ቦሪስ ጆንሰን በብሪታንያ እና የአውሮፓ ህብረት ፍቺ ዙሪያ ከሜርክል ጋር ሊወያዩ ነው

Source: https://fanabc.com/2019/08/%E1%89%A6%E1%88%AA%E1%88%B5-%E1%8C%86%E1%8A%95%E1%88%B0%E1%8A%95-%E1%89%A0%E1%89%A5%E1%88%AA%E1%89%B3%E1%8A%95%E1%8B%AB-%E1%8A%A5%E1%8A%93-%E1%8B%A8%E1%8A%A0%E1%8B%8D%E1%88%AE%E1%8D%93-%E1%88%85/

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 15 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ከጀርመኗ መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ጋር ሊወያዩ ነው።

ቦሪስ ጆንሰን ከቡድን ሰባት ስብሰባ ቀደም ብሎ ከሜርክልና ከፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ይወያያሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውይይታቸው ሜርክል ብሪታንያ ህብረቱን ለቃ በምትወጣበት ሂደት ላይ ከዚህ በፊት የያዙትን አቋም እንዲቀይሩ ይጠይቋቸዋል ተብሏል።

ቦሪስ ጆንሰን ሃገራቸው ህብረቱን ለቃ በምትወጣበት ሂደት ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ፍላጎት አላቸው።

በዚህም ሜርክል የቀድሞዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬዛ ሜይ ከህብረቱ ጋር በደረሱት ስምምነት ላይ የያዙትን አቋም እንዲቀይሩ ለማሳመን እሞክራለሁ ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሜርክል ከዚህ ቀደም በተደረሰው ስምምነት ላይ የያዙትን አቋም ይቀይሩ ከማለታቸው ውጭ ግን በምን እና እንዴት ባሉ ሁኔታዎች የሚለውን አላነሱም።

ብሪታንያ ህብረቱን ለቃ ስትወጣ ከአየርላንድ ጋር የሚኖረው የድንበር እና ከህብረቱ ጋር የሚኖራት ቀጣይ የንግድ ልውውጥ ጉዳይ ላይ ማስተካከያዎች እንዲኖሩ ፍላጎት እንዳላቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።

ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ብሪታንያ በተቀመጠው ቀነ ገደብ የአውሮፓ ህብረትን ያለ ስምምነት ለመልቀቅ ትገደዳለች ሲሉም ተደምጠዋል።

ይህ የእርሳቸው እቅድ ግን ከበርካቶች ለብሪታንያ ከባድ ጊዜን ያመጣል በሚል ትችት አጋጥሞታል።

ብሪታንያ ህብረቱን ያለምንም ስምምነት ለመልቀቅ ከወሰነች፥ ከባድ ኢኮኖሚያዊ ቀውስና በዲፕሎማሲው መስክ የመነጠል አደጋን ያስከትላል ሲሉም ያስጠነቅቃሉ።

ሜርክል በበኩላቸው የብሪታንያ የፍቺ ጉዳይ ለድርድ የማይቀርብ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከአየርላንድ ጋር የሚኖረው የድንበር ጉዳይ ግን ለንግግር ክፍት መሆኑን ገልጸዋል።

 

 

ምንጭ፦ ሬውተርስና ቢቢሲ

 

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.