ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከገጠማቸው ችግር እንዲወጡ ሁሉንም ያሳተፈ ውይይት ማድረግ እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ

Source: https://fanabc.com/2019/11/%E1%8A%A8%E1%8D%8D%E1%89%B0%E1%8A%9B-%E1%8B%A8%E1%89%B5%E1%88%9D%E1%88%85%E1%88%AD%E1%89%B5-%E1%89%B0%E1%89%8B%E1%88%9B%E1%89%B5-%E1%8A%A8%E1%8C%88%E1%8C%A0%E1%88%9B%E1%89%B8%E1%8B%8D-%E1%89%BD/

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 8 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በህብረ ብሄራዊነት የመኖር ምልክት የሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከገጠማቸው ችግር እንዲወጡ ሁሉንም አካላት ያሳተፈ ውይይት ማድረግ እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የፌደራሊዝም ምሁራን እንዳሉት፥ አሁን ላይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚስተዋለው ችግር ወቅታዊው የፖለቲካ ዋልታ ረገጥ አስተሳሰብ ያመጣው ውጤት ነው።

መንግስትም በተማሪዎች የአብሮነት አስተሳሰቦችን ለማሳደግ ኢትዮጵያዊ አንድነትና ስለ ሰላም ሊያስተምር ይገባል ነው ያሉት።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝም ጥናት እጩ ዶክተር ከድር ማሞ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች አብሮ የመኖር እሴት የሚታይባቸው መሆናቸውን ያነሳሉ።

የፌደራሊዝም ጥናት ረዳት ፕሮፌሰሩ ሀይለየሱስ ታዬ በበኩላቸው፥ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚታየው ችግር መንስኤ ከትምህርት ስርዓቱ እና ስልት ጋር የሚገናኝ መሆኑን ያነሳሉ።

አሁን ላይም በዩኒቨርሲቲዎች ከዚህ ቀደም ይታይ የነበረው ዴሞክራሲያዊና የነጻ አስተሳሰብ መጎልበት ሀሳቦች መጥፋቱንና ዋልታ ረገጥ አካሄድ እንደሚታይ እጩ ዶክተር ከድር ማሞ ይገልጻሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ጸጥታ ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዩናስ አደዬ አደቶ እንደሚሉት ደግሞ፥ አሁን ላይ ባለፉት አመታት የተዘራው የመጠራጠርና የጥላቻ ትርክት ፍሬ እየታየ ነው።

ምሁራኑ ከግጭት ይልቅ በሀሳብ ፍጭት የተሻለውን መርጦ ተግባራዊ ማድረግ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል ብለዋል።

መንግስትም የአጭር ጊዜ መፍትሄ ውይይትን አድርጎ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እንዲመለሱ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።

 

 

በሀይለየሱስ መኮንን

 

 

 

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.