ቴዲ አፍሮ 80 ሺህ ህዝብን በሚያስተናግደው የባህር ዳር ስታዲየም ኮንሰርቱን እንዲያቀርብ ፍቃድ ተሰጠው

Source: http://amharic.abbaymedia.info/archives/41281

አባይ ሚዲያ ዜና 

በአለም አቀፍ ደረጃ ስሙ የገነነውና ኢትዮጵያዊ ፖፕ ኮከብ ወይም ስታር ተብሎ የተሰየመው ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ በባህር ዳር ኮንሰርት ለማቅረብ ፍቃድ እንዳገኘ ተዘገበ።

የተለያዩ ግዙፍ የአለም አቀፍ የዜና አውታሮች ኢትዮጵያ በሚል ርእስ ባሳተመው አልበሙ ስሙ ስለ ናኘው ቴዲ አፍሮ  ከፍተኛ የዜና ሽፋን በመስጠት ሪፖርት ማቅረባቸው ይታወሳል።

አንድነትን፣ ፍቅርን፣ ሰላምን፣ ታሪክን እንዲሁም ኢትዮጵያዊነትን መልእክታዊ በሆኑ ግጥሞቹ፣ ጥኡም በሆነ ዜማዎቹ እና በአስደናቂ ድምጹ እያንቆረቆረ ለህዝብ በማቅረብ ዝናን ያተረፈው ቴዲ አፍሮ በኢትዮጵያውያን አድናቆት ቢጎርፍለትም በአገዛዙ ጥርስ ውስጥ ገብቶ ጥላቻን እያስተናገደ እንደሆነ የአለም አቀፍ የዜና አውታሮች በይፋ ለአለም አሳውቀዋል።

በጥር 12 ቀን 2010ዓም በአማራ ክልላዊ መንግስት መቀመጫ በሆነችው በባህር ዳር ከተማ ኮንስርቱን ለህዝብ እንዲያቀርብ ፍቃድ ያገኘው ቴዲ አፍሮ ከአቦጊዳ ባንድ ጋር ዝግጅቱን መጀመሩ ተሰምቷል።

የሙዚቃ ስራዎቹን በቱሪስት መስህብ በሆነችው በባህር ዳር ከተማ በጥር 12 ቀን 2010ዓም እንዲያቀርብ በተደረገው ጥረት የአማራ ክልላዊ መንግስት፣ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ጽህፈት ቤት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛ ትብብር ማድረጋቸው ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያ በሚል ርእስ ያሳተመው አልበም በአለም አቀፍ የፖፕ ቢልቦርድ ደረጃ ላይ ያስቀመጠው ቢሆንም አልበሙን ለማስመረቅ በአዲስ አበባ ሊያቀርብ የነበረውን ኮንስርት አገዛዙ መከልከሉ አይዘነጋም። ከዚህ በተጨማሪ የተወሰኑ ሙዚቃዎቹ በመንግስት ድጋፍ በሚተዳደሩት የሬዲዮና የቴሌቭዥን ጣቢያዎች እንዳይደመጡ መታገዱ ግዙፍ የአለም የዜና ተቋማት መዘገባቸው ይታወሳል። 

የአማራና የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ከቅርብ አመታት ጀምሮ እርስ በእርስ በመናበብ አገዛዙን በማስጨነቅ የተለያዩ ለውጦችን እንዲደረግ እያስገደዱ መሆናቸው እየተስተዋለ ይገኛል። አገዛዙ በቴዲ አፍሮ የሙዚቃ ስራዎች በንዴት እንደሚብሰለሰል እየታወቀ  በባህር ዳር ከተማ ለመላ ኢትዮጵያውያን የሙዚቃ ኮንሰርቱን እንዲያቀርብም የአማራ ክልላዊ መንግስት ፍቃድ መስጠቱ ከአገዛዙ ጋር ያለውን የሻከረ ግንኙነት እንደሚያሳይ ተነግሯል።

ጣና ኬኛ የሚል መፈክር በማንገብ ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጡ ከ 200 በላይ ወጣቶች ወደ ባህር ዳር በማቅናት ከባህር ዳር ህዝብ ጋር በመተባበር በጣና ሃይቅ የበቀለውን የእምቦጭ አረምን የመንቀል ዘመቻ ማድረጋቸው ይታወሳል። በፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ የሚመራ ቡድን ወደ አማራ ክልል በማቅናት ታሪካዊ እና የዘመናዊነት አስተሳሰብ መገለጫ የተባለለትን የውይይት መድረክ ማድረጋቸው የማይዘነጋ ቢሆንም ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለ ማርያም ደሳለኝ መርህን ያልተከተለ ግንኙነት በማለት በሁለቱ ብሄረሰቦች ያለውን የመደጋገፍና የመናበብ ሂደትን በይፋ አጣጥለውታል።

በጥር 12 ቀን 2010ዓም ባሕር ዳር ከተማ ከ80 ሺሕ ሕዝብ በላይ ማስተናገድ በሚችለው በታላቁ ብሄራዊ ስታዲየም  ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከተለያዩ የአገሪቷ ክፍል ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Share this post

Post Comment