ቦይንግ ለአውሮፕላን አደጋ ተጎጂ ቤተሰቦች የ144 ሺህ 500 ዶላር ሊሰጥ ነው

Source: https://fanabc.com/2019/09/%E1%89%A6%E1%8B%AD%E1%8A%95%E1%8C%8D-%E1%88%88%E1%8A%A0%E1%8B%8D%E1%88%AE%E1%8D%95%E1%88%8B%E1%8A%95-%E1%8A%A0%E1%8B%B0%E1%8C%8B-%E1%89%B0%E1%8C%8E%E1%8C%82-%E1%89%A4%E1%89%B0%E1%88%B0%E1%89%A6/

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የአሜሪካው ቦይንግ ኩባንያ በቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ተጎጂ ቤተሰቦች ለእያንዳንዳቸው 144 ሺህ 500 የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ  ሊያደርግ መሆኑ ተገለፀ።

ድጋፉ ቦይንግ ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ከገባው 100 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላይ የገንዘብ ድጋፍ ውስጥ የሚሰጥ መሆኑም ተነግሯል።

ከአውሮፓውያኑ 2020 በፊት ለሚያመለክቱ ለእያንዳንዱ የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ተጎጂ ቤተሰቦች እና ዘመዶች ገንዘቡ የሚሰጥ መሆኑንም ነው ኩባንያው ያስታወቀው።

የአሜሪካው ቦይንግ ኩባንያ ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ በቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን አደጋ ተጎጂ ቤተሰቦች የ100 ሚልየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጹ ይታወሳል።

ቦይንግ ኩባንያ ገንዘቡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በኢንዶኒዢያው ላየን ኤይር ባጋጠመው ሁለት የአውሮፕላን አደጋዎች ህይወታቸውን ላጡ የ346 ሰዎች ቤተሰቦች እና ተፅዕኖ ለደረሰባቸው ማኅበረሰቦች መደገፊያ የሚውል መሆኑም  ገልጾ ነበር።

ኩባንያው ከ100 ሚሊየን ዶላሩ ውስጥም ግማሹ ለተጎጂ ቤተሰቦች እና ዘመዶች በቀጥታ የሚከፈል መሆኑን እና ቀሪው 50 ሚሊየን ዶላር ደግሞ አደጋው ተዕእኖ ለተፈጠረባቸው ማህበረሰበ ለትምህርት ቤትና ሌሎች የልማት ስራዎች እንደሚውል ነው ያስታወቀው።

ሆኖም ግን ቦይንግን ፍርድ ቤት ማቆም የሚፈልጉ የተጎጂ ቤተሰቦች ጠበቆች ቦይንግ ያቀረበውን የገንዘብ ድጋፍ ውድቅ ማድረጋቸው ነው የተነገረው።

መቀመጫቸውን አሜሪካ ቴክሳስ ያደረጉት እና 15 ቤተሰቦችን የወከሉት ጠበቃ ኖማን ሁሴይን፥ “ቦይንግ እከፍላለሁ ያለው 144 ሺህ ዶላር በቤተሰቦቻችን ላይ የደረሰውን ጉዳይ አይክስም” ብለዋል።

“ይህ ገንዘብ የጎጂ ቤተሰቦችን ፍላጎት የሚያሟላ አይደለም፤ የተጎጂ ቤተሰቦች ትክክለኛ ምላሽ ነው የሚፈልጉት” ሲሉም ተደምጠዋል።

ባሳለፍነው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ በመብረር ላይ የነበረ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ተከስክሶ የ157 ሰዎች ህይወት ማለፉ የሚታወስ ነው።

በተመሳሳይ በ2011 ዓ.ም በጥቅምት ወር ላይ የኢንዶኔዢያው የላየን አየር መንገድ ንብረት የሆነ ቦይንግ አውሮፕላን ተከስክሶ የ189 ሰዎች ህይወት አልፏል።

እነዚህን ሁለት አደጋዎች ተከትሎ በአለም አቀፍ ደረጃ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ከበረራ እንዲታገዱ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን፥ አውሮፕላኖቹ መቼ ወደ በረራ ይመለሳሉ የሚለውም እስካሁን አልታወቀም።

ምንጭ፦ www.bbc.com

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.