ታቦታትን ጨምሮ ከመቅደላ የተዘረፉ ቅርሶች፣ “በውሰት ሊመጡ ነው፤” መባሉን መንግሥት አላወቅም አለ፤ “ከማስመለስ በመለስ መዋስን በፍጹም አናስበውም”

Source: https://haratewahido.wordpress.com/2018/04/09/%E1%89%B3%E1%89%A6%E1%89%B3%E1%89%B5%E1%8A%95-%E1%8C%A8%E1%88%9D%E1%88%AE-%E1%8A%A8%E1%88%98%E1%89%85%E1%8B%B0%E1%88%8B-%E1%8B%A8%E1%89%B0%E1%8B%98%E1%88%A8%E1%8D%89-%E1%89%85%E1%88%AD%E1%88%B6/
http://1.gravatar.com/avatar/7f09202441ad3b4b636e88820d6a7061?s=96&d=identicon&r=G
 • ቅርሶቹ፣ በእንግሊዝ የቪክቶሪያ አልበርት ሙዝየም፣ለአንድ ዓመት ኤግዚቢሽን ቀረቡ
 • ከ10 በላይ ታቦታት፣ ከ500 በላይ መጻሕፍት፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ይገኙበታል
 • ኢግዚቢሽኑን አንቃወመውም፤የተዘረፉ ቅርሶቻችን እንደኾኑ ግን ሊሠመርበት ይገባል
 • ኢትዮጵያን ለዓለም ለማስተዋወቅ እና የኛ እንደኾኑም ለማረጋገጥ ዕድሉን ይፈጥራል

†††

 • በ2007 ለእንግሊዝ መንግሥት ጥያቄ አቅርበናል፤በማስመለሱ ላይ አተኩረን እንገፋለን
 • የረጅም ጊዜ ውሰት”የሙዝየሙ ዳይሬክተር የተናገሩት እንጅ የመንግሥታቱ አይደለም
 • መዋስ ማለት በግማሽ መንገድ ሕጋዊነት እየሰጠን ነው፤ ከዘረፈን ጋራም አንደራደርም
 • ማስመለሱ የትውልድ ፕሮጀክት ነው፤የፈጀውን ጊዜ ቢፈጅ መዋስን በፍጹም አናስብም

†††

ከ150 ዓመታት በፊት(በ1868 እ.አ.አ) በኢትዮጵያ እና ብሪታኒያ መካከል መቅደላ ላይ በተደረገው ጦርነት የተዘረፉና በቪክቶሪያ አልበርት ሙዝየም የሚገኙ ቅርሶች፣ “በውሰት በኢትዮጵያ ለእይታ ሊበቁ ነው፤” የሚለው መረጃ ትክክለኛ ያልኾነና መንግሥት የማያውቀው መኾኑ ተገለጸ፡፡

“ኢትዮጵያን የሚዘክሩ የኢትዮጵያ ቅርሶች የሚገቡት ለኢትዮጵያውያን ነው፤” ያለው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ለማስመለስ ጥረት እያደረገ መኾኑንም አስታውቋል፡፡

47a810410567557a6f2ef4ec2b18ae30_L

ሚኒስትሯ ዶ/ር ሒሩት ወልደ ማርያም፣ ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ፣ መጋቢት 29 ቀን ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ ቢቢሲንና ዘጋርድያንን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የኅትመትና የኤሌክትሮኒክስ ብዙኃን መገናኛዎች፣ “ቅርሶቹ በረጅም ጊዜ ውሰት(long-term loan) ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው፤ በሚባለው ነገር እኛን ያማከረን የለም፤ መንግሥትም ኾነ ሚኒስቴሩ የተወያየንበት የምናውቀው ነገር የለም፤ ሊኾንም አይችልም፤” ብለዋል፡፡

ከመቅደላ የተወሰዱት ቅርሶች በእንግሊዝ የቪክቶሪያ አልበርት ሙዚየም ለአንድ ዓመት ለተመልካች ክፍት የተደረጉበት ኢግዚቢሽን ሲከፈት የሙዝየሙ ዳይሬክተሩ ባቀረቡት ንግግር ላይ ያነሡት ሐሳብ መኾኑን የጠቀሱት ዶ/ር ሒሩት፦ የእንግሊዝም የኢትዮጵያም መንግሥት አቋም እንዳልኾነና ይልቁንም ቅርሶቹ የኢትዮጵያ ንብረት እንደመኾናቸው ለማስመለስ መንግሥት በድርድር ላይ እንደሚገኝ፣ ባቀረበው ጥያቄም እንደሚገፋበት ገልጸዋል፡፡

“እንግዲህ ማንም ሐሳብ ሊሰጥ ይችላል፡፡ እኛን የሚገዛን ግን የአንድ ሙዝየም፣ የአንድ ተቋም ሐሳብ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም  ዝም አላለም፡፡ ቅርሶቼ ይመለሱልኝ፤ የሚል የይገባኛል ጥያቄ ለእንግሊዝ መንግሥት፣ በመንግሥት ደረጃ በወቅቱ በነበሩት ፕሬዝዳንት ፊርማ እ.አ.አ በ2007 አቅርቧል፡፡ እርሱን ገፍተን የምንቀጥልበት ነው የሚኾነው፡፡”

ሚኒስትሯ በመግለጫቸው፥ ንብረትነታቸው የኢትዮጵያ የኾኑ ከዐሥር በላይ ታቦታት፣ ከአምስት መቶ በላይ የብራና መጻሕፍት እንዲሁም ሌሎች ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች፣ “በእንግሊዛውያን ተወስደው በሙዚየሞች እና ግለሰቦች እጅ ተይዘው ይገኛሉ፤” ብለዋል።


በሙዝየሙ ለእይታ (Maqdala exhibition) መቅረባቸውም፥ የኢትዮጵያን ባህል፣ ታሪክና ወግ ለዓለም ከማስዋወቁ ባለፈ ጎብኚዎቹ፤ “ለእይታ የቀረቡት ቅርሶች የኢትዮጵያ ስለመኾናቸው ማረጋገጫ እንዲያገኙ ዕድል ይፈጥራል፤” ብለዋል።

ቅርሶች ከተወሰዱበት መቅደላ አካባቢ እስከ ቋራ ድረስ ያለውን ስፍራ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በጎንደር ዩኒቨርስቲ እና በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በኩል ጥናቶች እየተደረጉ እንደሚገኙም ሚኒስትሯ አክለው ጠቁመዋል።

የዐፄ ቴዎድሮስ 200ኛ ዓመት የልደት እና 150ኛ ዓመት የሙት ዓመት በዓል አከባበር ከሚያዝያ 2 እስከ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር እንደሚዘከርም አስታውቀዋል።

ስለጉዳዩ በመጀመሪያና በዋናነት የዘገቡት የእንግሊዝ ብዙኃን መገናኛዎች እንደኾኑ መመልከታቸውን ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተናገሩት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ በበኩላቸው፣ እይታውን የእንግሊዝ እንደኾኑ አድርጎ ግምት መውሰዱ መልካም ቢኾንም፣ ከእኛ እይታ አንጻር የማንቀበላቸው አቀራረቦች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ የቅርስ አጠባበቅ ዐዋጅ፣ በሕገ ወጥ መልኩ ከአገር የወጡ ቅርሶችን ከማስመለስ በመለስ የትኛውም ዐይነት ድርድር የማድረግ የሕግ ሰውነት ለማንኛውም አካል እንደማይሰጥ አስረድተዋል፡፡

ከባለቤቱ የተዘረፈ ቅርስ ለባለቤቱ ነው መመለስ ያለበት፡፡ ከዘራፊዎች ለመዋስ፣ አይደለም መስማማት ልንደራደር አንችልም፡፡ ዘገባው የዚያ ዐይነት ፍንጭ ባይኖረውም በእነርሱ እይታ የሙከራ ጉዳይ ሊኾን ይችላል፡፡ እኔም ኾንኩ በዚህ ጉዳይ ላይ የተሰለፍን አካላት በጣም አዝነን ነው ያነበብነው፡፡ አንደኛ በኢትዮጵያ ሕግ፣ የሕግ መሠረት የለውም፡፡ የኢትዮጵያ መገለጫ የኾኑትን ቅርሶች ከማስመለስ በመለስ ያለ ማንኛውንም ነገር ማድረግ አይቻልም፡፡

ቅርሶቹ በትክክለኛ ቦታቸው ላይ አለመኾናቸው አሳዛኝ ነው፡፡ ሊመለሱ የሚችሉባቸውን ቀዳዳዎች ኹሉ ፈልገን፣ የፈጀውን ያህል ጊዜ ፈጅቶ ትውልዶች ይመልሷቸዋል እንጅ መዋስን በፍጹም አናስበውም፡፡ ሕጋዊም አይደለም፤ ታስቦም የማይታወቅ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱም መዋስ ማለት በግማሽ መንገድ ሕጋዊ ሰውነት እየሰጠን ነው ማለት ነው፡፡ ከዘረፈን ጋር ልንደራደር የምንችልበት ዕድል ጠባብ ነው፡፡

በኤግዚቢሽን መልኩ ወጥቷል፤ የሚባል ነገር አለ፡፡ እኛ የትኛው ቅርሳችን የት ነው ያለው የሚለውን ነገር እናውቃለን፡፡ነገር ግን ከየተቀመጠበት ግምጃ ቤት በምን ደረጃ እንዳሉ ለማወቅ፣ ሞያውና የሥራው ተልእኮ ያልኾነው ሰው ጭምር የሚያይበት ዕድል መገኘቱ፣ ኢትዮጵያውያንና በቅርሶች ላይ ቀናዒና አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች የእኛ ደጋፊ አካላት እንዲኾኑ ዕድል ስለሚፈጥር ኢግዚቢሽን መደረጉን ብዙም አንቃወመውም፡፡ የተዘረፉ ቅርሶቻችን እንደኾኑ ግን በጣም ሊሠመርበት ይገባል፡፡ ስለዚህ ማስመለሱ ላይ አተኩረን ነው መሔድ የሚገባን፡፡

ለዘገባው ምላሽ መስጠትን በተመለከተ፣ የሙዝየሙ ዳይሬክተር የሰጡት አስተያየት ነው፡፡ እኛ የምንወክለው መንግሥትን ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ሙዝየም ለሰጠው አስተያየት በመንግሥት ደረጃ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ወይ የሚለው የራሱ ቢሮክራሲ ስላለው ያን ተከትለን የምናየው ነው የሚኾነው፡፡

afromet_press_conference

ኾኖም በኢትዮጵያ ሕግና በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ፕሮቶኮሎች አቋማችን ግልጽ ነው፡፡ ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ የተቋቋመ የመቅደላ ቅርሶች አስመላሽ ኮሚቴ/AFROMET/ አለ፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ሊነጋገር የሚችለው ከእንግሊዝ መንግሥት ጋራ እንጅ በተናጠል ከሙዝየሞች ጋራ አይደለም፡፡ በተናጠል ከወጡ ሪፖርቶች ጋራ እሰጥ አገባ ውስጥ መግባትም አያስፈልግም፡፡ ሕጉን ተከትለን ሔደን ውጤት ማምጣት ነው ያለብን፡፡ ይኼ የአጭር ጊዜ ፕሮጀክት አይደለም፤ ትውልዶች እየተቀባበሉት 150 ኾኖታል፤ የፈጀውን ያህል ጊዜ ፈጅቶ ወደ ቦታቸው በማስመለስ ላይ ብቻ ነው ትኩረታችንን የምናደርገው፡፡

የእንግሊዝ እና የኢትዮጵያ ጦርነት፣ በ1868 ዓ.ም. መቅደላ ላይ መካሔዱ ይታወሳል።

Share this post

One thought on “ታቦታትን ጨምሮ ከመቅደላ የተዘረፉ ቅርሶች፣ “በውሰት ሊመጡ ነው፤” መባሉን መንግሥት አላወቅም አለ፤ “ከማስመለስ በመለስ መዋስን በፍጹም አናስበውም”

 1. Studies indicate that the cost of historical items looted from Mekidela were too much.The items registered by the British Musium immidiate after the expedition were over 3.5 billion pound Sterling.This cost was in 1868 and does not include those taken by each member of individual army members,sold on the way to London,transported to India & other countries.More and above,they destroyed and burned whatever they considered was historical.The genocide undertaken by British army is not registered in history.They used chemical and biological amunitions in the expeditions. In my opinion,what British did against Ethiopia may need further study.

  Reply

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.