አርኪሜደስ፥ የቲም ጃዋር ቅጥፈትና፥ የዲሢ መንግሥት (ድንበሩ ደግነቱ)

Source: http://amharic.abbaymedia.info/archives/45991

አርኪሜደስ በ287 ዓመተ ዓለም ወደዚህች ዓለም የመጣ የክላሲካል ጥበበኞችን ያስናቀ ዐዋቂ ነበር። ሲራኩየስ በምትባል የሲሲሊ ደሤት ላይ የምትገኝ ከተማ ውስጥ ኖረ። ሂየሮን የተባለው ንጉሥ ዘውዱን እንዲሠራለት ለአንጥረኛው ከሰጠው ወርቅ፤ አንጥረኛው ሰርቆ፥ በምትኩ ብር በርዞበታል ብሎ ስለጠረጠረ፤ እውነታውን እንዲያጣራ አርኪሜደስን ጠየቀው። አርኪሜደስ ሲበላም፥ ሲጠጣ፥ ሲነቃም ሲተኛ ይህን እውነት ፍለጋ አዕምሮውን ጠመደው። የመታጠቢያ ገንዳውን ሞልቶ ሊጠመቅ ሰውነቱን ወደገንዳው በከተተ ጊዜ፤ ከገንዳው የሚፈሰው ውሀ በእሱ ሰውነት ልክ መሆኑን አስተዋለ። ወርቅ ከብር ስለሚከብድ ብር የተቀየጠበት ዘውድ የሚያፈናቅለው (displaced) ውሀ መጠን፤ ሙሉ በሙሉ ወርቅ ብቻ ከሆነው ዘውድ የበለጠ ነው ብሎ ራሱን አሳመነ። መልሱን እንዳገኘ ሲገነዘብ ከገንዳው ዘሎ ወጥቶ “ዩሬካ! ዩሬካ!” እያለ (አገኘሁት ማለት ነው) እየቀወጠው ወደቤቱ አቀና። ገመናውን መሽፈኛ እራፊ ጨርቅ በላዩ አልነበረምና፤ ተፈጥሮ ያንጠለጠለችለትን ክራባት እያወዛወዘ ሲጮህ፤ የሰው ሁሉ አይን እሱ ላይ እንደነበር የሚያስተውል ልቡና አልነበረውም። ይህ የአርኪሜደስ ግኝት (physical law of buoyancy) ተብሎ ይታወቃል። ዛሬም ድረስ በተለይ በታዳጊ አገሮች ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል።

አርኪሜደስ እውነትን ፍለጋ የተጋውን ያህል ጀዋርና የጀዋር ቲም ሰሞኑን ለመፈናቀሉና ለመሞቱ እራሳቸው ምክንያት በሆኑት ማኅበረሰብ ላይ የሚያፈሱት የማፈናቀል (displacement) የሀሰት ታሪክ ቀልባችንን ሳበንና ነው ለዘሬው ወጋችን የጋበዘን። መቶ ሚሊዮን ሕዝብ አምጦ የወለዳቸው እሳት የላሱ የታሪክ ተመራማሪዎች ያላት አገር፤ እዚህ ግቡ የማይባሉ ፈላዎች አዋቂ ሆነው ሀሰትን ሲሰብኩና ንግሥናቸውን ሲያመቻቹ፤ የለም ታሪክ ይስተካከል የሚል ጀግና መጥፋቱ ያሳዝናል። ግፋ ቢል ትሰደቡ ይሆናል። በመሰደብ ተሳዳቢው እንጂ ተሰዳቢው አይቆሽሽም። ለአገራቸው አባቶቻችን ሞትን እንኩዋን አልፈሩም። ዝም በማለት ከአገር አፍራሾች ጋር አንተባበር። እያንዳዳችን ይህ የመጣ ደግ ዘመን አንዴ ካመለጠ ተመልሶ እንደማይገኝ አውቀን፤ ለእውነት መቆሚያ ጊዜ ነው ወቅቱ። መክፈል ያለብን ብዙ መስዋዕትነት የለም። አንድ ሆነን ለክፉ አለመተባበር፥ ውሸትን መጠየፍና እውነትን ማስተጋባት ይጠበቅብናል።

  1. “የጋሞ ሕዝብ ትናንትም የተፈናቀሉት በነሱው ነበር።” ጀዋር መሀመድ

በቡራዩ ነዋሪ በሆኑት ነዋሪዎች መፈናቀል፥ መዘረፍ፥ መሳደድ፥ መገደልና መደፈርን አስመልክቶ ኦቦ ጀዋር በሰጠው ቃለ መጠይቅ በስም ያልጠቀሳቸው ወገኖች ባደራጁዋቸው ወሮበሎች ሆን ተብሎ የተፈፀመ ድርጊት መሆኑን ከገለፀ በሁዋላ፤ በቡራዩ አካባቢ የተገኙበት ዋና ምክንያት ከተፈጠሩበት ቦታ፤ ከአንድ ክፍለ ዘመን በፊት  ያፈናቀሉዋቸው ዛሬም ለመፈናቀላቸው ምክንያት እንደሆኑ ይከሳል። ጀዋር እንደዚህ ጊዜ የተምታታበት ወቅት ያለ አይመስለኝም። መለስ ተመሳሳይ ውሸቶችን በተሻለ ጥበብ ያስተላልፍ ነበር። የጋሞ ተወላጆች ቡራዩና አካባቢው መገኘታቸው ትክክል እንዳልሆነ በተናገረበት አፉ፤ በመፈናቀላቸው ሌላውን ይከሳል። ከአንድ ክፍለ ዘመን በፊት ከተፈጠሩበት ቦታ አሁን የሚከሰውን የአንድነት ኃይሉ ስላፈናቀላቸው የአዞ እንባ ለማፍሠስ ይሞክራል። ይህ ሁሉ ውሸት ለምን አስፈለገ። እንደኔ ሀሳብ ጃዋር ኦሮሚያ የሚባለውን ክፍል ከአንድነት ኃይሉ በቶሎ አፅድቶ ዘውድ ለመጫን ቸኩሎዋል። የሚኒሊክ አገርን አንድ የማድረግ ዘመቻ ማፈናቀል (displacement) አልነበረውም። ሰዎች ይሄ አገር አገራችሁ አይደለምና ለቃችሁ ውጡ አልተባሉም። የተባረሩ ፍልስጥኤሞች በእስራኤሎች እንጂ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያውያን ጥፉ ከዚህ አልተባሉም። ማባረርም አስፈላጊ አልነበረም። በዛን ጊዜ የመላዋ ኢትዮጵያ ሕዝብ ከአሥር ሚሊዮኖች ብዙም ያልዘለለ ነበርና ሰው ይፈለግ ነበር እንጂ ማባረር አልተደረገም። በደል አልተሠራም ነበር ማለቴ አይደለም። አሁን እነጀዋር እንደሚያስደርጉት ጥፉ ከዚህ ማለት አልነበረም። ኢትዮጵያዊ ናችሁና በአንድ አገር እንታቀፍ ነበር እንጂ ጥያቄው ውጡ ከዚህ አልነበረም። አይደለም ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን የሚሉ የአንድነት ኃይሎች፥ ቅኝ ገዢው ጣሊያን እንኩዋን በገዛበት ዘመን የኢትዮጵያውያንን የግል ይዞታ ሲፈልገው፤ በምትኩ ቤትና ቦታ ለተፈናቀሉት ይሰጥ ነበር። በሰላም ተገዙ እንጅ “ድራሻችሁ ይጥፋ!” አላለም። አገራችሁ ስላልሆነ ከዚህ ውጡ ማለት ዕድሜ ለዘረኞች፥ ፋሺስት እንኩዋን ያልሞከረው ጊዜ አመጣሽ ክስተት ነው። አሁን በነበረበት ቦታ የተፈጠረ ሕዝብ በዓለምም አይገኝም። አዲስአበባ የኦሮሞ ነች ከማለታችን በፊት የኦሮሞ የሆነችው ከመቼ ጀምሮ ነው? የታሪክ ስሌት የሚጀምረው ከመቼ ነው? ብለን መወሰን አለብን።

ምንሊክ የሸዋው ንጉሥ ልጅ ነበሩ። ከጎጃም፥ ከወሎ፥ ከጎንደር አማርኛ ተናጋሪ ማኅበረሰብ ጋር ከወዳጅ ይልቅ ተቀናቃኝ ስለነበሩ ወታደሮችን የመለመሉት ከሸዋ ነበር። ስለዚህም አገርን አንድ በማድረግ ዘመቻው የተሳተፉት ወታደሮች ኦሮምኛ ተናጋሪና አማርኛ ተናጋሪው መሳ ለመሳ ነበር። አሁን እንደሚሰበከው አማሮች በኦሮሞዎችና በሌላ ቁዋንቁዋ ተናጋሪዎች ላይ አልዘመቱም። አፈሩን ይቅለለውና አሠፋ ጫቦ ግዙፍ ስብዕና የነበረው የጋሞ ተወላጅ ኩሩ ኢትዮጵያዊ ነበር። አሠፋ ስል ዐዕምሮ ያለው፥ ያየውን የሚያስተውል፥ እውነትን ከመናገር መቆጠብ የማይችል፥ ለኃይለ ሥላሴ ብዙም ፍቅር የሌለው ሰው ነበር። ሰሚ ቢኖር ጮክ ብሎ ደጋግሞ ተናግሮዋል። ደጋግሞ ፅፎታልም። የሰዎችን ስም እየጠራ በጋሞ አካባቢ ነፍጠኞች በሙሉ ኦሮሞዎች እንደነበሩ ተናግሮዋል።  የሚሻለን አብሮ መኖር እንደነበር አጥብቆ ሰብኮዋል። ነፍጠኛ ኦሮሞዎቹም ቢሆኑ ጋሞዎችን አላፈናቀሉም። ተቃቅፈው ነው አብረው የኖሩት።

እንደ ጋሞ ተወላጅ በራሱ በጣም የሚኮራ የለም። የሌላው ብሔር ተወላጆች በማንነታችን ላይ ተፅእኖ ተደረገብን ሲሉ ጋሞዎች ማንነታቸውን አላስደፈሩም ነበር። ጋሞዎች በ1983 ቀኙ የኢትዮጵያዊነት ጠላቶች በነበረበት ወቅት እንኩዋን ምርጫቸው ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊነት እንደነበር በድፍረት ይናገሩ ነበር። ልጆቻቸው የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ልሣን በሆነው አማርኛ ቁዋንቁዋ እንዲማሩላቸው ይወተውቱ ነበር። ማንም ጋሞ ጋሞ መሆኑን ምንም ሳይደብቅና ሳያፍር ከኢትዮጵያዊነቱ ጋርም ሳይጋጭበት ኖሮዋል። አሠፋ ጫቦ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት እንዳይበተን መሙዋገቱ ወንጀል ሆኖበት ነው የተሳደደው። ይህ ማንነቱና ኢትዮጵያዊነቱ ሰምና ወርቅ መሆን ያበሸቃቸው ፀረ ኢትዮጵያውያን ቀን ጠብቀው አጠቁት። ኢትዮጵያዊነት ሲመቱት የሚጠብቅ ሊበጥሱት ሲጎትቱት የሚለጠጥ መሆኑ ጠፍቶዋቸዋል። ጋሞዎች ወደ መሃል ወይም ወደ ሰሜን የሄዱት ኢትዮጵያ አገራቸው ስለሆነች ብቻ ነው። እንዳይበርደን ሸምነው ሊያለብሱን ለኛው ብለው ነው። በሚጠልፉት ጥለት ሊያስውቡን ከጅለው ነው። እሁድ ቤተክርስቲያን የምንስምበትን ነጠላ ሊሰጡን ነበር አቆራርጠው ያለንበት ድረስ የመጡት። እድሜ ለነጃዋር የማፈናቀል ንድፈ ሃሳብ ባጎረሱ ተነከሱ። ለወደፊቱም በሰላም እንዳይኖሩ የሀሰት ወሬ እየፈበረኩ ያሰራጩባቸዋል።

  1. የዲሲ መንግሥት

ከላይ የተለጠፈው ፎቶ የዲሢ መንግሥት ሕዝብ ሊመለከተው በሚችል ሥፍራዎች ላይ የሰቀለው ማስታወቂያ ነው። የዲሢ ከተማ የአንድ ከተማ መንግሥት ነው። ዲሢ ተራራ፥ ሜዳ፥ ደን፥ እርሻ፥ ከጠበባት ወደፊት የምትስፋፋበት ትርፍ ቦታ የላትም። ጢም ብላ እንደ አርኪሜደስ ገንዳ ሞልታለች። መሬትዋ በሙሉ ወይ ህንፃ ወይ መንገድ ነው። በሰሜን የሜሪላንድ መንግሥት፥ በደቡብ ደግሞ ቨርጂኒያ ጭምቅ ያደረጉዋት ሚጢጢ ከተማ ብቻ የሆነች መንግሥት ነች። ሌላ ኅብረተሰብ የምትቀበልበት ምንም ቦታ የለም። በነጃዋር አስተሳሰብ ከሌላው የዓለም ክፍል አንድ ሰው ዲሢ ብትቀበል በዛው ልክ ከነባር ነዋሪዎች መፈናቀል አለባቸው። ዲሢዎች ለነዋሪዎቻቸው ቤት ለመሥራት የሚመነጥሩት ጫካ የላቸውም። የድሮዎቹን ጎጆዎች ነው ወደላይ የሚቀጥሉባቸው። ታዲያ ታሪክ ብርቃቸው ነው። ጎጆዎቹን የፊት ገፃቸውን ላለማጥፋት ከሥር ሰቅስቀው ቅስት ካስገቡላቸው በሁዋላ ለአዲሱ ህንፃ መሠረት ከሥሩ ይቆፍራሉ። ሲያሳዝኑ! ይሄ ሁሉ እኮ ለሁለት መቶ ዓመት ታሪክ ነው። ጃዋርና መለስ በሀሰት የሶስት ሺ ዘመናት ታሪክን እያጨዱ ገደል ሲከቱ ቢያዩ ምን ይሉ?

ዲሢ ያለማቁዋረጥ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች አዳዲስ ሰዎች እየመጡ ይኖሩባታል። የእንጀራ ነገር ሆኖ ጥለዋት የሚሄዱም ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት አይከብድም። ግን የሚፈናቀል የለም። ዲሢዎች ሲቀበሉህ የነዋሪውን መብት እስካከበርክ ድረስ መኖር ትችላለህ የሚል የሰበብ ቀይ መስመር እያሰመሩ አይደለም። ሰው ስለሆንክ ብቻ ከነሱ እኩል ነህ። የዲኤንኤ ምርመራ አያደርጉብህም። ሥራ ያፈላልጉልሀል። ሥራ በማለማመድ ይረዱሀል። ሰርተህ ማግኘት እስክትችል ቀለብ ይሰፍሩልሀል። ከሁሉም በላይ ባይተዋርነት እንዳይሰማህ ከላይ ባለው ማስታወቂያ ያስረዱሀል። ዲሢዎች ከፈለግህ ለራሥህ ስትል ቁዋንቁዋቸውን አጥና እንጂ ቁዋንቁዋችንን ካልተናገርህ ንቀኸናል አይሉህም። አገልግሎታቸውን ፈልገህ ወደነሱ ከሄድክ በነሱ ወጪ አስተርጉዋሚ ፈልገው ጉዳይህን ያደምጡሀል። የፅሁፍ ማስረጃም ከፈለግህ አንተ ምንም ወጪ ሳትጠየቅ ዶክመንቱን በእጅህ ይከቱታል። ይህንንም በህግ ከተውት ግድግዳ ላይ ለጥፈውታል። የኢትዮጵያውያን ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ የመንግሥት አገልግሎቶች በአማርኛ ቁዋንቁዋ ይሰጣሉ። ከላይ የተለጠፈውን ማስታወቂያም ከተለጠፈበት ቦታ ላይ ፎቶ አንስቼው ነው። አማርኛም እንግሊዝኛና ስፓኒሽኛን ተከትሎ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። ጃዋርና የጃዋር ቡድን በአሜሪካን ኖረው የሠለጠነውን ሕዝብ ፍልስፍናና ሕግ ጠንቅቀው ያውቃሉ። የችግር ጊዜንም አሳልፈውበታል። ከአራምባና ቆቦ የተሰባሰቡ የጋራ ታሪክ አልባ ስፔራንቶ ሰዎች ወረቀት ላይ በተፃፈ ሕግ አጣባቂነት ብቻ በሰላም ሲኖሩ አይተዋል። ታዲያ ስለምን በአገራችን ሕዝብ ላይ ጥላቻን እየዘሩ እሣትን ይለኩሳሉ። የጋሞ ሽማግሌዎችስ እስከመቼ ሳይሰለቻቸው ሌላው የለኮሰውን እሣት እያጠፉ ይኖራሉ። የዲሢ መንግሥትና የጋሞዎች ተግባር በሚገርም ሁኔታ ሲመሳሰል ለምን እነጀዋር መለስን ይደግሙታል። ስለምንስ ከህወሀቶች ጋር ወዳጅነታቸው ጠበቀ።

  1. “የዖሮሞን ሕዝብ በመናቅና በመጥላት መቀጠል አይቻልም!” ሕዝቅኤል ገቢሳ

ከውይይቱ ለመረዳት እንደሞከርኩት ፕሮፌሠሩ ይህን ለማለት ያስቻላቸው በቅርብ ጊዜ በተደረጉት ሠልፎችና በየሚዲያው የአንዳንድ ግለሰቦች ሥም እየተነሳ በመወገዙ ነው። ግለሰብን እያነሱ ከሕዝብ እኩል ማድረግ ሕዝቡን መናቅ አይደለም? እንዴት ቢታሰብ ነው ኢምንቱ ጀዋር መሀመድ ሲሰደብ የዖሮሞ ሕዝብ ተናቀ የሚያስብል መግለጫ ሊያሰጥ የሚችለው? ሕዝብ ከሰማይ በታች የሚፈራ የሚከበርና በተለይ በዲሞክራሢው ዓለም አድራጊ ፈጣሪ ባለሙሉ ምድራዊ ባለሥልጣን ነው። እንዴት ሕዝብ ሊናቅ ይችላል? ይህ ንግግር ወንጀል ሆኖ ሊያስቀጣ የሚገባ ጉዳይ ነው። በተለይ ገዳን የሚያክል የዴሞክራሢ ተቁዋም ባለቤት የሆነን ሕዝብ፤ የሞጋሳና የጉዲፈቻ ሥርዓት ፈጣሪ ሰፊና ትልቅ ሕዝብ እንዴት ሊናቅና ሊጠላ ይችላል? ምን ቢሆን አበበ ቢቂላን ለዓለም ያበረከተ፤ አበበ አረጋይን ያፈራ፤ ራስ መኮንን ወልደሚካዔል ጉዲሳን የሰጠን፤ ኧረ ስንቱን የለገሰ ሕዝብ ሊናቅና ሊጠላ ይችላል? የህወሀት ባለጌዎች “የትግራይ ሕዝብና ህወሀት አንድ ናቸው!” ሲሉ አለማፈራቸው ሲገርመን እኚህ ፕሮፈሰር ከነሱም ዝቅ ብለው “ጀዋር መሀመድና የዖሮሞ ሕዝብ አንድ ናቸው!” እያሉ ነው። አሳፋሪ ነገር! ዶር ዓቢይ እኔን ጨምሮ በጣም ብዙ ኢትዮጵያውያን በበዓለ ሲመታቸው ላይ ባደረጉት አንድ ንግግር አጃኢብ ብለን ወደድናቸው፥ አፈቀርናቸው፥ አከበርናቸው። ቢሆንም እንኩዋን ከኦሮሞ ሕዝብ እኩል ሊሆኑ አይችሉም። በቀለ ገርባን በክፉ ቀን ጮህንለት ለነፃነቱ ባደረገው ተጋድሎ አከበርነው። በአገራችን አንድነት ላይ ሲመጣብን ደግሞ በዐይናችን ሆነብንና ናቅነው። ጀዋር መሀመድ ከፋፋይ ንግግሩን በየአዳራሹ ሲዘራ ለረዥም ጊዜ ታገስነው። ጭብጨባው አስክሮት ሕዝብን ወደገደል እየመራ መሆኑ ሲያሰጋን በቃህ ብንለው እንዴት ዖሮሞን መናቅና መጥላት ተብሎ ይተረጎማል? ይሄ ፖለቲካ የሚሉት ነገር እንደው ምን ዓይነት አረቄ ይሆን ስንት ዓመት ሙሉ በመፅሀፍ የገነቡትን ዓዕምሮ ሙልጭ አርጎ አጥቦ መና የሚያስቀርና እንዲህ አይነት ፀያፍ ንግግር የሚያናግር?

  1. እንደምድመው

የለውጥ ኃይሉ እስካሁን የሄድንበት የዘር ፖለቲካ አያዋጣም በማለት ወደ ኢትዮጵያ አንድነትና ከዚያም በላይ እየተለመ ነው። እግዚአብሔር ይመስገን! በዚህም ምክንያት የለውጥ ኃይሉና የአንድነት ኃይሎች በማይታመን ደረጃ እየተቀራረቡ ነው። በመጪው ምርጫ ዋናው የኢትዮጵያ መረጋጋትና የአምባገነን ገዢዎች ዘመን ግብአተ መሬት መፈፀሙ ነው፤ በሚል አመክንዮ አርበኞች ግንቦት 7 ራሤን ከምርጫ አገላለሁ ብሎ፤  ዶ/ር ብርሀኑ ለዶ/ር አቢይ መመረጥ ቢቀሰቅስ አይገርምርኝም። እንደውም እንደገና እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። ከስድስት ወራት በፊት በእንጨት እንኩዋን ለመንካት የምንጠየፈውን ድርጅት፤ ኢህአደግን ዛሬ በአቢይና በለማ በኩል እያንቆለጳጰስነው ነው። ይህን ማን ያምናል? አለማመን ብቻ አይደለም የዘር ፖለቲካ እነሱ ሥልጣን መንበር ላይ እስኪወዘቱ ድረስ እንዲቀጥል ጠዋት ማታ እንቅልፍ አጥተው የሚታትሩ በዝተዋል። ስለዚህ ጃዋር=በቀለ=የኦሮሞ ሕዝብ፤ ቀመር ሠርተዋል። ይህ ነው የኦሮሞን ሕዝብ መናቅ። እኛኮ በእያንዳንዳችን ደም ውስጥ 40%ኦሮሞ 30% አማራ 3%ትግሬ 4% ሶማሌ ወዘተ ሆኖብን ተቸግረን ነው ዘረኝነትን የተጠይፍነው። እንዴት ራሳችንን በመናቅ እንከሰሳለን? “አድራጊ ፈጣሪ ሕዝብ ነው!” ብለን የምናምን ነን። ይህን ቀመር ለማስረፅ ላንቃቸውን ሲያላቅቁ የሲራኩየስ ነዋሪዎች የአርኪሜደስን ነውር ከውጭ እንደታዘቡት እኛም የነዚህን ዘረኞች ነውር ከውስጥ እየታዘብን ነው። ትዝብት ግን አይበቃም።  የድርሻችንን እንወጣ። እኛ ስንል ዖሮሞ ነን! ጋምቤላ ነን! ሶማሌ ነን! አማራም ትግሬም ወዘተ ነን! እኛ እኛን አንጠላም! እኛ እኛን አንንቅም! አትከፋፍሉን! የአንድነቱና የዴሞክራሢው ጉዞ እንዲቀጥል አስፈላጊውን እናደርጋለን። ቅን ልቦና ይዘን ብንነጋገር መንገዳችን የጨርቅ ይሆናል። ዋቀዮ ይህን ያመላክተን።

እኛ ተጎሳቁለን ኢትዮጵያን ይመቻት!

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.