%8B%88%E1%89%85%E1%8B%B1%E1%88%B5-%E1%8A%A0%E1%89%A1%E1%8A%90-%E1%88%98%E1%88%AD%E1%89%86%E1%88%AC%E1%8B%8E%E1%88%B5-%E1%8C%A5%E1%88%9D%E1%89%80%E1%89%B5%E1%8A%95/
https://haratewahido.files.wordpress.com/2019/01/fb_img_1533132080587.jpg
  • ከስደት መልስ ከአዲስ አበባ ውጭ የመጀመሪያ ጉብኝታቸው ነው፤
  • ጉብኝታቸውን ከአኵስም ለመጀመር የተያዘው ዕቅድ አልተሳካም፤

***

fb_img_1533132080587

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ከ26 ዓመታት ስደት ወደ ሀገር ከተመለሱ በኋላ ከአዲስ አበባ ውጭ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን በጎንደር የሚጀምሩ ሲኾን፣ በዓለ ጥምቀትንም በዚያው ያከብራሉ፡፡

ቅዱስነታቸው ዛሬ ማለዳ፥ ከብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ እና በጠቅላይ ጽ/ቤት የገዳማት አስተዳደር የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ጋራ በመኾን ወደ ጎንደር አቅንተዋል፡፡

እስከ ጥር 13 ቀን ድረስ በሚዘልቀው በዚሁ አባታዊ ጉብኝታቸው ጎንደርን ጨምሮ በባሕር ዳር እና በደብረ ታቦር ከተሞች እየተዘዋወሩ ቡራኬ የሚሰጡበት መርሐ ግብር እንደተያዘላቸው ታውቋል፡፡ ከአቀባበል መርሐ ግብር ጀምሮ የስብከተ ወንጌል እና የሰላም ተልእኮ ያለው ጉዞ እንደኾነ ተጠቁሟል፡፡

የጉብኝት መርሐ ግብሩን ከአኵስም በመጀመር ለማካሔድ ታቅዶ ለሚመለከታቸው የክልሉ አካላት በጽሑፍ ጥያቄ በማቅረብ የተለያዩ ሙከራዎች ተደርጎ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ ኾኖም፣ በፓትርያርክ ደረጃ የሚመጥንና የሚገባቸውን ዝግጅት አድርጎ ለመቀበልና ለማስተናገድ ምንም ዓይነት ምላሽ ባለመሰጠቱ፣ የአኵስም ጉብኝት ተሰርዞ በጎንደር መጀመሩ ተገልጿል፡፡

“ከአሜሪካ እንደተመለሱ፣ ከአዲስ አበባው አቀባበል ቀጥሎ ወደ ጎንደር እንዲመጡ ጥያቄ ቀርቦ ነበር፤ ጉብኝቱ ከአኵስም መጀመር አለበት ተብሎ ነበር የዘገየው፤ ዋናውን ቦታ ተሳልሞ ወደ ሌሎች ለመቀጠል ነበር ዕቅዱ፤ ለዚህም ከደኅንነት ጉዳይ ጀምሮ አመቻችተው እንዲቀበሉ ደብዳቤ ተጽፎ የተለያዩ ሙከራዎች ቢደረጉም፣ ምንም ዓይነት ምላሽ ከዚያ አልመጣም፤ ለማስተናገድና ለመቀበል ምንም ዓይነት ዝግጁነት ባለማሳየታቸው የአኵስም ጉብኝታቸው ተሰርዞ ቀጥታ ወደ ጎንደር ይሔዳሉ፤ በዚሀም አዝነዋል፤” ብለዋል የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች፡፡

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.