ኢትዮጵያውያን አርበኞች!

Source: http://welkait.com/?p=9356
Print Friendly, PDF & Email

(ቀሲስ አስተርአየ)

nigatuasteraye@gmail.com ነሐሴ 25 ቀን፡ 2ሽ 9 ዓ/ም

ኢትዮጵያውያን አርበኞች፦ በነገሥታት ወይም በማሳፍንት ዘር ከማይወረሰው፤ የተለያዩ ቋንቋ ከሚናገሩና በተለያዩ መንደሮች ከሚኖሩ ልጆቿ ኢትዮጵያ በመከራዋ ጸንሳና አምጣ እንደገና ምትወልዳቸው ናቸው።

ኢትዮጵያውያን አርበኞች

ኢትዮጵያ ለመከራዋ ዘመን አምጣ ከወለደቻቸው ሊቃውንት አንዱ ሊቀጠበብት አድማሱ ካምስቱ አመታት ወረራ በኋላ፤ ለአገርና ለቤተ ክርስቲያናቸው የሰጡትን የመንፈስና የዜግነት አስተዋጽኦ አቀርባለሁ ብየ ቃል ገብቼ ነበር። የገባሁትን ላማቅረብ ጀምሬ ሳለ፤ በወረራው ዘመን ተመሳሳይ ታሪክ የሰሩ አባቶች ብዙ ቢሆኑም፤ በተደጋጋሚ ሲወሱ የሰማኋቸው እጅግ አስደናቂ ስራ የሰሩ ስመ ጥር አርበኞች የሊቀጠበብት አድማሱን ጓዶች ከዚህ ቀደም ባቀረብኴቸው ጦማሮች ሳልጠቅሳቸው በማለፌ፤ ከወረራው በኋላ ሊቀ ጠበብት ወደሰሯቸው ለመሻገር ጭንቅላቴ አልታዘዝልኝ አለ።

ኢትዮጵያውያን አርበኞች

ተመሳሳይ ታሪክ የሰሩ አባቶች ብዙ ቢሆኑም፤ ከዚህ ቀደም እንዳልኩት፤ የነ ሊቀ ጠበብት መቃብር መፍለስ ስለቀሰቀኝ እንጅ፤ ከዚያ በፊት ስለነ ሊቀጥበብት አድማሱ ለመጻፍ ያሰብኩበት ጊዜ አልነበረም። እነመላከ ሰላም ዓላማየሁ ሰሩትን ጀብዱ በመላ ኢትዮጵያ ካሉት ሁሉ ኢትዮጵያውያን የተወለዱ የሰሩ ብዙ እንዳሉ አውቃለሁ። ባውቅም፤ ከቤት፤ ከጎረቤ፤ ከሊቃውንትና ካዛውንት ተደጋግሞ የተነገረኝን ባቀረብኩበት መንፈስ ሀላፊነቱን ወስጄ ማቅረብ አልችልም። ላቅርብ ብልም በመቁረጥና በመለጠጥ አበላሽ ይሆናል ብየ እፈራለሁ። የዚህን ሀላፊነት በሙያው እጅግ ለደከሙት ለመምህራችን ለክቡር ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ እተወዋለሁ።

ስለ ሊቀጠበብት አድማሱ ባዛውንቱ በሊቃውንቱ ሲነገር ከሰማሁት ጋራ፤ በተጨማሪ ካንድ እስከ ሶስት ጊዜ አካላቸውን ለመየት ድምጻቸውን ለመስማት እድል ስለገጠመኝ ምስክርነቴን ሰጥቻለሁ። ሆኖም ባምስቱ የወረራ ዘመን ከበረንታ ጎይ ጊርጊስ ጀምሮ እስከ ከደብረ ማርቆስ ሊቀጠበብት አድማሱ የሰሩትን፤ የሊቀ ጠበብት አድማሱ ጓዶች መላከ ሰላም ዓለማየሁ ሻሾና ራስ ኃይሉ ከደብረ ማርቆስ ጀምሮ በቆላ ደጋ ዳሞት ሰሩ እየተባሉ በመደነቅ መወሳታቸውን በዚህች ጦማር ላወሳቸው ተገደድኩ።

ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤ፤ ሊቀ ጠበብት አድማሱ፤ መላከ ሰላም ዓለማየሁ ሻሾና ራስ ኃይሉ ባምስቱ የመከራው ዘመን የሰሩትን፤ የነበሩ ያዩ ሰዎች በሚያረካው ምስክርነታቸው እውነትን ለመስማት ሁልጊዜ በሚጠማው ጆሮየ ሰምቼ፤ የመስማት ጥማቴን አርክተውልኛል። በወገን በአገር በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ሚካሄደውን ከመስማት የተወገደ ኢትዮጵያዊ በሀሳብ ድርቅ የተማታ ይመስለኛል።

ባለነበርነበት የተደረውን በዜና መልክ የሚደርሱን ክስተቶች ለመስማት ጆሯችን የተጠማ ነው። የመስማት ጥማችንን አስወግደው የተጠማውን ወገናቸውን ከሀሳብ ድርቅ ለማላቀቅ የሚታገሉትን ግለ ሰቦች፤ ድረ ገጾችና ብዙሀን መገናኛዎች ሁሉ አርበኞች ነቸውና ሊመሰገኑ ይገባል።
ሁኔታውን ጠቢቡ ሰሎሞን “ከመ ማይ ቆሪር ለነፍስ ጽምእት አዳም፤ ከማሁ ዜና ሠናይ እምድር ርሁቅ” ተግ 1፡25። ብሎ ገልጾታል። ማለትም፦ ከሩቅ አገር የሚመጣ ዜና በውሀ ጥም የተንገበገበችውን ሰውነት እንደምታረካ ቀዝቃዛ ውሀ ናት።

ጠቢቡ እንዳለው በዘመንና በቦታ ርቆ ያለ ወገን፤ በራቀው ወገኑና አገሩ ላይ ምን ተደርጎ ተፈጽሞ ይሆን? እያለ እንደ ምንጭ ውሀ የጠራ ዜና ለመስት ይጠማል። ዜና ሠናይ ማለትም ያልተለጠጠና ያልተቆረጠ ለፖለቲካ ወደብ መድረሻ ተብሎ ያልተዘጋጀ ለመስማት የተጠማውን ለማርካት በጆሮ የሚንቆረቆር እውነተኛ ምስክርነት ነው። ይህን የመሰለ ዜና ከሚጠሙት ብዙዎቹ አንዱ ነኝ።

ይህን አይነት ጥማት እነ ሊቀጠበብት አድማሱ፦ ዳዊት ተጠማሁ ካላት በቤተ ልሄም ምንጭ ውሀ ይመስሏታል። ዳዊት በመከራው ዘመን ያደገባት የተወለደባት የቤተ ልሄም ሁኔታ አስጨነቀው። ከቤተ ልሄም ውሀ ማን ባመጣልኝ በማለት ጭንቀቱን በውሀ ጥም ገለጸው። የዳዊት ባልደረቦቹ (40ኞቹ)ለህይወታቸው ሳይሳሱ የሚቃወሟቸውን ሠራዊት ሰንጥቀው አልፈው ከቤተ ልሄም ምንጭ የተጠማውን ውሀ ለዳዊት አመጡለት(2ኛ ሳሙ 23፡16)። እነዚህ የዳዊት አርበኞች ይባላሉ።

በሩቅ ላለን የወገን ሁኔታ እንደ እህል ለሚርበን እንደ ውሀ ለሚጠማን፤ ዜናው እንዳይደርሰን አፍኖ የያዘውን ሠራዊት ሰንጥቀው አልፈው ከአገራችን ከምንጩ የተደረገውን ዜና የሚያደርሱልንን ወገኖች የምንፈርጃቸው፤ ዳዊት የቤተ ልሄምን ውሀ ማን ባመጣልኝ ብሎ በጔጔበት ወቅት ከምንጩ ቀድተው ካመጡለት ባልደረቦቹ ወይም 40ኞቹ ጋር ነው።

ከኢትዮጵያ አገራችን ርቀን ላለን ሰዎች የተደረገውንና የሆነውን የሚያሰሙን ባይኖሩ ኖሮ፤ ስለ ሊቀጠበብት አድማሱ ጀንበሬ መጻፍ ቀርቶ አላስብም ነበር። ባለፉ ጦማሮች ስለታለፉት ስለ ሊቀጠበብት አድማሱ ጔዶች ወይም 40ኞች ስለነ መላከ ሰላም ዓለማየሁ ሻሾና ስለ ራስ ኃይሉም ይህችን ጦማር ባላዘጋጀኋትም ነበር።

ባለፉት ጦማሮች የተረሱትን እነ መላከ ሰላም ዓለማየሁን በማነሳበት በዚህች ጦማር እነመላከ ሰላም ዓለማየሁንና ራስ ኃይሉን ያስተሳሰረቻቸውን አርበኛ የምትለውን ቃል፤ ራሳቸው እነ ሊቀጠበብት አድማሱ እንዴት እንደሚገልጿት ብዳስሳት ከዚህ ቀደም ላልሰሟት ወጣቶች የሚትጠቀማቸው ይመስለኛል።

አርበኛ የምትለው ቃል በሊቃውንቱ በነ ሊቀጠበብት አገላለጽ ምንድናት?

በተለምዶ አጠራር አርበኛ እየተባለች የጀግኖች መግለጫ ሆና ምትጠቀሰዋን ቃል እነ ሊቀጠበብት አድማሱ እንደሚከተለው ይገልጿታል። ኢትዮጵያ በወራሪዎቿ በምትደፈርበት ዘመን ለመከላከልና ለማትረፍ በግንባር የሚሰለፉትን ወገኖች ህዝቡ አርበኞች በሚለው ቅጽል ይገልጻቸዋል። ለጀግኖች የተሰጠችው ይህች የመግለጫ ቅጽል፤ በተለምዶ ህዝባዊ አነጋገር እንደተቀየሩት ሌሎች ቃላት ተቀይራለች።

ለምሳሌ ኢትዮጵያን ጦቢያ፤ ነነዌን ነነይ፤ ፍሬ ከርስች የምትለውን ቃል፤ ፍሬ ፈርስች እንደሚለው፤ አርበኛ የምትለውም ቃል ከ40 ቁጥር የወሰደች 40ኛ መባል ሲገባት በተለምዶ ህዝባዊ አጠራር ወደ አርበኛ ተለውጣለች። 40 የምትባለው የቁጥር ኛ የተባለችውን አገናዛቢ አገባብ የተንተራሰች ቃል ናት“ ይሉና 40 የሰማኒያ ዘመን ማእከል ናት። 80 ዘመን የሰው ልጅ አስቦ አልሞ ማድረግ የሚፈልገውን ማድረግ የማይችልበት እድሜ ነው። 80 የሁለት40ዎች ድምር ናት። ይህች የ80 ዘመን ግማሽ የሆነችው 40 ቁጥር ኛ የተባለችውን አገናዛቢ ፊደል የተንተራሰች ቃል ናት ይሉና የሚጠቅሳቸው አስረጅወች አሏቸው።

ቤርዜሊ የተባለ የሰማኒያ ዕድሜ አዛውንት “እኔ የሰማኒያ አመት ሽማግሌ ነኝ። ክፉውን ከደገ፤ የወንዶችንና የሴቶችን ድምጽ መለየት እችላለሁን?ለምን ተጨማሪ ሸክም እሆናለሁ? ወደ መቃብር ቤት መሄድ ነው። እነሆ ከመዓምን ሰጥቸሀለሁ” (2ኛ ሳሙ 19፡ 32᎗39። ሲል የተናገረውን ይጠቅሳሉ።

የመጻህፍት መተርጉማንና የቅኔ መምህራን የቤርዜሊን ንግግር ተንተርሰው፤ “የሰማንያ ዕድሜ አዛውንቶች ጀግንነትንና ወኔን የሚቀሰቅሰውን ቅራርቶ፡ ፉከራ፡ የሴቶችንም የቅስቃሳ እንጉርጉሮ ለመስማት ይዘገያሉ። ለይቶ ለማወቅ ያቅታቸዋል። በወቅቱ ተገቢ የሆነ ዝግጅት ለማድረግ ያስቸግራቸዋል” ይላሉ።

ዳዊትም “እመሰ በዝኀ ሰማንያ ዓመ ወፈድፋዶንሰ እም እላ ጻማ ወህማም(መዝ 89፡9፡10)ብሏል። ይህም ማለት፦ ሰው ግፋ ቢል በዚህ ዓለም የሚኖረው 80 ዓመት ነው። ከሰማንያ ካለፈ የራሱን ሰውነት መሸከም ያቅተዋል። የህብረተ ሰብ ምንጭ የሆነው ሊሻር ሊሻሻል የማይቻለው ጋብቻም ”በሰማኒያ የታሰረ ነው“ የሚባለው ከዚህ በመነሳት እንደሆነ ይናገራሉ።

እንደ ዳዊት አገላለጽ 80 ዘመን የምድራዊ ዘመን የማጠቃልያ ጊዜ ናት። 40 እድሜ ለሰው ጤናማ እድሚ ማእከል፡ አፍላ እና አፋፍ ናት። በ40 እድሜ ላይ ያለ ዜጋ፤ ከ40 እድሜ በታች ያለውን ወጣት 40 ላይ ለመድረስ በአካልና በአዕምሮ የሚያደርገውን ግስጋሴ ቁልቁል የሚያይበት እድሜ ነው። እንደገና 40 እድሜ አፋፍ ላይ ከደረሰ በኋላ ወደ ማብቂያው እድሜ ማለትም 80 ላይ ለመውደቅ ቁልቁለት በመውረድ ላያ ያለውን አዛውንት የሚያይበት እድሜ ነው።

ከ40 እድሜ ክልል በታች ያሉት ወጣቶች እንደ ምሳሌ አርገው የሚመለከቷቸው ከነሱ በላይ ያሉትን የ40 ዘመን ጎልማሶችን ነው። በሰማኒያ ዘመን ያሉት አበውም ብዙ የሚጠብቁት ከነሱ ተከታዮች በ40 ዘመን ካሉት ነው። ይህም ማለት በ40 እድሜ ላይ ያሉት ሙሉ ጎልማሶች፤ ከ40 ዘመን በታች ላሉት ወጣቶችና፤ ከ40 ዘመን በላያ ላሉ አዛውንቶች መካከል ያሉ አጣማጆች አገናኞች ድልድዮች ናቸው።

በ40 እድሜ ላይ ያሉ “ከመ ይሚጥ ልበ ውሉድ ሀበ ልበ አበው”(ሉቅ 1፡17 ) እንደተባለው እንደ ዮሐንስ ምጥምቁ ናቸው። ካዛውንቱ የሰሙትንና ያዩትን ዘፈኑን እስክስታውን ቅራርቶውንና ፉከራውን እምነቱንና ባህሉን በበዓላት በወንፈል በደቦና በሰርግ ካ40 ዕድሜ በታች ላሉት ወጦች የሚያቀብሉ ናቸው። “አሁንስ መልካም ፍሬ የማያፈራ የማያደርግም ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል”(ማቴ 3፡10)እያለ ከበርሀ ገስግሶ እንደወጣው እንደ ዮሐንስ፤ ኢትዮጵያዊነት በጭንቅ በምጥ ላይ ስትወድቅ ከተለያዩ ኢትዮጵያውያን ነገዶች ተወልደው ብቅ የሚሉ ከኢትዮጵያዊነት ማህጸን እንደገና የሚወለዱ ኢትዮጵያ በርሀ ስትሆን የምትጠራቸው አርባኞ ጔዶች ናቸው።

አርበኝነት በአርባ ዕድሜ ክልል ላይ ሳሉ፦ በኢትዮጵያ መስዋእትነት የሚጠይቀውን ነገር ሁሉ ለመፈጸም ካማራው፡ ከኦሮሞው፡ ከአፋሩ፡ ከትግሬው፡ ከጉራጌው፡ ከሲዳሞው፡ ከወላይታው፡ ከጋሞው። ከጋምቤላው፡ ከቅማንቱና በመላ ኢትዮጵያ ካሉት ሁሉ ዘርና ነገድ 40ኛ እድሜያቸው የሚገጥማቸው ክስተት የሚስባቸው እንጅ ከነገስታትና ከመሳፍንት ዘር ቅብብሎሽ የሚወለዱ አይደሉም። ይህም ማለት ያርበኛ ልጅ እንደ አባቱ አርበኛ ይሆናል ማለት አይደለም።

“ጋሻና ጦር ለማንሳት ካልሆነ እንዳባቱ
ጥጡን አቅርቡለት ይፍተል እንደ እናቱ”

የተባለውም ግጥም የተገጠመለት፦ ያርበኛ ልጅ አርበኛ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ፤ ሳይሆን ቀርቶ እምድጃ ለምድጃ ሲርመጠመጥ በተገኘው ያርበኛ ልጅ ነው።

አርባኛነት የዘመን ክስተት የጠራቸው የእድሜ ጓዶች አፍላወች አቀበት ለመውጣት ቁልቁለት ለመውረድ የሚገታቸው ሃይል የሌለባቸው ናቸው። እነዚህም በአፍላ ዘመናቸው የተገኙ በዘመኑ ለተከሰተው ፈታኝ ክስተት ሁሉ የተጋለጡ አርባኞች ወይም ጓዶች ናቸው።

ከ40 ዘመን በታች ያለው ወጣት ፈጣን ትኩስ ቢሆንም። ሚዛናዊ መረዳት መቀበል ያለበት ከ40 ዘመን ቡድን ነው። አርባኛው በየጎራው በየሸንተረሩ ከሁሉም ቀድሞ እየተገኘ ለመስማት በመዘግየት ላይ ያለውን አዛውንት እየቀሰቀሰ፤ ቀድሞ በመገስገስ ተፈንጥሮ በመሄድ ላይ ያለውን ወጣት ”ልጅ ያበካው ለራት አይበቃም“ በሚለው ኢትዮጵያዊ ብሂል እየተቆጣጠረ የሚመራ ነው።

ከ 40 ዘመን በታች ያለው ወጣት ዘፈኑን፡ ቅራርቶውን፡ ፉከራውን፡ የባህሉና የሃይማኖቱን መረብ ከናት ካባትና ከዚያም በላይ ካለው አዛውንት ይልቅ የሚማረው የሚቀበለው በዕድሜ ከሚቀርበው ከትልቅ ወንድምና እህት ነው። ወጣቱን ካዛውንቱ የሚያስተሳስረው 40ኛ እድሜ ላይ ያለ ነው።

”ይህም ሲባል“ ይሉና ሊቃውንቱ፦ የቃሉን ይዘትና የሰውነትን አካላዊና መንፈሳዊ ብስለት ለመግለጽና በ 40 እድሜ ላይ ባለው ዜጋ ላይ ያለውን ከባድ ሃላፊነት ለመግለጽ እንጅ፤ ከ40 ዘመን በታች ካሉ ወጣቶችም ሆነ። ከ40 ዘመን በላይ ካለ አዛውንቶች የጀብዱ ስራ አይጠበቅም። አይሰራም። አልተሰራም ማለት እንዳይደለም ሊቃውንቱ ያስገነዝባሉ።

ከቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ ዘመን ጀምሮ የተከሰተው ሁሉ ራእይ በ40 እድሜ ያለውን ባዛውንቱና በወጣቱ መካከል ያለውን እየበላ የመጣ ነው። የአሁኑማ እንዲያውም አርባኛ የሚለውን ለአማራው ብቻ በመስጠት እያደነ በምብላትና በአርባናነታቸው የሰሩትን ወገኖች ሳይቀር መቃብራቸውን በማፍለስ ላይ ነው።

አርበኝነት በልጃገረድ አንገት ላይ የሚታየውን ዶቃ ሰብስቦ እንደያዘ ማተብ በኢትዮጵያ ዙሪያ የተሰለፉትን ማርዳወች (አርበኞች) ሰብስቦ አስተሳስሮ የሚይዝ ረቂቅ ክር ነው። 40ኛ በላይን ከሶማ፤ ሊቀጠበብት አድማሱን ከብቸና ደብር፤ መላከ ሰላም ዓለማየሁን ከአብማ ደብር፤ ራስ ሃይሉን ከደብረ ማርቆስ ሰብስቦ አስተሳስሮ የያዘ ማተብ እንደሆነ ሲናገሩ የሰማኋቸው የመላከ ሰላም ዓለማየሁ ሻሾ ትንሽ ወንድም መላከ ብርሃን በላይ ሻሾ ናቸው።

መላከ ብርሃን በላይ ሻሾ፤ አብማ ማርያም ተወልደው ላደጉት የመላከ ሰላም ዓለማየሁ ታናሽ ወንድም ናቸው። የብቸናን ቅዱስ ጊርጊስ ደብር ለቅቄ ለትምህርት ወደ ደብረ ሊባኖስ እስክመጣ ድረስ፤ ሊቀጠበብት አድማሱ ይመሩት ለነበረው ለብቸና ቅዱስ ጊዮርጊስ ደብር በመላከብርሃንነት ተሰይመው በመምራት የነበሩ ሊቅ ነበሩ።

እኒህ ሊቅ አባት እንደነገሩኝ፤ ታላቅ ወንድማቸው ዓለማየሁ ሻሾ የነቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሤና የነ አቶ አዲስ ዓለማየሁ የቅርብ ጓደኛ ነበሩ። ካምስቱ የመከራው ዘመን በፊት ሁለቱም ሊቀጠበብት አድማሱና መላከ ሰላም ዓለማየሁ ሻሾ ትምህርታቸውን ጨርሰው በስራ ተሰማርተው ነበር።

ሊቀጠበብት አድማሱ በሊቀጠበብትነት ታላቁን የብቸና ቅዱስ ጊርጊስን ደብር በመምራት ላይ ሳሉ፤ መላከ ሰላም ዓለማየሁ ሻሾ የራስ ኃይሉ የቅርብ አማካሪ ነበሩ። ዓለማየሁ ሻሾ በትምህርታቸውና በችሎታቸው ራስ ኃይሉ የሚያከብሯቸው በዘመኑ አሉ ከሚባሉት ከሊቃውንት አንዱ ነበሩ። መላከ ሰላም ዓለማየሁ ሻሾና ሊቀጠበብት አድማሱ ጀንበሬ ያብነቱን ትምህርት አብረው የተሳተፉ የሚዋደዱና የሚግባቡ ጓደኞች ነበር።

ባምስቱ የመከራው ዘመን ሊቀጠበብት አድማሱ ከጎይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጀምሮ እስከ ደብረ ማርቆስ ያሉትን አድባራትና ካህናት እንዳንቀሳቀሱ፤ መላከ ሰላም ዓለማየሁ ሻሾም ከራስ ኃይሉ ጋራ በመመካከር ከደብረ ማርቆስ ጀምሮ በቆላ ደጋ ዳማት የነበሩትን አድባራትና ካህናት እንዳንቀሳቀሱ ይነገራል።

በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ራስ ሃይሉ እንደነ ሊቀጠበብት አድማሱና መላከ ሰላም ዓለማየሁ ሻሾ ጎልተው በግንባር ቀደም ባይሰለፉም ጣሊያንን በመዋጋቱ ውስጥ እንዳሉበት ይነገራል። ራስ ኃይሉ በዘመኑ ከነበሩት መሳፍንት ይልቅ የጣሊያንን ዝግጅት የተረዱ ነበሩ። ከነ ሊቀጠበብትና ከነመላከ ሰላምም በተሻለ መጠን የጣሊያንን አሰላለፍና ስነ ልቡና ያውቁ ነበር። በጎጃም ከነበላይ ይልቅ ብዙ ተሰሚነት ተከታይና ንብረት የነበራቸው እጅግ የተደራጁ ነበሩ።

ይሁን እንጅ ከጣሊያን ጋራ በመሰለፍ አገራቸውን አልወጉም። ከበላይ ጋራ በመወገንም በይፋ ሠራዊት አስነስተው ለበላይ እንቅፋት አልሆኑም። ለምን? ለሚለው ጥያቄ እነ መላከ ብርሃን በላይ ሻሾ ያሉ ሊቃውንትና እና ያካባቢው ሰዎች የሚናገሩት የሚመልሰው ይመስለኛል።
ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ልጅ ኢያሱን በመግደላቸው ከተቀየሟቸው ብዙ ሰዎች ራስ ኃይሉ አንዱ ነበሩ። ልጅ ኢያሱ የሰብለ ወንጌል ሃይሉ ባል፤ የራስ ኃይሉ አምቻ ናቸው። ራስ ኃይሉም የልጃቸውን ባል አምቻቸውን ስለገደሉ በቀደማዊ ኃይለ ሥላሴ ላይ ቅሬታ ነበራቸው። በዚህ ምክንያት ህሊናቸው የቀዳማዊ ሃይለ ስላሴን መንግስት ተጸይፏል። የቀዳማዊ ሃይለ ስላሴን መንግስት ቢጸየፉም ራስ ኃይሉ እንደ ኃይለ ስላሴ ጉግሳ ሠራዊት ክተት ብለው በአገራቸው ላይ አልዘመቱም። ይልቁንም በጥጋቸው ያሉት እነ መላከ ሰላም ዓለማየሁን እየደገፉ ተዋጊ አርበኞችን የሚያጠናክሩበትን ዘዴና ጥበብ በማቀበል ያበረታቱ ነበር። የነበላይን የነአበረ ይማምን ጥንካሬ ያደንቁ ነበር። “የኮስተር አሽከር” እየተባለ ለሚፈክርለትን ለበላይ ይገባዋል ይሉ ነበር። በላይ በስቅላት ሲገደል ራስ ኃይሉ አዝነዋል።

ከመላ ጎጃም ከወሎ ከቤገምድር ከሸዋና ከወለጋ አዛውንቱን ጠርተው በደብረ መርቆስ ለበላይ ባወጡለት የመታሰቢያ ተዝካር ላይ፦

“አሁን ለምን ሞተ ለምን ተቀበረ
ክፉ የክፉ ቀን ይሆን የነበረ”

ብለው ምሾ እንዲወርድለት አድርገዋል። ራስ ኃይሉ በመስፍንነት የምታስተስተሳስራቸውን ማተብ በጥሰው ኢትዮጵያ በመከራዋ ዘመን ከወለደቻቸው ከእነ መላከ ሰላም ዓለማየሁ፤ ሊቀጠበብት አድማሱ ጀንበሬና ከነ በላይ ዘለቀ ጋራ በአርበኝነት እትብት ተሳስረው ከአርባኛነት ማህጸን ተጸንሰው እንደገና የተወለዱ አርበኛ ነበሩ።

ካምስቱ የወረራ ዘመን በኌላ ሊቀ ጠበብት አድማሱ ጀንበሬ ለአገራችንና ለቤተ ክርስቲያናችን የሰሯቸውን አቀርባለሁ ብየ ከዚህ ቀደም በገባሁት ቃል መሰረት፤ ቀጥየ በማቀርባት ጦማር እስክንገናኝ የሁላችንም አምላክ የተሻለ ዜና ያሰማን!

Share this post

One thought on “ኢትዮጵያውያን አርበኞች!

Post Comment