እነ ንግስት ይርጋ የቀረበባቸውን “የሽብር” ወንጀል ክስ እንዲከላከሉ ተበየነባቸው

Source: http://welkait.com/?p=10901
Print Friendly, PDF & Email

በአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖችና ከተሞች ከሐምሌ ወር 2008 ዓ.ም ጀምሮ እጃቸው እስከተያዘበት ዕለት ህዝባዊ አመጽ በማነሳሳት፣ አመጹን በበላይነት በማስተባበርና በመምራት የሽብር ወንጀል ፈጽመዋል በሚል በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብር ክስ የቀረበባቸው እነ ንግስት ይርጋ ክሱን እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ህዳር 05/2010 ዓ.ም የአቃቤ ህግ ማስረጃዎችን መርምሮ ብይን የሰጠ ሲሆን፣ እነ ንግስት ይርጋ (ስድስቱም ተከሳሾች) በአቃቤ ህግ የቀረበባቸውን የጸረ ሽብር አዋጅ 652/2001 አንቀጽ 3(4 እና 6) የተመለከተውን መተላለፍ የወንጀል ድርጊት እንዲከላከሉ ሲል ፍ/ቤት በይኗል፡፡

ፍ/ቤቱ በአቃቤ ህግ በኩል በሰው ምስክርነት ከተዘረዘሩት ሰባት ምስክሮች መካከል ሁለቱን ብቻ በ3ኛ ተከሳሽ አቶ ቴዎድሮስ ተላይ ላይ ቀርበው መስማቱን አስታውሶ፣ ቀሪ ምስክሮችን አቃቤ ህግ በተያዘለት ቀጠሮ ባለማቅረቡ ሳይሰሙ በመታለፋቸው፣ ፍ/ቤቱ በሰው ምስክር ማስረጃነት የመረመረው የሁለት ምስክሮችን ቃል ብቻ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል ግን ፍ/ቤቱ በአቃቤ ህግ የቀረቡለትን የሰነድ ማስረጃዎች፣ ማለትም፣ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ሪፖርት፣ የእያንዳንዳቸው ተከሳሾች ለፖሊስ የሰጡት የተከሳሽነት ቃል፣ እንዲሁም ከንግድ ባንክ የተላከ የሰነድ ማስረጃና የሰላም ባስ አክሲዮን ማህበር በጎንደር ከተማ አንድ አውቶብስ በግለሰቦች በተቀሰቀሰ አመጽ ምክንያት እንደተቃጠለበት የሚገልጽ ሰነድ፣ በማስረጃነት ቀርበውለት እንደመረመራቸው ችሎቱ ግለጹዋል፡፡

በዚህም ‹‹ችሎቱ ማስረጃዎችን ሲመረምር እንዳረጋገጠው፣ አቃቤ ህግ እንደክስ አቀራረቡና በክሱ ላይ በጠቀሰው የህግ ድንጋጌ አግባብ ሁሉም ተከሳሾች የአርበኞች ግንቦት ሰባት የሽብር ቡድን ውስጥ አባል በመሆን፣ የገንዘብ ድጋፍ በመቀበል ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው በማስረጃ ማስመስከሩ/ማስረዳቱን ተግንዝቧል›› በማለት ዳኞቹ በሙሉ ድምጽ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ መወሰናቸውን ገልጸዋል፡፡
ፍ/ቤቱ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት የተላከው ሰነድም ሆነ ተከሳሾች ለፖሊስ የሰጡት የተከሳሽነት ‹የእምነት› ቃል በክሱ ላይ እንደተመለከተው በጸረ ሽብር አዋጁ አንቀጽ 3(4 እና 6) በመተላለፍ በፈጸሙት አመጽን ማነሳሳት፣ አመጹን በበላይነት መምራትና ማስተባበር ወንጀል ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የመንግስትና የግል ንብረት ውድመት ማድረሳቸው ሲታይ የፈጸሙት የሽብር ወንጀል ከፍተኛ ሊባል የሚችል ስለሆነ፣ ተከሳሾቹ በክሱ ላይ የተመለከተውን የወንጀል ድርጊት እንዲከላከሉ ሲል ብይኑን ሰጥቷል፡፡
የተከሳሽ ጠበቆች ከብይኑ መደመጥ በኋላ በሰጡት አስተያየት ችሎቱ በአቃቤ ህግ ማስረጃ ላይ ጠበቆቹ የሰጡት የሰነድ ትችት አስተያየት ሳይመረመር እንደታለፈባቸው በመግለጽ ችሎቱን ጠይቀዋል፡፡ ችሎቱ በበኩሉ በብይኑ ሳይካተት ታልፎብናል የምትሉት ነጥብ ካለ ወደፊት በሚኖረው ክርክር ሂደት አያይዛችሁ ማሰማት ትችላላችሁ ሲል መልስ ሰጥቷል፡፡
በእነ ንግስት ይርጋ መዝገብ የተካተቱትና ክሳቸውን ተከላከሉ የተባሉት ተከሳሾች፣

1. ወ/ት ንግስት ይርጋ
2. አቶ አለምነህ ዋሴ
3. አቶ ቴዎድሮስ ተላይ
4. አቶ አወቀ አባተ
5. አቶ በላይሁን አለምነህ፣ እና
6. አቶ ያሬድ ግርማ፣ ናቸው፡፡
ፍ/ቤቱ የተከሳሾችን የመከላከያ ማስረጃ ለማድመጥ በሚል ለታህሳስ 12 እና 13/2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል፡፡

ምንጭ:- Ethiopia Human Rights Project

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.