ኢትዮጵያውያን አደገኛ ወንጀል በመፈጸም የተሰወሩ ግለሰቦችን መረጃ በመስጠት እንዲተባበሩ የዋሽንግተን ዲሲ ፖሊስ ጠየቀ

Source: http://amharic.ethsat.com/%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB%E1%8B%8D%E1%8B%AB%E1%8A%95-%E1%8A%A0%E1%8B%B0%E1%8C%88%E1%8A%9B-%E1%8B%88%E1%8A%95%E1%8C%80%E1%88%8D-%E1%89%A0%E1%88%98%E1%8D%88%E1%8C%B8%E1%88%9D/

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 12/2010)በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች ዜጎች በዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ አደገኛ ወንጀል በመፈጸም የተሰወሩ ግለሰቦችን በተመለከተ መረጃ በመስጠት እንዲተባበሩ ጥሪ ቀረበ።

የዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ፖሊስ ዲፓርትመንት ለኢሳት በላከው መግለጫ በመሳሪያ የተደገፈ ጥቃት ፈጽመው የተሰወሩ ግለሰቦችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ መረጃ በመስጠት እንዲተባበር ጥሪ አቅርቧል።

በቅርቡ ህዳር 6/2017 ከምሽቱ 8 ሰዓት ከ20 ላይ በጆርጂያ ጎዳና በ5 ሺ አራት መቶ አድራሻ የመሳሪያ ጥቃት በመሰንዘር አንድን ግለሰብ ያቆሰለ ተጠርጣሪ መሰወሩን በቪዲዮ በተደገፈ መረጃ ይፋ አድርጓል።

የዋሽንግተን ዲሲ ፖሊስም በዚህ መረጃ ላይ ተመስርተው ተጠርጣሪውን እንዲጠቁሙ ጥሪ አቅርቧል።

እንዲሁም ማክሰኞ ህዳር 7/2017 በሪትን ሀውስ ጎዳና ከምሽቱ 8 ሰአት ከ15 ደቂቃ ላይ አንድን ግለሰብ በመግደልና ሌላውን በማቁሰል የተሰወረውን ግለሰብም በመጠቆም እንዲተባበሩ ጠይቋል።

እንዲሁም ህዳር 5/2017 በዋሽንግተን ዲሲ ሼፐርድ መንገድ ከምሽቱ 8 ሰዓት ከ20 ላይ የ35 አመቱን ሁዋት ኒልሰን ሮበርትስን ገድሎ የተሰወረውን ግለሰብ በተመለከተም የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

የዋሽንግተን ዲሲ ፖሊስ ይህን ላደረገ ለወሮታው ከ10 ሺ እስከ 25 ሺ የአሜሪካን ዶላር በስጦታ እንደሚያበረክት አስታውቋል።

መረጃ ያላቸውና ጥቆማ መስጠት የሚፈልጉ በስልክ ቁጥር 202-727-9099 እንዲሁም በቴክስት ቁጥር 50411 መጠቀም እንደሚችሉም የዋሽንግተን ዲሲ ፖሊስ ለኢሳት የላከው መረጃ ያሳያል።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.