ኢትዮጵያ ወይስ ኩሽ? – ጌታቸው ኃይሌ

Source: http://welkait.com/?p=11197
Print Friendly, PDF & Email

ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ

አንድ ሰሞን “የጀርመን ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን በሪቨረንድ በንቲ ቴሶ ኡጁሉ ተጽዕኖ የኢትዮጵያን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰርዛ በኩሽ ለውጣዋለች” የሚል ወሬ ተናፍሶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን አበሳጭቶ ነበር። ብዙ ተቃውሞም ተጽፏል። ይኼ ተጨማሪ ማብራሪያ ነው።

ከመጀመሪያው ለመነሣት፥ መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው ቅድመ ክርስቶስ፥ ሁለተኛው ድኅረ ክርስቶስ የተጻፉ ባለ ሁለት ክፍል ነው። የመጀመሪያው ክፍል ብሉይ ኪዳን ይባላል። ይህንን ክፍል በቋንቋቸው በዕብራይስጥ ጽፈው የሰጡን አይሁድ ናቸው። ሁለተኛው ክፍል ሐዲስ ኪዳን ይባላል። የተጻፈው በጽርእ (በግሪክ ቋንቋ) ነው። በግሪክኛ ጽፈው የሰጡን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ናቸው።

ብሉይ ኪዳን በመሠረቱ የአይሁድ መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። ግን የክርስትና ሃይማኖት በብሉይ ኪዳን ላይ ስለተመሠረተ ፈላጊዎቹ እጅግ ብዙ ሆኑ። የአይሁድ ሃይማኖትም ምን እንደሆነ ለማወቅ ፈላጊው ስለበዛ፥ የዕብራይስጡን ብሉይ ኪዳን የግብፁ ግሪካዊ ገዢ (በጥሊሞስ ፊላዴልፎስ (285-246 ቅድመ ክርስቶስ) ሰባ (ሁለት) ሊቃናት ሰብስቦ ወደዓለም አቀፉ ቋንቋ ወደግሪክኛ አስተረጐመው። (ሕፃኑን ኢየሱስን በቤተ መቅደስ ያቀፈው ሽማግሌው ስምዖን ከሰባ ሊቃናት አንዱ ነበር የሚል ተአምር በእኛ ዘንድ ይነገራል።) አሁን እንግዲህ፥ ሐዲሱም ብሉዩም በግሪክ ቋንቋ ሊነበብ ቻለ። የግዕዙ መጽሐፍ ቅዱስ የተተረጐመው ከዚህ ከግሪኩ ቅጂ ነው። አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፥ “ኢትዮጵያ ብሉይ ኪዳኗን የተረጐመችው በቀጥታ ከዕብራይስጡ ነው” ይላሉ። ማስረጃቸው አርኪ አይደለም።

እነዚህ ሰባ (ሁለት) ሊቃናት ሲተረጉሙ፥ ዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን ውስጥ የሀገርና የሕዝብ ስም ሲያጋጥማቸው አንዳንዱን ዕብራይስጡ ውስጥ እንዳለው ይወስዱታል። አንዳንዱን፥ ለምሳሌ እንደ “ኹሽ” እንደ “ፍልስጥኤም” ያሉ ስሞችን እንዳለ በመውሰድ ፈንታ፥ የግሪክ ተመሳሳይ ስም ይሰጡታል። (ፍልስጤምን “ኢሎፍሊ”፥ ኩሽን “ኤይቲኦፕ” አሏቸው።) የዕብራይስጡ “ኩሽ” የሚያመለክተው ጥቁርን ሕዝብ ነው። ግሪኮች ደግሞ ጥቁሩን ሕዝብ የሚጠሩት “ኤይቲኦፕ” ብለው ስለሆነ፥ “ኩሽ” የሚለውን ስም “ኤይቲኦፕ” ቢሉት አይገርምም። ባጭሩ፥ ግሪኩ “ኤይቲኦፕ” የሚላቸው ዕብራይስጡ “ኩሽ” የሚላቸውን ሕዝቦች ነው። “ስልቻ” እና “ቀንቀሎ” እንደማለት ነው፤ ሁለቱ ቃላት በምን ይለያያሉ? እኛ ደግም፥ ከላይ እንደተናገርኩት፥ መጽሐፍ ቅዱሳችንን የተረጐምነው ከግሪኩ ስለሆነ፥ “ኤይቲኦፕ” የሚለውን “ኢትዮጵያ” አልነው። ከዕብራይስጡ ተርጕመነው ቢሆን ኖሮ ምናልባት “ኩሽ” (ኩሳ) እንለው ነበር። “አለቀ ደቀቀ። ፓስቶሩ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የዛሬ ስድሳ ሁለት ዓመት ባሳተሙት በግዕዝ መዝገበ ቃላታቸው ውስጥ “ኢትዮጵያ” የሚለውን ስም እንዴት እንደተቹት ቢያይ ኢትዮጵያና ኩሽ ትርጕማቸው አንድ ሆኖ የሚያመለክቱት ኢትዮጵያንና ሱዳንን መሆኑን እንደምናስተምር ይረዳ ነበር። …..  (Read more, pdf)

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.