ከአበበ ካሴ ከእስር ቤት ለኢትዮጵያ ኒው ዮርክ ኒው ጀርሲ ግብረ ኃይል የደረሰ የሰቆቃ ደብዳቤ

Source: http://amharic.abbaymedia.info/archives/41308

ስም አበበ ካሴ

እድሜ 41

አድራሻ ሰሜን ጎንደር / አርማጭሆ

አሁን በእስር የምገኝበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት

ጥር 12/2006 ዓ.ም ከተያዝኩ በኋላ ወደማዕከላዊ ወሰዱኝ። በማዕከላዊ እስር ቤት ከ5 ወር በላይ ታስሬአለሁ። ከዚህ መካከል 4 ወር ከ25 ቀናት በጨለማ ቤት ተቆልፎብጭ ቆይቻለሁ።ማዕከላዊ በነበርኩበት ወቅት የሁሉም እግርና እጆቼ ጥፍሮች ተነቅለዋል። አንዳንድ ቀን እጄ ላይ የሆነ ነገር ስለሚወጉኝ ጥፍሮቼ ሲነቀሉ አላውቅም። ስነቃ ነው መነቀላቸዉን የማዉቀው። ከዛም ቁስሉን እየነካኩ ያሰቃዩኛል። ማደንዘዣ ለምን እንደሚወጉኝ አላውቅም። ጥፍሮቼን ሲነቅሉኝ ብቻ ሳይሆን ሌላ ጊዜም እራሴን እንድስት ያደርጉኛል። እጅና እግሬን አስረው እጅግ በጣም በሚቀዘቅዝ ቦታ ዉስጥ ያስቆሙኛል። ለብዙ ሰዓት በጣም ቀዝቃዛ የሆነ ቦታ ላይ እስክደነዝዝ ቆሜ እዉላለሁ። እስከሚበቃቸው ከደበደቡ በኋላ እጅና እግሬን አስረው ከምርመራ ክፍሉ በታች በሚገኝ ምድር ቤት ክፍል ዉስጥ ያለ ጉድጓድ ላይ ጥለዉኝ ይሄዳሉ። ጉድጓዱ ጉንዳንን  ጨምሮ ተባዮች ያሉት ነው። ከዚህ በተጨማሪ እጄንና እግሬን አስረው ዘቅዝቀዉኝ ይሄዳሉ። የመጣው ሁሉ ዥዋዥዌ እንደሚጫዎት ህፃን ወዲያና ወዲህ ያደርጉኛል። ገልብጠው አስረው ሲዘቀዝቁኝ በአብዛኛው ራሴን እስታለሁ። እግርና እጄን ከወንበር ጋር ያስሩኛል።

ከወንዶች በተጨማሪ ሴቶችም ይመረምሩኛል። ሴቶቹ የሚመረምሩኝ እራቁቴን አድርገው ነው። እነርሱም እራቁታቸዉን ሁነው ነው የሚመረምሩኝ። አሁን ለመናገር የማልደፍረው አፀያፊ ነገርም ፈፅመዉብኛል። ይህን አፀያፊ ነገር የሚፈፅሙት አደንዛዥ እፅ እየተጠቀሙ ነው። ይህን ሲያደርጉ በዐይኔ አይቻቸዋለሁ። መርማሪዎቹ ሰዉነቴን በኤሌክትሪክ አቃጥለዉኛል። ኤሌክትሪኩን የሚሰኩት ደረቴና የዉስጥ እግሬ ላይ ነዉ። በዚህም የዉስጥ እግሬ ተገልብጦ ሌላ ሰዉነት አምጥቶ ነበር። እጄን ወደላይ አስረው ብልቴ ላይ ሀይላንድ አንጠልጥለውበታል። ሴቶቹ ሀይላንዱን የሚበቃቸዉን ያህል ያወዛዉዙታል። በዚህም ምክንያት የዘር ፍሬየን ከጥቅም ዉጭ አድርገው ዘሬን እንዳልተካ አድርገውኛል። ሽንቴንም መቆጣጠር አልችልም ነበር።  ይህን ያህል አሰቃይተው ከጥቅም ዉጭ ስሆን ቂልንጦ ወስደው ጣሉኝ። 11 ወር ያህል አልጋ ላይ ነበርኩ። በኤሌክትሪክ ግርፊያው ምክንያት ግራ ሰዉነቴ ሽባ ሁኖ ነበር። ግራ እግሬም መንቀሳቀስ አይችልም ነበር። በምርኩዝ ነበር የምሄደው። ለረጂም ጊዜ እያነከስኩ ነበር የምሄደው።

በተለይ ማዕከላዊ ዉስጥ ይህን ያህል ያሰቃዩኝ ምክንያቱ አንደኛ አብረው ስለነበሩት ጓዶቼ እንዲሁም ስለ ድርጅቱ(አርበኞች ግንቦት7)ሚስጥር እንድሰጣቸው ነው። በሁለተኛ ደረጃ የሚአሰቃዩኝ የት የት ቦታ ነው የሰለጠንከው እያሉ ነው።

ቂሊንጦ  ከገባሁ በኋላም ያሰቃዩኝ ነበር። ወጣቶች እንዳይቀርቡኝ ያስፈራሯቸዋል። ማንም ጠርቶ እንዳይጠይቀኝ ተደርጓል። ጨለማ ክፍል ወስደውም አስረዉኝ ያዉቃሉ። እነሱ ደብድበው ከጥቅም ዉጭ ካደረጉኝ በኋላ የምደገፍበትን ምርኩዝም ቀምተውኛል። ቂሊንጦ በነበርኩበት ክፍል ዉስጥ እንድተኛበት የተሰጠኝ ቦታ ሽንት ቤት አጠገብ ነው። ሽንት እየሸተተኝ እተኛ ነበር። ወደሌላ ቦታ ቀይሩኝ ስላቸው ደግሞ “ለአንተ ይህ አንሶህ ነው?” ይሉኛል። ያ ሁሉ ድብደባ ደርሶብኝ አልጋ ላይ በነበርኩበት ወቅት ወጣቶች ህክምና እንዳገኝ ወደ ሀኪም ቤት ወሰዱኝ። እነሱ ግን “ለአንተ ህክምና ሳይሆን ጥይት ነበር የሚገባህ” ብለው መለሱኝ። እንዲህ እያሉ ለምን እንደማይገድሉኝ ይገርመኛል። አሁን በምገኝበት በቃሊቲ ማጎሪያ ቤት ለብዙ ጊዜ በጨለማ ቤት አስረዉኝ ነበር። ከዚያ ካስወጡኝ በኋላም ግብረሰዶም ፈፃሚዎች ከሚገኙበት ቦታ አብረው አስረዉኛል።

ይህ በእኔ ላይ የሚፈፀመው በደል ሁሉ ሆን ብለው ነው። አንድም በቀል ነው። ሁለተኛም የአካልና የዐእምሮ ሰቆቃ በኔ ላይ ለመፈፀም ነው።

ይህ የደረሰብኝ በደል ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት በመታገሌ ነው። ይህን ህዝቡ ሊያውቅልን ይገባል። ይህ ሁሉ ግፍ የሚፈፀምብን ሀገራችንን ባልን ነው። እኔ ለመሞት ነበር በረሃ የገባሁት ነገርግን እግዚአብሄር ያዘዘልኝ ይህ ነዉና ሁሉንም እቀበላለሁ። እኛ እስረኞች ይህ ሁሉ በደል እየተፈፀመብንም ጠንካሮች ነን። ያ ወኔያችን ከእኛ ጋር ነው። እኛ ተስፋ አንቆርጥም።

Share this post

Post Comment