ከንቲባ አበበ ተካልኝ በመኖሪያ ቤታቸው ደጃፍ ላይ ተገደሉ

Source: https://mereja.com/amharic/v2/147309

በምዕራብ ወለጋ የምትገኘው የጉሊሶ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ ተካልኝ በመኖሪያ ቤታቸው ደጃፍ ላይ በታጣቂዎች ተገደሉ።
BBC Amharic :
ከተማዋን ላለፉት ጥቂት ወራት ያስተዳደሩት የከንቲባው ሥርዓተ ቀብር ትናንት መፈጸሙም ተነግሯል።
አቶ አበበ ዕሁድ ምሽት ላይ ከመኖሪያ ቤታቸው ውጪ በታጣቂዎች መገደላቸውን የጉሊሶ ወረዳ የአስተዳደር እና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋ ሊካሳ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
“ደጃፋቸው ላይ በሁለት ጥይት ግንባራቸውን ተመትተው ነው የተገደሉት” ሲሉ የጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊው ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹ ከንቲባውን ደጃፋቸው ላይ ከገደሉ በኋላ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ዘልቀው በመግባት “ለስብሰባ የተዘጋጀ ጽሑፍ እና የአካባቢውን ባለስልጣናት ስም ዝርዝርን የያዘ ላፕቶፕ ኮምፒዩተር ይዘው ሄዱ” ሲሉ አቶ ተስፋ ጨምረው ተናግረዋል።
ከንቲባውን ገድለው ላፕቶፕ ዘርፈው ሄዱ የተባሉት ታጣቂዎች በቁጥር ወደ ስድስት እንደሚጠጉ የሟች የቤተሰብ አባላት ለመንግሥት የጸጥታ አካል መናገራቸውም ተገልጿል።
ግድያው እንዴት ተፈጸመ?
ጥቃቱ በተፈጸመበት ምሽት የሁለት ልጆች አባት የነበሩት ከንቲባ አበበ ተካልኝ እሁድ ምሽት ላይ ከልጆቻቸው ጋር ቴሌቪዥን እየተመለከቱ ላፕቶፓቸው ላይ እየጻፉ ነበር።
አራት ሰዓት ገደማ ላይ ከንቲባውን የሚፈልግ ሰው ከውጪ እንደተጣራና 10 ዓመት የማይሞለው ልጃቸው ወደ ውጪ ሊወጣ ሲል አባት ልጅን ከልክለው እንደወጡ ደጃፋቸው ላይ በሁለት ጥይት ግንባራቸውን ተመትተው መገደላቸውን የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ተስፋ ለቢቢሲ አስረድተዋል። ከዚህ ቀደምም በምዕራብ ኦሮሚያ በነዋሪች ላይ ከሚፈጸሙ ጥቃቶች በተጨማሪ፤ የአካባቢው ባለስልጣናት የታጣቂዎች ኢላማ ሆነው ቆይተዋል። ከጥቂት ወራት የቄለም ወለጋ ዞን የደህንንት እና የኦዲፒ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ግለሰብ ተገድለዋል።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.