ኮማንድ ፖስቱ የክልል የሥልጣን መዋቅሮችን መቆጣጠሩ ተጠቆመ

Source: http://www.yegnagudday.com/2018/03/10/%E1%8A%AE%E1%88%9B%E1%8A%95%E1%8B%B5-%E1%8D%96%E1%88%B5%E1%89%B1-%E1%8B%A8%E1%8A%AD%E1%88%8D%E1%88%8D-%E1%8B%A8%E1%88%A5%E1%88%8D%E1%8C%A3%E1%8A%95-%E1%88%98%E1%8B%8B%E1%89%85%E1%88%AE%E1%89%BD/

ኮማንድ ፖስቱ የክልል የሥልጣን መዋቅሮችን መቆጣጠሩ ተጠቆመ

ራሱን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈጻሚ እያለ የሚጠራው ኮማንድ ፖስት የክልሎችን የስልጣን መዋቅሮች ከጥቅም ውጭ አድርጎ እንደተቆጣጠረ ታወቀ፡፡

በተለይ አዋጁ ከጸደቀ በኋላ፣ በክልሎች የተዘረጋው የስልጣን መዋቅር በኮማንድ ፖስቱ ቁጥጥር ስር በመሆኑ፤ የክልል አስተዳዳሪዎች በኮማድ ፖስቱ ትዕዛዝ ስር እንደሚገኙ ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ፣ ኮማንድ ፖስቱ በተለይ ደግሞ በኦሮሚያ እና አማራ ክልል አስተዳዳሪዎች ላይ የበረታ ጫና እያሳደረ ሲሆን፤ በተዋረድ ያሉ የክልል ኃላፊዎች ከኮማንድ ፖስቱ እውቅና ውጭ ምንም ዓይነት መግለጫ መስጠት እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መመሪያ ላይ ‹‹የጸጥታ ጉዳይን በተመለከተ ክልሎች ከኮማንድ ፖስቱ እውቅና ውጭ ምንም ዓይነት መግለጫ መስጠት አይችሉም›› የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል አንቀጽ የሚገኝ ሲሆን፤ ይህ አንቀጽ የክልል ኃላፊዎች የክልላቸውን የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ ለሚዲያም ሆነ ለሌሎች አካላት መረጃ እንዳይሰጡ ያግዳል፡፡

እገዳው ከጸጥታ ጉዳዮች በተጨማሪም ኮማንድ ፖስቱ በየክልሉ የሚፈጽማቸውን ግድያዎች እና እስራቶች አስመልክቶም፣ የክልል ኃላፊዎች አስተያየትም ሆነ መግለጫ እንዳይሰጡ ይከለክላል፡፡

ከአዋጁ አፈጻጸም ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን አስመልክቶ የክልል አስተዳዳሪዎች ምንም ዓይነት መረጃም ሆነ አስተያየት መስጠት እንዳይችሉ ተደርገው፣ በኮማንድ ፖስቱ የአፈና ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ መረጃዎች አስረድተዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ታውጆ የነበረው አዋጅ፣ በዜጎች ላይ ካልሆነ በስተቀር በክልል አስተዳዳሪዎች ላይ ይሄን ያህል የስልጣን ገደብ እንዳልጣለ ያስታወሱ አስተያየት ሰጪዎች፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የታወጀው አዋጅ ግን ከህዝብ በተጨማሪም የክልል አስተዳዳሪዎች የክልላቸውን ሁኔታ አስመልክቶ መግለጫም ሆነ መረጃ እንዳይሰጡ የሚያዝ ሆኖ እንደተዋቀረ ይናገራሉ-አስተያየት ሰጪዎቹ፡፡

ፌደራላዊ ስርዓትን እከተላለሁ የሚለው አገዛዙ፣ በአዋጅ ስም ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበትን መብት ጥሶ፣ በአንድ ወታደራዊ ዕዝ ስር እንዲጠቃለሉ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አስተያየት ሰጪዎች አክለው ይገልጻሉ፡፡

አዋጁን ያስፈጽማል ተብሎ በተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ውስጥ ከሚገኙት አባላት፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እና መከላከያ ሚኒስትሩ ውጭ ሶስቱ የህወሓት ሰዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡

The post ኮማንድ ፖስቱ የክልል የሥልጣን መዋቅሮችን መቆጣጠሩ ተጠቆመ appeared first on Yegna Gudday.

Share this post

One thought on “ኮማንድ ፖስቱ የክልል የሥልጣን መዋቅሮችን መቆጣጠሩ ተጠቆመ

  1. ANDM and OPDO have instruments to avoid the role of the command post. All they need to do is call for Parliament session and get the emergency decree lifted. How? ANDM and OPDO should alert their respective parliamentarians and ask them to vote for lifting it.

    Reply

Post Comment