አብዴፓ ባካሄደው ጉባኤ ውህደቱን በመደገፍ በሙሉ ድምፅ አፀደቀ

Source: https://fanabc.com/2019/11/%E1%8A%A0%E1%89%A5%E1%8B%B4%E1%8D%93-%E1%89%A3%E1%8A%AB%E1%88%84%E1%8B%B0%E1%8B%8D-%E1%8C%89%E1%89%A3%E1%8A%A4-%E1%8B%8D%E1%88%85%E1%8B%B0%E1%89%B1%E1%8A%95-%E1%89%A0%E1%88%98%E1%8B%B0%E1%8C%88/

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ወደ ብልፅግና ፓርቲ የሚደረገውን ውህደት በመደገፍ በሙሉ ድምፅ አፀደቀ።

አብዴፓ በጠቅላላ ጉባዔው ውህደቱን በመደገፍ በመሉ ድምጽ ያጸደቀው ለአርብቶ አደሩ ህብረተሰብ ባለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ዙሪያ በስፋት ከተወያየ በኋላ ነው።

የአብዴፓ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አወል አርባ እንደተናገሩት ባለፉት 27 ዓመታት አፋርን ጨምሮ አምስቱን ክልሎች አጋር በመባል ተገልለው ቆይተዋል።

የክልሉ መሪ ፓርቲ ጉዳዩን አስመልክቶ በተለያዩ መድረኮች ችግሩ እንዲፈታ ሲጠይቅ ቢቆይም አጥጋቢ መልስ እንዳልነበረው አስታውሰዋል።

አሁን የተገኘው ውህደት የአፋር ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹ ጋር በጋራ ሀገርን ወደተሻለ ከፍታ ለመሻገር የሚያስችል መልካም አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

“አፋር እራሱን አጥሮ ከመቀመጥ ይልቅ ከተሻሉ ሰዎች ጋር ተወዳድሮ ልማትና ሁለንተናዊ እድገት በማስመዝገብ አንድ ኦኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመፈጠር የራሱን አሻራ የሚያሳርፍበት ጊዜ ላይ ይገኛል” ብለዋል።

ምክትል ሊቀመንበሩ እንዳሉት ውህደቱ በተጨማሪም አፋርኛ የሀገሪቱ ብሄራዊ ቋንቋ በማድረግ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር ያለውን ትስስር እንዲያጎለብት  እድል ይፈጥራል።

ውህደቱን በተመለከተ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች እንደሚወራው እንዳልሆነ ገልጸው የድርጅቱ አባላት እስከታች ወርደው ትክክለኛውን ሀቅ ህብረተሰቡ እንዲገነዘብ ተግተው በመስራት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.