“እኛን አባልተው ስንዳከም ሊበሉን ላቆበቀቡ የቀን ጅቦች ዕድል አንስጣቸው!” ዶ/ር አቢይ

Source: http://amharic.abbaymedia.info/archives/44675

ከአንደበታቸው ሁል ጊዜም መልካም ቃላትን ብቻ ማዝነብን የለመዱት ጠሚር ዐቢይ አሕመድ፥ በዛሬው ዕለት ለእስላም ወንድሞቻችን የእንኩዋን አደረሳችሁ መልዕክት ለማድረስ በቴለቪዥን መስኮት ቀርበው ነበር። ከአረብ ኤምሬትስ ከመጡባቸው እንግዳ ጋር በመቆየታቸው መልዕክቱን ለማስተላለፍ መዘግየታቸውን ገልፀዋል። ጠ/ሚሩ ሲያደርጉ በነበረው የዲፕሎማሲ ተግባር የውጭ ምንዛሪውን ችግር ሊያቃልል የሚችል ድጋፍ ማግኘታቸውን አብስረዋል።
በአዋሳ፥ በወላይታ ሶዶና በወልቂጤ  ግጭቶች መከሰታቸውን በሀዘኔታ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ተምሳሌት ሆኖ በሚጠቀሰው የደቡብ ክልል ይህ በመሆኑ ማዘናቸውን አልደበቁም። ለሠላሙ መደፍረስ ምክንያቶቹ መታየት ላይ ባለው ለውጥ ያልተደሰቱ ወገኖች መሆኑን አጋልጠዋል። የሳቸው በማይመስል ቃል “የቀን ጅቦች!” ብለው የጠቀሱዋቸው ወገኖች አልተሳካላቸውም እንጂ የሃይማኖት ግጭቶችን ለመቀስቀስም ከጅለው እንደነበር ገልፀዋል።
በሁሉም አካባቢዎች የድንበር ጥያቄዎች አሉ ያሉት ጠ/ሚ/ር፥ በክልሎች መካከል ያሉት መለያዎች ድንበር ሳይሆኑ አርተፊሻል የአስተዳደር መለያዎች መሆኑን ጠቅሰዋል። ማንም ሰው በየትም ቦታ ያለከልካይ መዘዋወር መኖርና መስራት እንደሚችል ሕገመንግስቱን በመጥቀስ ተናግረዋል። ችግሩን ከመሠረቱ በአገር ደረጃ ዕውቀትን ተንተርሶ ለመፍታት ኮሚሽን እንደሚቁዋቁዋምና ጥናት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
በሚቀጥለው ሣምንት ከሕዝብ ጋር ለመወያየት ወደ ደቡብ እንደሚያቀኑ ተናግረዋል። እስከዛው ግን ጥያቄዎችን በሠለጠነና በሠላማዊ መንገድ መጠየቅ እንደሚቻል ጠቁመው ኅብረተሰቡ ለሠላም ዘብ እንዲቆም ተማፅናዋል።
አያሌ ሰዎችን በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን ጠይቀናቸው ነበር። አስተያየታቸው ጠቅለል ሲደረግ “ከዐቢይ ጎን ቆመን ካልተረባረብን (የሳቸውኑ ቃል በመጠቀም) የቀን ጅቦቹ ለአብዲ ኢሌ ይዳርጉናል የሚል ነው!” “ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለራሥህ ስትል ተነሥ!” የሚሉ በዝተዋል።

Share this post

2 thoughts on ““እኛን አባልተው ስንዳከም ሊበሉን ላቆበቀቡ የቀን ጅቦች ዕድል አንስጣቸው!” ዶ/ር አቢይ

  1. kuchiye

    @SelamLeEth ለጅቦቹም ላገር ወዳዶችም በቅጡ የተቀመመ መልዕክት! የለመድነው “እደመስስሀለሁ!” ፍካሬስ? በቃ ቀረ?

    Reply

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.