አትሌት አሰለፈች መርጊያ በ200 ሚሊየን ብር ወጪ ያስገነባችውን ባለ ሶስት ኮኮብ ሆቴል አስመረቀች።በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ወሰን አካባቢ የተገነባው ሆቴል እና ስፓ በዛሬው እለት ተመ…

አትሌት አሰለፈች መርጊያ በ200 ሚሊየን ብር ወጪ ያስገነባችውን ባለ ሶስት ኮኮብ ሆቴል አስመረቀች።

በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ወሰን አካባቢ የተገነባው ሆቴል እና ስፓ በዛሬው እለት ተመርቋል።

በምረቃ መረሀ ግብሩ ላይ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር ሚንስትር ዴኤታ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ እንዲሁም አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ ፤ አትሌት ደራርቱ ቱሉ ፤ አትሌት ገዛሀኝ አበራ እና ሌሎችም ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሆቴሉን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ በብዙ ችግር በምታልፍበት ጊዜ ሁሉ አትሌቶቻችን ግን የሀገሪቱን ሰንደቅ አላማ በመልካም ስም ከፍ አድርገው ማውለብለብ ችለዋል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በልዩ ልዩ የልማት ዘርፍ በመሰማራት ለዜጎች የስራ እድል ከመፍጠር ጀምሮ ለሀገሪቱ የሆቴል ኢንቨስትመንት እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እያከናወኑ ይገኛል።

በዛሬው እለት አገልግሎቱን በይፋ የጀመረው የአትሌት አሰለፈች መርጊያ እና ባለቤቷ ሆቴል የዚሁ አካል ነው ያሉ ሲሆን ወደ ፊትም ለሚሰሯቸው የልማት ተግባራት የኦሮሚያ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በምርቃቱ ወቅት እንደገለፁት ሆቴሉ የጥንካሬያችሁን ፤ የጥረትታችሁ እና የፅናታችሁ ተምሳሌት ነው ብለዋል።

ይህንን የመሰለ ሆቴል በራሳችሁ ወጭ ገንብታችሁ ለከተማችን ውበት ስለሰጣችሁን እናመሰግናለን በማለት ገልፀዋል።

የባህልና ሚንስቴር ሚንስትር ዴኤታ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ በበኩላቸው አትሌቶቹ የሚያገኙትን ጥሪት በልማት ዘርፉ ማፍሰሳቸው የስራ እድል መፍጠር መቻላቸው ያስመሰግናቸዋል።

የሆቴል ኢንቨስትመንቱ ሀገሪቱ ከምትቀባላቸው ቱሪስቶች አኳያ ውስን በመሆኑ የሰራችሁት ሆቴል ይህንን ክፍተት ከማቃለል አንፃር የራሱ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል።

አትሌት አሰለፈች መርጊያ እና ባለቤቷ አትሌት ኪዳኔ ገመቹ በእለቱ እንደገለፁት በአትሌቲክሱ ዘርፍ ብዙ ነገር አሳልፈናል ፤ ወደ ፊትም ጥረታችን ይቀጥላል ፤ ለዚህም ስኬት ከጎናችን ሆናችሁ ለደገፋችሁን ምስጋናችን የላቀ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

አትሌቶቻችን በሩጫም ብቻም ሳይሆን ለሀገር ልማት የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል።

ሆቴሉ በ200 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባ ሲሆን የመሰብሰቢያ አዳራሽን ጨምሮ 42 በላይ የመኝታ ክፍሎች፣ ሬስቶራንት፣ ጂም እና ሌሎች የሆቴልና ስፓ አገልግሎቶችን ያካተተ ነው።

በደረሰ አማረ
ጥቅምት 7 ቀን 2013 ዓ.ም

Source: Link to the Post

Leave a Reply