ከ6 ወራት በፊት በምስራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ ተሽከርካሪ እንደተገጩና አካላቸውም እንደጎደለ የተናገሩት ግለሰብ እስካሁን ምንም ዓይነት ድጋፍ አልተደረገልኝም ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ። አማራ ሚዲያ ማ…

ከ6 ወራት በፊት በምስራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ ተሽከርካሪ እንደተገጩና አካላቸውም እንደጎደለ የተናገሩት ግለሰብ እስካሁን ምንም ዓይነት ድጋፍ አልተደረገልኝም ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ። አማራ ሚዲያ ማ…

ከ6 ወራት በፊት በምስራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ ተሽከርካሪ እንደተገጩና አካላቸውም እንደጎደለ የተናገሩት ግለሰብ እስካሁን ምንም ዓይነት ድጋፍ አልተደረገልኝም ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ። አማራ ሚዲያ ማዕከል/አሚማ መስከረም 17 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ሸዋ ከምስራቅ ጎጃም ዞን አዋበል ወረዳ ለአማራ ሚዲያ ማዕከል ቅሬታ ያቀረቡት ግለሰብ አቶ ሞሲዬ አላምረው ይባላሉ። አቶ ሞሲዬ አላምረው ነዋሪነታቸው በአዋበል ወረዳ እነዚጭፋር ቀበሌ መሆኑን ገልፀው ሚያዚያ 7 ቀን 2012 ዓ.ም በወረዳው ከወጀል ወደ እነዚጭፋር ቀበሌ የግራ መስመራቸውን ጠብቀው በእግራቸው እየተጓዙ ሳለ በድንገት ከሲኖትራክ ተደርቦ የመጣ ንብረትነቱ የምስራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ በሆነ ቶዮታ መገጨታቸውን ገልፀዋል። በደረሰው የመኪና አደጋም ሁለት እግራቸው እንደተጎዳ እና በአቅመ ደካማ እናታቸው እርዳታ አማካኝነት ወደ ደብረ ማርቆስ ሆስፒታል ተወስደው የህክምና እርዳታ እንደተደረገላቸው አውስተዋል። በህክምናውም የቀኝ እግራቸው አጥንት ሙሉ በሙሉ በመከስከሱ እንዲቆረጥ የተደረገ ሲሆን የግራ እግራቸውም ክፉኛ መጎዳቱን ነው አቶ ሞሲዬ የተናገሩት። ይሁን እንጅ ጉዳት ያደረሰባቸው የምስራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መኪና ሾፌር ዋና ሳጅን ደመላሽም ሆኑ ተቋሙን ከሚመሩትና በወቅቱ አብረው ከነበሩት ከምስራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ አዛዥ ከኢ/ር አያልነህ አንድም ሰብአዊ ድጋፍ አልተደረገልኝም፤ እስካሁንም ወንጀሉን የፈፀመው አካል ተገቢውን ህጋዊ ቅጣት አላገኘም ሲሉ የፍትህ አካሉን ይወቅሳሉ። የአማራ ሚዲያ ማዕከል ያነጋገራቸው የወረዳው ነዋሪ በቅርብ ሆነው ተጎጅውን እንዳናገሩና ተገቢ ፍትህ አለማግኘታቸውን እንደታዘቡ ገልፀው የሚመለከተው ሰብአዊነት የሚሰማውና የሚችል አካል ሁሉ ድጋፉን እንዲቸር ጠይቀዋል። ሌላው የተጎጅው የቅርብ ቤተሰብ አቶ ግርማ ታደሰ በበኩላቸው ተጎጅውን በመወከል እስከ ወረዳ፣ዞንና ክልል ባህር ዳር ድረስ በማቅናት ጉዳት አድራሹ አካል በህግ እንዲጠቅ ብዙ ጥረት ማድረጋቸውን አውስተው ነገር ግን እስካሁን አንድም ተጨባጭ እርዳታም ሆነ በህግ አግባብ የተቀጣ ሰው ያለማየታቸውን አሳዛኝ ሁኔታ አውስተዋል። የአዋበል ወረዳ ፖሊስ ጉዳዩን ሲከታተለው ነበር መባሉን ተከትሎ ለወረዳው ፖሊስ አዛዥ ለዋና ኢ/ር ፈንታሁን ደውለን ለማናገር ጥረት ብናደርግም ቅሬታውን ካደመጡ በኋላ ስልካቸውን በመዝጋታቸው ሀሳባቸውን ለማካተት አልተቻለም። በምስራቅ ጎጃም ዞን የአቃቢ ህግ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አበበ አወቀ በአቶ ሞሲዬ አላምረው ላይ የደረሰውን ጉዳት እንደሚያውቁና ኬዙን ይዘው ከዞን እስከ ወረዳ በተደራጀ አጣሪ ቡድን ሰፊ ምርመራ መደረጉን ተናግረዋል። የምርመራ ውጤቱም ጥቃቱ የደረሰው የምስራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስን ተሽከርካሪ በያዘ ሾፌር መሆኑን በማመልከቱ ተጠርጣሪ ዋና ሳጅን ደመላሽ ታስረው በዋስ እንደወጡ ነው አቶ አበበ የገለፁት። መዝገቡ ላለፉት 6 ወራት የዘገየውም የምስራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ ድርጊቱ በእኛ አልተፈፀመም ከማለት አልፎ የተለያዩ ቅሬታዎችን እያነሳ ስለነበር ቅሬታዎችን በአግባቡ ለመፍታት በሚል እንደሆነ አውስተው አሁን የጉዳዩ ፍሬ ነገር በወረዳ መታየት የሚችል በመሆኑ ለወረዳ አቃቢ ህግ መተላለፉን አስታውቀዋል። በቀጣይም ተጎጅው ግለሰብ ተገቢውን ፍትህ እንዲያገኝ ለማድረግ በአቃቢ ህግ ደረጃ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። የአማራ ሚዲያ ማዕከልም ግለሰቡ በተገጩበት ወቅት በመኪናው ተሳፍረው ነበሩ ለተባሉት ለምስራቅ ጎጃም ዞን የፖሊስ መምሪያ አዛዥ ለሆኑት ለኢ/ር አያልነህ ደውሎ ለማነጋገር ሞክሯል። በተጎጅም ሆነ በዞን አቃቢ ህግ የተነሱ ቅሬታዎችን ፈቅደው እንዲሰሟቸውና ምላሽም እንዲሰጡባቸው በሚል የተጠየቁ ቢሆንም ጉዳዩ በህግ የተያዘ በመሆኑ አስተያየት ለመስጠት እንደማይፈልጉ ነው የገለፁት። ኢ/ር አያልነህ ከአማራ ሚዲያ ማዕከል ጋር በነበራቸው አጭር ቆይታ ግን ተጎጅው ፍትህ እንዲያገኙ እንደሚፈልጉና በባለቤትነት እንደሚሰሩም አስታውቀዋል። #ከአቶ ሞሲዬ አላምረው፣ከአቶ ግርማ ታደለ፣ምስክርነት ከሰጡ ግለሰብ፣ከዞኑ አቃቢ ህግ ጽ/ቤት ኃላፊ ከአቶ አበበ አወቀና ከሌሎችም የፀጥታ አካላት ጋር የተደረገውን ቆይታ በአሚማ/AMC የዩቱብ አድራሻ የምናጋራ ይሆናል፤ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ወይም ምላሽ መስጠት ለሚፈልግ አካል ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ መሆናችን በመግለፅ ጭምር።

Source: Link to the Post

Leave a Reply