ከ600 በላይ የአማራ ተወላጆች ተፈናቀሉ

Source: https://amharic.ethsat.com/%E1%8A%A8600-%E1%89%A0%E1%88%8B%E1%8B%AD-%E1%8B%A8%E1%8A%A0%E1%88%9B%E1%88%AB-%E1%89%B0%E1%8B%88%E1%88%8B%E1%8C%86%E1%89%BD-%E1%89%B0%E1%8D%88%E1%8A%93%E1%89%80%E1%88%89/

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 28/2011) ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ከ600 በላይ የአማራ ተወላጆች ተፈናቅለው ባህርዳር መግባታቸው ተገለጸ።

ከካማሼ ዞን ያሶ ወረዳ የተፈናቀሉት የአማራ ተወላጆቹ በማንነታችን ላይ ያተኮረ ጥቃት እየተፈጸመብን ነው ብለዋል።

ፋይል

ለሶስት ወራት በጫካ ውስጥ ተደብቀው ከቆዩ በኋላ ህይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ባህር ዳር መምጣታቸውን ነው ለአማራ ክልል ብዙሃን መገናኛ ድርጅት የገለጹት።

ተፈናቃዮቹ ባህርዳር ሜዳ ላይ ወድቀን ቀርተናል የአማራ ክልል መንግስት ድጋፍ እያደረገልን አይደለም ሲሉም አማረዋል።

በቤንሻንጉል ጉምዝና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ላለፉት አምስት ወራት በተፈጠረው ውጥረት ከ100 ሺህ በላይ የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች መፈናቀላቸው የሚታወስ ነው።

ከካማሼ ዞን ያሶ ወረዳ፡ የአማራ ተወላጆች የድረሱልን ጥሪ መሰማት ከጀመረ ቆይቷል።

ለዓመታት ኑሮአቸውን በዚያው ያደረጉ፡ ወልደው ሃብትና ንብረት ያፈሩ የአማራ ተወላጆች ከጥቂት ወራት ወዲህ ግን ነገሮች ጥሩ ሊሆኑላቸው አልቻሉም።

ማንነታቸው እያስጠቃቸው፡ እያስገድላቸው መሆኑን ተከትሎ ቤት ንብረታቸውን ጥለው መሰደድ ብቻ ሆኗል ምርጫቸው።

ባለፉት ዓመታት በተመሳሳይ ከካማሼና ከሌሎች የቤንሻንጉል ጉምዝ አካባቢዎች በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች በደረሰባቸው ማንነት ተኮር ጥቃት መሰደዳቸው የሚታወስ ነው።

ሰሞኑን ከያሶ ወረዳ ተፈናቅለው ባህርዳር የደረሱት ከ600 በላይ የሚሆኑት የአማራ ተወላጆች በማንነታቸው የተነሳ የሚደርስባቸው ጥቃት እየጨመረ በመምጣቱ ህይወታቸውን ለማትረፍ ጫካ ተደብቀው ከቆዩ በኋላ ወደ አማራ ክልል መግባታቸውን ነው ለአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት የገለጹት።

የተገደሉም እንዳሉ ተፈናቃዮቹ ይናገራሉ።

ለወራት ከጫካ ከተደበቁ በኋላ ወደ ባህርዳር የደረሱት ተፈናቃዮቹ ባህርዳር ከደረሱ በኋላ የሚቀበላቸው አጥተው እየተንገላቱ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ምንም ያደረገልን ነገር የለም ሲሉም አማረዋል።

ባህርዳር ከደረሱ አምስት ቀናት የሆናቸው ቢሆንም እስከአሁን ድጋፍ እንዳላገኙ የሚገልጹት ተፈናቃዮች በከፍተኛ ችግር ላይ ነን ብለዋል።

የክልሉ መንግስት ለጊዜው በባህርዳር መጠለያ ባለመኖሩ ድጋፍ ለማድርግ መቸገሩን ገልጿል።

 

 

 

The post ከ600 በላይ የአማራ ተወላጆች ተፈናቀሉ appeared first on ESAT Amharic.

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.