ኡጋንዳ በሶማሊያ ያሰፈረችውን ወታደሮቿን ወደ ሀገሯ መለሰች

Source: http://amharic.abbaymedia.info/archives/39864

አባይ ሚዲያ ዜና
ዘርይሁን ሹመቴ

ኡጋንዳ በሶማሊያ ለሰላም ማስከበር ሂደቱ የመደበቻቸውን  ወታደሮች በማስወጣት ወደ ሀገሯ መመለስ እንደጀመረች ተዘገበ።

በሱማሊያ ሰላምን ለማረጋጋት ከየትኛውም አገራት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጦርን ያሰፈረችው ኡጋንዳ ከ 200 በላይ ወታደሮቿን ከሱማሊያ ማስወጣት መጀመሯ ታውቋል።

በያዝነው የፈረንጆች አመት መገባደጃ በሶማሊያ የሚገኙ ወደ 1000 የሚሆኑ ከተለያዩ የአፍሪቃ አገራት የተውጣጡ ወታደሮችን እንዲቀነሱ ትእዛዝ መተላለፉ ይታወሳል።

በዚህም መሰረት ኬኒያ፣ ኢትዮጵያ፣ ቡሩንዲና ጅቡቲም በሶማሊያ ያዘመቱትን ወታደሮች ከአመቱ መጠናቀቂያ በፊት እንዲቀንሱ ትእዛዝ ተሰጥቷል።

ምንም እንኳን እነዚህ አገራት በሶማሊያ ሰላም ለማስከበር ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ ሆኖ እንዳገኘው የተባበሩት መንግስታት ቢገልጽም ህይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ለሚዋደቁ ወታደሮቹ መከፈል የሚገባው ክፍያ በሙስና መመዝበሩን ግን ተችቷል።

ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ የአፍሪቃ ሀገራት በሶማሊያ የታሰበውን ሰላምና መረጋጋት የማስፈን አላማን አጥጋቢ በሆነ ፍጥነት እውን ማድረግ እንደተሳናቸውም የተባበሩት መንግስታት ገልጿል።  

በአገሪቷ ሰላምንና መረጋጋትን ለማምጣት ከሌሎች አገራት የወታደር ልመና ይልቅ ሶማሊያ የራሷ የሆነ የመከላከያ ሃይል መገንባት እንዳለባትና ይህንንም የተባበሩት መንግስታት እንደሚደግፍ ተገልጿል። 

ዩናይትድ ስቴትስ በአየር የምታደርገውን የጦር እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ወደ 500 የሚደርሱ  የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮችም በሶማሊያ ሰፍረው ከሶማሊያ መከላከያ ጋር በጥምረት እንደሚሰሩ ታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ወደ 1000 የሚጠጉ ወታደሮችን ከከባባድ የጦር መሳሪያዎች ጋር በማጀብ ወደ ሶማሊያ ክልል ዘልቆ ማስገባቱን መግለጹ ይታወሳል።

 

Share this post

Post Comment