ተማሪዎች አደባባይ በመውጣት ሀዘናቸውን ገለጹ

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%89%B0%E1%88%9B%E1%88%AA%E1%8B%8E%E1%89%BD-%E1%8A%A0%E1%8B%B0%E1%89%A3%E1%89%A3%E1%8B%AD-%E1%89%A0%E1%88%98%E1%8B%8D%E1%8C%A3%E1%89%B5-%E1%88%80%E1%8B%98%E1%8A%93%E1%89%B8%E1%8B%8D%E1%8A%95/

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 6/2010)

የጨለንቆውን ጭፍጨፋ በማውገዝ የኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች የሚማሩ ተማሪዎች አደባባይ በመውጣት ሀዘናቸውን ገለጹ።

በተለይ በወለጋ ነቀምት ጥቁር ልብስ የለበሱት ተማሪዎች በሰልፍ ወጥተው ግድያውን በማውገዝ ላለቁት ወገኖች ሀዘናቸውን ገልጸዋል።

ከአንድ ቤተሰብ 5 ሰዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 18 ሰዎች የተገደሉበት የባለፈው ሰኞ የጨለንቆው ጭፍጨፋ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ግድያውን በማውገዝ በሂደቱ ተሳታፊ የሆኑትን ለፍርድ ለማቅረብ እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

የመከላከያ ሰራዊቱ ያለ ኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፈቃድ መግባቱንም አስታውቀዋል።

ቢቢሲ ግድያውን በተመለከተ ባጠናቀረው ዘገባ እንዳመለከተው ሳሊ ሃሰን ኢብሮና አብዲ ሳሉ የተባሉ አባትና ልጅ እንዲሁም ሚካኤል አብዱ ሀሰን የተባሉ ወንድማማቾችና አብደላ ኢሳ የተባለ አምስቱም የአንድ ቤተሰብ አባላት ባለፈው ሰኞ ታህሳስ 2/2010 በእርሻ ማሳቸው ላይ እንዳሉ ተገድለዋል።

ሟቾቹ ከ15 እስከ 60ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ መሆናቸውም ተመልክቷል።

ሜታ በተባለው ወረዳ ሰርከማ በተባለ መንደር የሶማሌ ልዩ ሃይል ፖሊስ ድንገት በከፈተው ጥቃት አንድ የማህበረሰቡን ታዋቂ ሰው መግደሉ፣በአካባቢው ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ምክንያት መሆኑም ተመልክቷል።

ለተቃውሞ አደባባይ የወጡት ወጣቶች የመከላከያ ሃይል ሲመጣ የመኪና መንገድ ዘግተዋል።

በመጨረሻም እንደማያቆሟቸው ሲያውቁ ተደዋውለው ከአካባቢው መሰወራቸውን የቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ዘገባ ያመለክታል።

የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት ግን ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸው፣ ሌላው ቀርቶ ተቃውሞ እንኳን እየተካሄደ መሆኑን በማያውቁት ግለሰቦች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ግድያ ፈጽመዋል።

ከጨለንቆ 6 ኪሎ ሜትር ርቀት ጂያ ዴራ በተባለ ቦታ በሚገኝ የእርሻ ቦታ ላይ በደቦ የማሽላ ምርት ለመሰብሰብ የሔዱት ሰዎች ስራቸውን አከናውነው አረፍ ባሉበት ሰራዊቱ ድንገት በከፈተባቸው የእሩምታ ተኩስ 5 የአንድ ቤተሰብ አባላትን ጨምሮ 18 ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።

5 የቤተሰባቸውን አባላት በአንድ ጊዜ ያጡት አቶ አብዱሰላም አባድር ሀሰን ለቢቢሲ እንደገለጹት የሟቾቹንም ቀብር ለማስፈጸም ችግር ገጥሟቸዋል።

በተሽከርካሪና በከባድ መሳሪያ ተደግፈው የመጡት የመከላከያ ሰራዊት አባላት የሟቾቹ ቀብር አንድ ቦታ እንዳይፈጸምና በተለያየ ቦታ እንዲቀበሩ እንዳስጠነቀቋቸውም አቶ አብዱሰላም ገልጸዋል።

“ወታደሮቹ ልክ የጠላትን ሃይል የረቱ ይመስል የፌደራሉን ባንዲራ እያውለበለቡ መጡ፣እኛ በባንዲራው ላይ ልዩነት የለንም፣እኛም የፌደራሉን ባንዲራ እናውለበልባለን ትምህርት ቤት የሚውለበለበውም እሱ ነው” ሲሉ አብዱሰላም አባድር ገልጸዋል።

 

 

 

 

 

 

The post ተማሪዎች አደባባይ በመውጣት ሀዘናቸውን ገለጹ appeared first on ESAT Amharic.

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.