ተማሪ ሃይማኖት በዳዳን በመግደል ወንጀል ምርመራ ሲደረግበት የነበረው ደግነት ወርቁና 2ኛ ተከሳሽ ምህረቱ ሚጣ ላይ ክስ ተመሰረተ

ተማሪ ሃይማኖት በዳዳን በመግደል ወንጀል ምርመራ ሲደረግበት የነበረው ደግነት ወርቁና 2ኛ ተከሳሽ ምህረቱ ሚጣ ላይ ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2013(ኤፍ.ቢ.ሲ) ግንቦት 17 ቀን 2012 ዓ.ም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በቤተ ሙከራ ክፍል ውስጥ ተማሪ ሃይማኖት በዳዳን በመግደል የወንጀል ምርመራ ሲደረግበት የነበረው ደግነት ወርቁ በውንብድና ወንጀል እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ ምህረቱ ሚጣ ላይ ደግሞ በከባድ የመሸሸግ ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ክሱ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የከባድ የውንብድና ወንጀል ችሎት የተመሰረተ ሲሆን፥ በተረኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት መዝገቡ ታይቷል።

የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በሁለቱ ተከሳሾች ላይ ሁለት ክስ ነው እንደተሳትፏቸው መጠን ክስ የመሰረተው።

የዐቃቤ ህግ ክስ እንደሚያመላክተው 1ኛ ተከሳሽ ደግነት ወርቁ የወንጀል ህግ 671 ንኡስ ቁጥር 2 ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላላፍ በከባድ ውንብድና ወንጀል ለመፈጸም እና የማይገባ ብልጽግና ለማግኘት ወይም ለሌላ አካል ለማስገኘት በማሰብ በግንቦት 17 ቀን 2012 ዓ.ም በጥቁር አንበሳ ስፔሻላየዝድ ሆስፒታል መግባቱ በክሱ ተመላክቷል።

በእለቱም ወደ ኬሚስትሪ ላብራቶሪ ለመግባት ከሞከረ በኋላ ተማሪ ሃይማኖት በዳዳ እጇ ላይ ቦርሳ አንጠልጥላ ወደ ፋርማሲ ላብራቶሪ ስትገባ በመመልከቱ ፕሮፖዛል የያዘ በማስመሰል ነጭ ወረቀት ይዞ ገብቶ በር ከውስጥ መዝጋቱ በክሱ ተጠቅሷል።

ወደ ሟች ሃይማኖት በመጠጋት ያለሽን አምጪ ማለቱን በክሱ የጠቀሰው ዐቃቤ ህግ ቢላ አውጥቶ በማስፈራራት በእጇ የያዘችውን አይፎን ስልክ እንድትሰጠውና ፓተርን እንድትከፍትለት ሲጠይቋት አልከፍትም አልሰጥም ማለቷን ተከትሎ ገፍትሮ መሬት ላይ በመጣል እራሷን ለመከላከል ስትሮጥ እጇ ላይ ጉዳት ካደረሰ በኋላ ጭካኔ በሞላበት ሁኔታ በአንገቷ ላይ ጥቃት በማድረስ ህይወቷን ማጥፋቱን ዐቃቤ ህግ በክሱ አመላክታል።

በዛው ሰአት ማስረጃ የማጥፋት ስራ መስራቱን የገለጸው ዐቃቤ ህግ ከቦርሳዋ ውስጥ 400 ብር፣ የ5 ሺህ ብር ቼክ፣ ላፕቶፕ እና አይፎን ሞባይል ስክል በመውሰድ ከውጭ በሩን ቆልፎ መውጣቱን በክሱ ተገልጻል።

በ2ኛ ክስ ደግሞ የወንጀል ህግ 683/ሐ’ን በመተላለፍ በከባድ መሸሸግ ወንጀል ክስ የተመሰረተበት 2ኛ ተከሳሽ ምህረቱ ሚጣ ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር በአንድ ቤት ወስጥ ተከራይተው እንደሚኖሩ ዐቃቤ ህግ በክሱ ጠቅሷል።

በእለቱ 1ኛ ተከሳሽ ወደዚህ ቤት በመሄድ ለ2ኛ ተከሳሽ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሰው አስሬ ነው የመጣሁት ብሎ በመግለጽ የወሰደውን ስልክ፣ ላፕቶፕ እና ቼክ እንዲሁም 400 ብሩን በመናገር የወሰደውን የ5 ሺህ ብር ቼክ ከአዋሽ ባንክ በመመንዘር 2 ሺህ ብር ለ2ኛ ተከሳሽ ሲሰጠው አንድ ሞባይል ገዝቶ ሲጠቀም በመያዙ በመሸሸግ ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።

ተከሳሾቹ ክሱ የደረሳቸው እና ያቀረቡትን ዋስትና ጥያቄ ውድቅ ያደረገው ፍርድ ቤቱ ጠበቃ ለማቆም አቅም የለንም ማለታቸውን ተከትሎ የመንግስት ተከላካይ ጠበቃ እንዲመደብላቸው እና ተማክረው እንዲቀርቡ ክሱን ለማንበብ ለመስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰቷል።

እስከዚያው በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ፍርድ ቤቱ አዟል።

በታሪክ አዱኛ

The post ተማሪ ሃይማኖት በዳዳን በመግደል ወንጀል ምርመራ ሲደረግበት የነበረው ደግነት ወርቁና 2ኛ ተከሳሽ ምህረቱ ሚጣ ላይ ክስ ተመሰረተ appeared first on Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C.

Source: Link to the Post

Leave a Reply