ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት ስንት ወልድያ ያስፈልገናል?

Source: https://kalitipost.com/%E1%89%BD%E1%8C%8D%E1%88%A9%E1%8A%95-%E1%8A%A8%E1%88%98%E1%88%A0%E1%88%A8%E1%89%B1-%E1%88%88%E1%88%98%E1%8D%8D%E1%89%B3%E1%89%B5-%E1%88%B5%E1%8A%95%E1%89%B5-%E1%8B%88%E1%88%8D%E1%8B%B5%E1%8B%AB/

የጸጥታ ኃይሎች በወልድያ ነዋሪዎች ላይ የፈጸሙት ግድያ በምንም ዓይነቱ መመዘኛ ከውግዘት የሚያመልጥ አይደለም፡፡ በአንድ በኩል ‹ጸረ መንግሥት ዝማሬ ያሰሙ ነበር›፣ በሌላ በኩል ደግሞ ‹ድንጋይ ይወረውሩ ነበር› የሚሉት ምክንያቶች የጸጥታ ኃይሎች በሕዝብ ላይ ጥይት እንዲተኩሱ የሚያበቁ ሕጋዊና ሞራላዊ ምክንያቶች አይደሉም፡፡ ማንኛውም ጸጥታን የማስከበር ሥራ መከናወን ያለበት ሰላምን በሚያሰፍን፣ የሰዎችን ሕይወትና ንብረት በሚጠብቅና ተመጣጣኝ የሆነ ኃይልን ለመጠቀም በሚፈቅድ ሁኔታ መሆን አለበት፡፡

በኃይል የሚፈታ ችግር እንደሌለ መንግሥት ራሱ ከማናችንም በላይ የሚያውቀው ነገር ነው፡፡ የዛሬውን መንግሥት የመሠረተው ኢሕአዴግ ወደ በረሓ እንዲገባ ያደረገው ደርግ ችግሮችን ሁሉ በውይይት ሳይሆን በኃይልና በኃይል ብቻ ለመፍታት በመፈለጉ መሆኑን በየግንቦት ሃያ በዓሉ ስንሰማው ኖረናል፡፡ ለሰው የሚጠላውን ኃጢአት ራሱ ከመሥራት በላይ ውድቀት የለም፡፡ በዓሉ የአንድ ቀን በዓል ነው፡፡ ቢታገሡት ያልፍ ነበር፡፡ ሌላ ችግር ይከሰታል ተብሎ ከተጠረጠረና መረጃ ከተሰበሰበ እንኳን አያሌ የችግር መፍቻ አማራጮች ነበሩ፡፡ ‹የጸጥታ ችግርም› ‹የጸጥታ ኃይሎች›ም እኛ ሀገር ብቻ አይደለም ያሉት፡፡ ባለ ሥልጣኖቻችንም ለልምድ ልውውጥ በየሀገሩ ሲሄዱ ነው የሚኖሩት፡፡ ምነው ታድያ የተሻለ አማራጭ መማር አቃታቸው?
በዓሉ ሕጻናት፣ አረጋውያን፣ ዐቅመ ደካሞች፣ ነፍሰ ጡሮች፣ አካል ጉዳተኞች ሳይቀሩ የሚታደሙበት በዓል ነው፡፡ እንዴት ነው ወደነዚህ ሁሉ የሚተኮሰው? እንዴትስ ነው ‹ችግር ፈጠሩ› የተባሉትን አካላት ከሌሎች ለመለየት የሚቻለው? ጥይቱስ እንዴት ነው ከ9 ዓመት ሕጻን የሚጀምረው? እንዲህ ባሉ ዓመታዊ በዓላት ቀን የሚፈጠር ግፍ ከልጅ ልጅ ለመታወስና የበቀልን ስሜት ለመቀስቀስ ቀላል መሆኑን እንዴት ለማሰብ ከበደን? ከዚህ በኋላ ወልድያ ላይ የቃና ዘገሊላ በዓል ቃና ዘገሊላ ብቻ ሆኖ የሚታሰብ ይመስለናን? ገና ይዘፈንበታል፣ ይፎከርበታል፣ ይተረትበታል፣ ሙሾ ይወረድበታል፣ ውሎ ለቅሶ ይዋልበታል፡፡ ለመሆኑስ በየልቅሶ ቤቱ የተቀመጠው ሕዝብ ስለ ልማትና ዴሞክራሲ፣ ስለ መንገድና ትምህርት ቤት፣ ስለ ባቡርና አውሮፕላን ማረፊያ የሚጨዋወት ይመስለናል? ገና ተዝካር፣ መት ዓመት፣ ሰባት ዓመት፣ ሃያ አንድ ዓመት የሙታን በዓል አለ፡፡ በነዚህ ዘመናት ሁሉ ምን የሚባል ይመስላችኋል?

እንዲህ ላሉ ችግሮችስ ጥይት መፍትሔ አለመሆኑን ባለፉት ሁለት ዓመታት ሀገሪቱ ያለፈችበት ሁኔታ ብቻ እንዴት አያስተምረንም? ይልቅ ለምን የችግሩን ምንጭ ለማድረቅ አንሠራም? ‹የሚያስለቅስ ነገር ነግሮ አታልቅስ ይለኛል› የሚል የትግርኛ አባባል አለ፡፡ ሕዝቡ ለምን ባሰው? ወጣቶቹ ለምን ተቃወሙ? የዚህ ሁሉ ችግር ምንጩስ ምንድን ነው? ብሎ መሥራት አይሻልም፡፡ ለምን ሕዝብን ከሕዝብ ወገንን ከወገን የሚያጋጭና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ቂም እንዲቋጠር ይፈለጋል? ለምንስ የዘርና የጎሳ መልክ እንዲይዝ ይፈለጋል? ወንጀለኞችስ ለምንድን ነው በጎሳ ካባ ውስጥ እንዲደበቁ ሁኔታዎች የሚመቻቹት? ከመሬት መንቀጥቀጡ(shock) በላይ ድኅረ መንቀጥቀጡ(aftershock) ውጤቱ የከፋ መሆኑን አናውቅምን? ችግሩንስ ከመሠረቱ ለመፍታት ስንት ወልድያ ያስፈልገናል?

አሁንም ባለ ሥልጣኖቻችን ቆም ብለው የማሰቢያ ጊዜያቸው ባያሳጥሩት መልካም ነው፡፡ ችግርን ከመፍታት ይልቅ ‹የከተማዋ ሁኔታ እየተረጋጋ ነው› ዓይነት ዜና ራስን ማታለያ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ስብሰባ ደምን አድርቆ አያውቅም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዝምታ በመቀበል፣ ፋታም በፍጻሜነት ሊተረጎም አይችልም፡፡ በበላይ ዘለቀ ምክንያት በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ወታደሮች ግፍ የተፈጸመበት የጎጃም ገበሬ ምነው ዝም አለ? ሲባል
ዝም አልክ ይለኛል ዝምታ የታለ
ውስጤ እየጮኸ ነው እየተቃጠለ
ብሎ የገጠመው የልቅሶ ግጥም ሁኔታውን በሚገባ የሚገልጠው ይመስለኛል፡፡ አሁንም ሰይፍ ወደ ሰገባው፣ ቃታም ወደ ቦታው፣ ይግባ፡፡ ወንጀለኞችም ወደ ፍርድ፣ ችግሮችም ወደ መሠረታዊ መፍትሔ ይምጡ፡፡ መንግስትም ወደ ልቡናው ይመለስ፡፡

(ዳንኤል ክብረት)

Share this post

One thought on “ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት ስንት ወልድያ ያስፈልገናል?

 1. የሁለት ታዛዦች ወግ….
  *የአማሮች ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንድአርጋቸው በወሎ ከፍለ ሀገር ወልዲያ ከተማ “የተፈፀመው ጥፋት ነው” “ከሕዝብ ጋር ተወያይተናል፣ ችግሮችን በየደረጃው እንፈታለን” የጭፍጨፋው ምክንያት ባሻገር ሕዝብ በርካታ ችግር እንዳለበት፣ እሱም በየደረጃው መፈታት እንደሚገባው ገልፀዋል።”

  * የሰሜን ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አማረ ጎሹ “ያጠፋነው አጥፊዎችን ነው፣ አሁንም እናጠፋቸዋለን” “ጦር እየተጨመረልን ነው፣ አሁንም እንገድላቸዋለን” አይነት መግለጫ ይሰጣል። የችግሩ ምንጭ የፖለቲካ አላማ ያላቸው አካላት ናቸው። መፍትሄው “መደምሰስ” ነው።
  *******************
  “ወልዲያ ውስጥ የተፈጠረው የከተማዪቱን ማኅበራዊ ስብጥርና ግንኙነቶች የማያንፀባርቅ አሣዛኝ ሁኔታ መሆኑን በሰሞኑ ግርግር የንግድ ተቋማቸውና መኖሪያ ቤታቸው ሙሉ በሙሉ እንደወደሙባቸው በጓደኛቸው ልጅ ሞት ያዘኑት “ከእኔ ንብረት የሰው ሕይወት ይበለጣል” የኃይላይ ሕንፃ ባለቤት አቶ ኃይላይ ንጉሴ።
  __________________________________________
  ”ተገዳይ ወንድሜ ገብረመስቀል ጌታቸው እንዳይተርፍ ነው ፭ ጊዜ በጥይት የመቱት” ሲል በምሬት ይናገራል። ኪዳኔ ዕለቱን ሲያስታውስ ”ግርግር እንደተነሳ ደጋግሜ ስልክ ደወልኩለት አያነሳም። ብጠብቀውም መልሶ አይደውልም። በጣም ስለተጨነኩኝ ወደ ሆስፒታል ልፈልገው ሄድኩኝ፡ አንገቱ ላይ፣ ደረቱ ላይ፣ ሆዱ ላይ እና ብልቱ ላይ አምስት ጊዜ በጥይት የተመታ እና በደም የተሸፈነውን የወንድሜን አስከሬን ሆስፒታል ውስጥ አገኘሁ”ኪዳኔ ጌታቸው

  >› “ተመጣጣኝ እርምጃ!” የሚሉ ጨዋታ በህወሓት/ኢህአዴግ ተጀምሮ ነበር። ያውም ሱሪ ባስታጠቀው አባቱ ሻዕቢያ ላይ ግን የድሃ ልጅ መሐል ለጦር ማግደው እነሱ ኑሮአቸውን ዙሪያውን በመፎከርና በመፎካከር እንዲሁም በስውር ልዩ ጥቅማጥቅም ይደጋገፋሉ።” ብልጥ ልጅ እየበላ ያለቅሳል” ህወሓት ኤሌትሪክ ለሱዳን ሸጠች ሱዳን ለሻቢያ አቀበለች ያው ግሎብላይዜሽን ዓለም አንድ መንደር ሆነች ማለት ይህ አደለምን። ሁለቱም የአዞ እንባ ያነባሉ.. አንዱ በሌላው ላይ እጅ ይቀስራሉ፡ የአካባቢው ቀጠና አተራማሽነታቸውን ቀጥለዋል!
  * ህወሓት/ኢህአዴግ ተሰብስበው ለጦመሩም ይሁን፡ ለዘመሩ፡ ወይም ድማፃቸውን ላሰሙ ‘ተመጣጣኝ እርምጃው’ ግንባርና ደረቱን በአልሞ ተኳሽ ማስበርቀስ ነው።ድሮስ የተናቀ ሠፈር..!የመጀመሪያ ሞታችን ወደብ አልባ እንደከብት ስንከለል።
  *የአማራና ኦሮሞ ወጣት ወንድምና እህቱ ከጎኑ እንደቅጠል ሲረግፍ የሚሰጠው ተመጣጣኝ እርምጃ …የካድሬና የክልል(ባንዳ) ተላላኪ ጣራ በድንጋይ ደበደቡ ነው። ቢያንስ ድሃ ተቀጠሮ የሚሰራበትን አቃጥሎ ዓመድ ከመታቀፍ፡ በሕገወጥ የሚዘዋወር የሙሰኛና ልዩ ተጠቃሚ ንብረትን ወርሰው ለድሃ አከፋፈሉ የሚለው እጅጉን ይመረጣል!።
  __ ከዚህ በኋላ ወልድያ ላይ የቃና ዘገሊላ በዓል ቃና ዘገሊላ ብቻ ሆኖ የሚታሰብ ይመስለናልን? ገና ይዘፈንበታል፣ ይፎከርበታል፣ ይተረትበታል፣ ሙሾ ይወረድበታል፣ ውሎ ለቅሶ ይዋልበታል፡፡ገና ተዝካር፣ሙት ዓመት፣ ሰባት ዓመት፣ ሃያ አንድ ዓመት የሙታን በዓል አለ፡፡ በነዚህ ዘመናት ሁሉ ምን የሚባል ይመስላችኋል?
  * አሁን ያለው በተናጠል እየለየህ በለው የህወሓት የመቀሌው ስብሰባ ውሳኔ በእየክልሉ ቦታና ግዜ እያመቻቹ ለሚደረግ የመንገድ ላይ ግድያ፡ ወጣቱ ያለማቋረጥ በአንድነት ቆሞ ያሰበና ያሳሰበውን፡ የገደለና ያስገደለውን፡ እየለየ ተንበርክኮ ማፅዳት ይጠበቅበታል። “እያንዳንዱና ሁሉም አካባቢውን ቢያፀዳ ከተማችን ንጹሕ ትሆን ነበር። ”እንደሚለው ሁሉ ” እያንዳንዱና ሁሉም በቀበሌው የተሰገሰገን ሌባ፡ አስመሳይ፡ አድርባይ፡ አውርቶ አደር፡ ባንዳ፡በእየቀኑ ቢያፀዳ የነጻነት ጎዳናው ቀና፡ ተከብሮና ታፍሮ ለመኖር ግዜው ብሩሕ ይሆን ነበር። አራት ነጥብ። እንበለ፲፪ ግዜ!

  Reply

Post Comment