እንኳን ለገናናው ንጉሥ ዳግማዊ ቴዎድሮስ 200ኛ አመት የልደት በአል አደረሳችሁ!

Source: http://welkait.com/?p=11543

እንኳን ለገናናው ንጉሥ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ልደት አደረሳችሁ!

ባየ ተሻገር (ነአኩቶለአብ)

አሁን ሁሉም እየተነሳ አንድነት እያለ የሚያላዝንባትን እና ፋሺስት ወያኔ በጠብመንጃ ቀንበር ስር ወድሮ የሚገዛትን ኢትዮጵያ የፈጠራት ዐማራው ነው፤ ‘ከኋላ የመጣ አይን አወጣ’ ሆኖ በደረስንበት እንድንገፋና እንድንገደል ተፈረደብን እንጅ ሃገሯን የመሰረቷት የእኛው አያቶች ናቸው። በዚህች አጭር ጽሁፍ ውስጥ ማስተላለፍ የፈለኩት ግን የኢትዮጵያን አመሰራረት ሳይሆን ኢትዮጵያ እንዳሁኑ በፖለቲካ አዘቅት ወስጥ በገባችበት ጊዜ አያቶቻችን ከወሰዱት እርምጃና ከተከተሉት መንገድ መማር የሚጠበቅብንን ለመጠቆም ነው።

“ዘመነ-መሳፍንት” ተብሎ በሚጠራውና ወደ 70 ዓመት ገደማ በዘለቀው ጊዜ ኢትዮጵያ በአካባቢያዊ መኳንንቶችና መሳፍንቶች ስር ወድቃ አንድነቷ ተናግቶ ነበር። በጊዜው ለነበረው የፖለቲካ ውጥንቅጥ ዕልባት የሰጡት ቋረኛው ካሳ ወይንም ገናናውና ጀግናው ንጉሥ ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ናቸው።

አፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ሲያስቡ የጀመሩት በደፈናው አንድነትን በመዝፈንና ቀቢፀ-ተስፋን በመንዛት አይደለም፤ ብሔር ብሔረሰብን በመሰብሰብ 87ቱ እያሉ በመንበዛበዝም አይደለም። ይልቁን #አካባቢያቸውን_መሰረት_ያደረገ ተከታታይነት ያለው #ተሸጋጋሪ_ድልን በማሰብ ነው። በመጀመሪያ ቋረኛው ካሳ ቋራንና አካባቢውን በደንብ ማስተዳደራቸውን ሕዝቡም በእርሳቸው ገዥነት ማመኑን አረጋገጡ። ጉዳዩ በዘመኑ የነበሩትን የጎንደር ገዥዎች ስለአስደነገጠ ነገሩን በቤተሰብ ፖለቲካ ወይንም በጋብቻ ገመድ አስክኖ ለመፍታት በማሰብ የራስ ዓሊ እናት እቴጌ መነን የልጅ ልጃቸውን ወይዘሮ ተዋበችን አጋቧቸው፤ ቋረኛው ካሳ ሚስታቸውን ይዘው ሸፈቱ። በደጃች ወንድይራድ ተፈትነው ያለፉት ቋረኛው ካሳ እቴጌ መነንን ድል አድርገው በድርድር ደንቢያ ተጨምሮላቸው ግዛታቸው ሰፋ። ቀጣይ ባለተራ ደጃች ጎሹ ነበሩ፤ ድል የለመዱት ቁረኛው ካሳ አካባቢያዊ ገዥዎችን ማንበርከኩን ቀጠሉበት። ይሁን እንጅ ሁለት ሶስት አገረ-ገዥዎች ተቧድነው ሲመጡባቸው መውጫ መግቢያውን ወደሚያውቁት ቋራ የሸሹበት ጊዜ ነበር፤ ጨርሰው ሄደዋል ብለው የተቧደኑት ሲለያዩ ቋረኛው ካሳ ተመልሰው አንድ በአንድ እየገጠሙ እያጠቁ ድል በድል ሆኑ። በዚህ አካሄድ ደጃች ውቤን ደረስጌ ላይ ወግተው እንደ ደንቡ ተቀብተው ንጉሰ-ነገሥት ሆኑ። የጎጃምንም፣ የወሎንም የሸዋንም ነገስታት ድል ነስተው መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያንም ከዘመነ-መሳፍንት መንጋጋ መንትፈው አላቀቋት። በኋላ ላይ እምዬ ምኒልክ የአጼ ቴዎድሮስ ፈለግ በመከተል ከጥንታዊዋ አብሲኒያ ይዞታ ውስጥ አሁን ኢትዮጵያ ብለን የምንጠራትንና ኤርትራን ጭምር ያካተተውን አገር በማዕከላዊ መንግስት ስር አፀኑ።

እንግዲህ ከታሪኩ እንደምናየው አፄ ቴዎድሮስ ከሸዋ ወይንም ከወሎ ወይንም ከጎጃም አልጀመሩም፣ የጀመሩት ከአካባቢያቸው ከቋራ ነው፤ #ጉልበት_እያገኙ_እና_እየተደራጁ ሲሄዱ ግን ዐማራውን በሙሉ አስገብረው እንደቀድሞው አንድ አደረጉት።

አሁን ለምናዬው ውጥንቅጥም መፍትሔው በተመሳሳይ መንገድ መሔድ ነው። ቅድሚያ አማራውን ማንቃት፣ በአማራዊ ድርጅት ስር ማደራጀት፣ እራሱን እንዲከላከል አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ነው። ይህ እንግዲህ ዘመን በሻረው አኳኋን የራስህን ወገን በጦር መሳሪያ በማስገበር አይሆንም፤ ይልቁን የወሎን፣ የሸዋን፣ የጎጃምንና የጎንደርን እንዲሁም በተለያዬ አካባቢ ተበትኖ የሚገኘውን አማራ ጥንተ-መሰረትና አንድ አማራ ማንነት በመግለጥና በማስረዳት እንጅ፤ ባሳለፍነው ሩብ ምዕተ-ዓመት አማራው በአማራነቱ ብቻ ያሳለፈው መከራ ጥሩ አድርጎ ስለመከረው
ማንቃቱ ምንም ያህል ጊዜም አይወስድም እንዲያውም ትንታጉ አዲስ ትውልድና አስትዋዩ ነባር ትውልድ ተደጋግፈው አማራው በማንነቱ የመሰረተውን ብሔርተኛነት የማይነቃነቅ መሰረት ላይ ተክለውታል።

አማራው ተደራጅቶ፣ ታጥቆና ተሰልፎ ሲነሳ የዛን ጊዜ ስለአንድነት ማውራት ተገቢ ሊሆን ይችላል፤ የአማራው ሕዝብ ፈቃድ ከሆነ አንድነቱን ይቀበላል ካልሆነ ይተወዋል። አሁን ግን አንድነት እያለ የሚሰብክ ቡድን ያለ እንደሆን ለጊዜው ጆሮ ነስቶ አድፍጦ የቤት ስራን መስራት አማራዎች ሁሉ ዓይነተኛ ምርጫችን ልናደርገው ይገባል።

በማጠቃለያ አፄ ቴዎድሮስ ከቋራ ተነስተው አማራውን ከእርስበርስ ውጊያና ከታላቅ ጥፋት ታደጉት በማንነቱ መሰረት እጅ-ለ-እጅ አያያዙት፤ የእፉኝት ልጆች ተነስተው ዳግም ማዕከላዊ መንግስቱን እንኪበጠብጡ ድረስ የታፈረችና የተከበረች አገር ባለቤት አድርገውን ለዘለዓለም በማንነታችን እንድንኮራ #በፊተኛው_መሰረት_ላይ_ማገር_አድርገው በጥብቅ አሰሩት። እንግዲህ ጊዜው ዳግም ዘንብሎ አማራው ሕልውናው ጭምር ፈተና ውስጥ በወደቀበት ሰዓት በታሪክ መስታዋት ወደኋላው ዞሮ ማየት ግዴታው ነው፤ ታሪኩም #ቅድሚያ_ራስህን_አድን#አማራነትህን_አጽና ይላልና እናስተውል።

ድል ለዐማራ ሕዝብ!

ባየ ተሻገር (ነአኩቶለአብ)

#ልሣነ_ዐማራ
#AmharaPress

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.