አቶ ጌታቸው አምባዬ ከስልጣን የተነሱት በሙስናና እስረኞችን አልፈታም በማለታቸው ነው ተባለ

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%8A%A0%E1%89%B6-%E1%8C%8C%E1%89%B3%E1%89%B8%E1%8B%8D-%E1%8A%A0%E1%88%9D%E1%89%A3%E1%8B%AC-%E1%8A%A8%E1%88%B5%E1%88%8D%E1%8C%A3%E1%8A%95-%E1%8B%A8%E1%89%B0%E1%8A%90%E1%88%B1%E1%89%B5-%E1%89%A0/

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 16/2010)በኢትዮጵያ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሆነው የሰሩት አቶ ጌታቸው አምባዬ ከስልጣን የተነሱት ከሙስናና ከሕወሃት ጋር ባላቸው ቅርበት እስረኞችን አልፈታም እያሉ በማስቸገራቸው መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገለጹ።

አቶ ጌታቸው አምባዬ በተለይም የዋልድባ መነኮሳትን ላለመልቀቅ በማቅማማታቸው ከእስር ሳይፈቱ እንዲዘገዩ አድርገዋል ተብሏል።

የቀድሞው አቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ በነባሩም ይሁን በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መነኮሳቱን እንዲፈቱ ተጠይቀው እምቢተኛ ሆነው መቆየታቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

ብአዴንን ወክለው በተለያዩ የስልጣን እርከኖች በልዩ ልዩ ሃላፊነት የሰሩት አቶ ጌታቸው አምባዬ በሙስናና ለሕወሃት ባላቸው ታማኝነት ይታወቃሉ።

በአማራ ክልል የፍትህ ቢሮ ሃላፊ ሆነው በሰሩበት ወቅት በርካታ ዳኞችን በማባረርና የጥብቅና ፈቃድ በመከልከል እንዲሁም በልዩ ልዩ የስነ ምግባር ችግር የሚጠቀሱት  አቶ ጌታቸው አምባዬ ከነጋዴዎች ጋር ባላቸው ትስስርም ሙሰኛና ለጥቅም የቆሙ መሆናቸው ይነገራል።

ይህም ሆኖ ግን ለሕወሃት ባላቸው ታማኝነትና ታዛዥነት በስልጣን ላይ ስልጣን ደርበው የፍትህ ሚኒስትር ለመሆን በቅተዋል።

የፍትህ ሚኒስትር በነበሩበትም ጊዜ በርካታ ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞችን በሐሰት በመወንጀል እየከሰሱ ለፍርድ ሲያቀርቡ የነበሩትም እራሳቸው ናቸው።

በጤና እክል ምክንያት አብዛኛውን ጊዜ በሆስፒታልና ውጭ ሃገር ቢያሳልፍም ከስልጣን ሳይነሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በመሆን አዲሱ ካቢኔ እስከተሰየመበት ጊዜ ድረስ የሕወሃት ታማኝ ሆነው አገልግለዋል።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተደጋጋሚ ሲደነገግ ሕጉን በማርቀቅና ተፈጻሚነቱን በመከታተል ሪፖርት ሲያቀርቡ እንደነበርም ይታወሳል።

የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ እስረኞችን ለመፍታት ሲወስን ከሕወሃት ጋር ሆነው ከፊሎቹ እንዳይፈቱ ሲከራከሩ ነበርም ተብሏል።

በተለይ ደግሞ የዋልድባ መነኮሳት ከእስር እንዳይፈቱ ጉዳዩን በማዘግየት ትልቁን ሚና የተጫወቱት አቶ ጌታቸው አምባዬ መሆናቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

መነኮሳቱ እንዳይፈቱ በአቶ ሃይለማርያምም ሆነ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ሲታዘዙ አቶ ጌታቸው አምባዬ እምቢተኛ በመሆናቸው መነኮሳቱ ከሌሎች ታሳሪዎች ዘግይተው እንዲፈቱ ተደርገዋል።

አቶ ጌታቸው በ24 ሰአታት ውስጥ መነኮሳቱን እንዲፈቱ የጊዜ ገደብ ተቀምጦላቸው ባለመታዘዛቸው ከአዲሱ የኢሕአዴግ አመራር ጋር አተካራ ውስጥ ነበሩ ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በባህርዳር በነበራቸው ቆይታ የዋልድባ መነኮሳት በብዙ ትግል እንዲፈቱ መደረጋቸውን መግለጻቸውም ይታወሳል።

በመጨረሻም ከባለስልጣናት ጋር ተናበው ባለመስራታቸውና በሙስናም የሚጠረጠሩ በመሆኑ አቶ ጌታቸው በአዲሱ ካቢኔ እንዳይካተቱ መደረጋቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል።

አቶ ጌታቸው አምባዬ በቅርቡ አቶ ካሳ ተክለብርሃንን ተክተው የብአዴን ስራ አስፈጻሚ ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል።

ይህም ሁኔታ እያወዛገበ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል እንዲጠየቁ የሚገፋፉ ባለስልጣናት መበራከታቸው ይነገራል።

 

 

 

The post አቶ ጌታቸው አምባዬ ከስልጣን የተነሱት በሙስናና እስረኞችን አልፈታም በማለታቸው ነው ተባለ appeared first on ESAT Amharic.

Share this post

One thought on “አቶ ጌታቸው አምባዬ ከስልጣን የተነሱት በሙስናና እስረኞችን አልፈታም በማለታቸው ነው ተባለ

  1. Getachew Ambaye should be arrested and face the same justice system he deprived others. I have never seen such stupid Amara who persecutes Amaras.

    Reply

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.