ቱርክ በሶሪያ የሚገኙ የውጭ ሃይሎች እስኪወጡ ድረስ በስፍራው ትቆያለች-ኤርዶሃን

Source: https://fanabc.com/2019/11/%E1%89%B1%E1%88%AD%E1%8A%AD-%E1%89%A0%E1%88%B6%E1%88%AA%E1%8B%AB-%E1%8B%A8%E1%88%9A%E1%8C%88%E1%8A%99-%E1%8B%A8%E1%8B%8D%E1%8C%AD-%E1%88%83%E1%8B%AD%E1%88%8E%E1%89%BD-%E1%8A%A5%E1%88%B5%E1%8A%AA/

አዲስ አበባ፣ጥቅምት 29፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ቱርክ በሶሪያ የሚገኙ የውጭ ሃይሎች ሀገሪቱን ለቀው እስኪወጡ ድረስ በስፍራው የምትቆይ መሆኑን የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ተናግረዋል።

አንካራ በቅርቡ በሰሜን ሶሪያ የሚንቀሳቀሱ የኩርድ አማጺያንን ከስፍራው ለማስወገድ ያለመ የጸረ ሽብር ዘመቻ ማካሄድ መጀመሯ ይታወሳል።

በዚህም በአሜሪካ እንደሚደገፉ የሚነገርላቸው እና በቱርክ በአሸባሪነት የተፈረጁት በርካታ የኩርድ አማጺያን ቦታውን ለቀው መውጣታቸው ተነግሮ ነበር።

ይሁን እንጂ አማጽያኑ እንደተባለው በስፋት የሚንቀሳቀሱበትን የሰሜን ሶሪያ ቀጠና ለቀው እየወጡ አለመሆናቸውን ቱርክ አስታውቃለች።

ፕሬዚዳንት ኤርዶሃን በትናንትናው ዕለት ጉዳዩን እስመልክተው በሰጡት መግለጫ፥ በሶሪያ የሚገኙ የውጭ ሃይሎች ሀገሪቱን ለቀው አስካልወጡ ድረስ የቱርክ ወታደሮች በቦታው የሚቆዩ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ የሚንቀሳቀሱት የኩርድ አማጺያን ቀጠናው ለቀው እስኪወጡ ድረስ ቱርክ በአካባቢው የምታከናውነውን የጸረ ሽብር ዘመቻ አጠናክራ ትቀጥላለች ነው ያሉት።

ቱርክ በሰሜን ሶሪያ  ጥቃት መሰንዘር የጀመረችው በቀጠናው ለመመስረት ያቀደችውን “ደህንነቱ የተጠበቀ ቀጠናን” በስፍራው ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሃይሎች ለማስለቀቅ ነው።

በዚህ የሰላም ቀጠናም ከተለየዩ የሶሪያ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ከሁለት ሚሊየን በላይ ሶሪያውያን ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ታስቧል።

ምንጭ ፦አልጀዚራ

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.