ከመኖሪያ ቀያቸው ከተፈናቀሉ ሕፃናት ከመቶ ግማሹ የትምሕርት እድል አያገኙም ተባለ

Source: https://mereja.com/amharic/v2/142553

በስደተኛ የመጠለያ ጣቢያዎች ከሚገኙ ህፃናት መካከል ከግማሽ በመቶ በላዩ የትምህርት ዕድል አያገኙም ተባለ፡፡
በዓለማችን በተለያዩ ምክንያቶች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ከሚኖሩ ህፃናት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የትምህርት እድል እንደማያገኙ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን UNHCR አስታውቋል፡፡
በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናት ከትምህርት ዕድል ውጭ ሆነዋል ብሏል ተ.መ.ድ በጥናቱ፡፡ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ያላቸው ሀገራት በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ የሚኖሩ ህፃናት የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ የሚያስችል ፖሊሲ ነድፈው እንዲሰሩም ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡

እንደ ተ.መ.ድ ዘገባ በዓለም ላይ የሚገኙ እና እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ 7 ነጥብ 1 ሚሊዮን ህፃናት የትምህርት እድል እያገኙ አይደለም፡፡
ከ10 ስደተኛ ህፃናት መካከል ስድስቱ ብቻ የመጀመሪያ ደረጃ የትምህርት ዕድል ያገኛሉ ያለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአንፃሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውጭ ካሉ 10 ህፃናት መካከል ዘጠኙ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህር እንደሚያገኙም አመላክቷል፡፡ በተመሳሳይ ከ10 ስደተኛ ተማሪዎች ውስጥ ሁለቱ ብቻ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንደሚያገኙ ሲያመላክት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከስደተኞች ውጭ ያሉ ከ10 ታዳጊዎች መካከል ስምንቱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት እንደሚያገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ ብሏል፡፡
በተለይም በሦስተኛው የዓለም (በድሀ) ሀገራት በሚገኙ ስደተኞች ችግሩ የከፋ ነው ያለው ተ.መ.ድ ያደጉት ሀገራት በተለይም በአውሮፓ በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ህፃናት መደበኛ ትምህርት እንዲያገኙ የሚያደርጉት ጥረት አበረታች ቢሆንም በቂ ግን አይደለም ብሏል፡፡
ምንጭ፡- ሲ ጂ ቲ ኤን

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.