አርበኞች ግንቦት ሰባትና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሀይል ንቅናቄ በከፍተኛ ሁኔታ በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸው ተገለጸ

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%8A%A0%E1%88%AD%E1%89%A0%E1%8A%9E%E1%89%BD-%E1%8C%8D%E1%8A%95%E1%89%A6%E1%89%B5-%E1%88%B0%E1%89%A3%E1%89%B5%E1%8A%93-%E1%8B%A8%E1%8A%A0%E1%88%9B%E1%88%AB-%E1%8B%B4%E1%88%9E%E1%8A%AD%E1%88%AB/

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 21/2010) አርበኞች ግንቦት ሰባትና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሀይል ንቅናቄ በአማራ ክልል ወጣቶችን በማደራጀትና በማሰልጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን አንድ የኮማንድ ፖስት ሰነድ አመለከተ።

ለኢሳት የደረሰውና በጎንደር የኮማንድ ፖስት የተዘጋጀው ሰነድ ላይ አርበኞች ግንቦት ሰባትና አዴሀን ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለማፍረስ እየተረባረቡ መሆናቸው ተገልጿል።

በጎንደር ከተማ በስድስቱ ክፍለከተሞችና በጎንደር ዩኒቨርስቲ በተዘጋጀው የኮማንድ ፖስቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መድረክ ላይ የቀረበው ሰነድ በጎንደር ከተማ በተደጋጋሚ የሚፈጸመው የቦምብ ጥቃት የቱሪስት ፍሰቱ እንዲቀንስና ባለሀብቶች ስጋት እንዲያድርባቸው ማድረጉ ተመልክቷል።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማስፈጸሚያ የኮማንድ ፖስት ዕቅድ በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ሰነድ ባለፉት አራት አመታት በአማራ ክልልና በመላ ሀገሪቱ በተነሱ የህዝብ ተቃውሞዎች ከሰው ህይወት መጥፋት ባሻገር ታላላቅ ኢኮኖሚያዊ አውታሮች እንደወደሙ ጠቅሷል።

በአጠቃላይም ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶች መፈጠራቸውን በዝርዝር አስቀምጧል።

ለሁለተኛ ጊዜ የተደነገገውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስፈጸም በዋናነት ህዝቡ ስለኮማንድ ፖስቱ ያለውን የተዛባ አመለካከት ማስተካከል አለብን ያለው ሰነዱ አፋኝና ህዝብን ለመጉዳት የተቋቋመ ተደርጎ ስለኮማንድ ፖስቱ በህበረተሰቡ ውስጥ የሰረጸውን አመለካከት ለመቅረፍ መስራት ይጠበቅብናል።

ከእነዚህም አንዱ የፖሊስ፣ የመከላከያና በሌሎች የጸጥታ ሃይሎችን ዩኒፎርም በመልበስ ግድያዎች እንደሚፈጸሙ ለህዝቡ የማሳመን የፕሮፖጋንዳ ስራ መሰራት እንዳለበት ተገለጿል።

የውጭና የውስጥ የጸረ ሰላም ሃይሎች ከምንጊዜውም በላይ ተቀናጅተው በህዝብ ይሁንታ የተመረጠውን ህገመንግስታዊ ስርዓት ለማፍረስ በመረባረብ ላይ ናቸው ሲል ያመለከተው ሰነዱ ከእነዚህ ሃይሎች ጀርባ ኤርትራና ግብጽ ይገኛሉ ብሏል።

እነዚህ ሃይሎች በተደራጀ ሁኔታ የከተማ ውስጥ ትግልና የሽምቅ ውጊያ በማድረግ በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ለማስወገድ ከምንጊዜውም በላይ ርብርብ እያደረጉ መሆናቸውን ሰነዱ አመልክቷል።

በተለይም አርበኞች ግንቦት ሰባትና የአማራ ዴሞክራሲያ ሃይሎች ንቅናቄ አዴሀን በአማራው ክልል ወጣቶችን በማደራጀት፣ በማሰልጥንና በማስታጠቅ መጠነ ሰፊ የማወክ ዘመቻ መክፈታቸውን ነው በሰነዱ ላይ የተገለጸው።

አርበኞች ግንቦት ሰባት ሀገር ውስጥ ጥቃት ለመፈጸም በአዲስ መልክ እየተደራጀ ነው ሲል የገለጸው ሰነዱ አዴሀንም በሰሜን ጎንደር፣ ጎጃምና ደቡብ ወሎ ሰፊ የወታደር ምልመላ በማካሄድ ለጥቃት እየተዘጋጀ ነው ሲል በዝርዝር አስፍሯል።

እነዚህ ሃይሎች ሀገር ውስጥ ከሚገኙ ቡድኖች ጋር በመሆን እየፈጠሩት ያለው የማደናገርና የማጥቃት ዘመቻ ህዝቡ ለመንግስት ያለው ዕምነት እንዲሸረሸር ከማድረጉም በላይ በመንግስት ላይ ተስፋ ቆርጦ የጥፋታቸው ተባባሪ እንዲሆን አድርገውታል ሲልም ያትታል።

በታላላቅ ፋብሪካዎችና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ ጥቃት በመፈጸም የባላሀብቶችን ተሳትፎ በመገደብ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተላቸውን በሰነዱ ተጠቅሷል።

ኢሳት እጅ በገባው በዚሁ የኮማንድ ፖስቱ የእቅድ ሰነድ ላይ በጎንደር ከተማ የተሽከርካሪዎች የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉንም ይገልጻል።

በዚህም መሰረት በጎንደር ሞተር ሳይክል ከ12 ሰዓት፣ ባጃጆች ደግሞ ከምሽቱ አራት ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ተመልክቷል።

 

 

 

 

 

The post አርበኞች ግንቦት ሰባትና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሀይል ንቅናቄ በከፍተኛ ሁኔታ በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸው ተገለጸ appeared first on ESAT Amharic.

Share this post

One thought on “አርበኞች ግንቦት ሰባትና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሀይል ንቅናቄ በከፍተኛ ሁኔታ በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸው ተገለጸ

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.