ዘመን ተሻጋሪ የኢትዮጵያ ችግሮች እና የልሂቃን ክፉ እሳቤዎች፤(ያሬድ ኃይለማርያም)

Source: https://mereja.com/amharic/v2/145816

መቼ ይሆን ሸክማችን ቀለል ብሎን ዘመን የምንሻገረው?
እኛ ዘመንን፣ ችግሮቻችን ደግሞ እኛን እየተከተሉ የአብሮነት ጉዟችን እንደቀጠለ ነው። ዘመን ሲታደስ የማይታደሱት ክፉ እሳቤዎቻችን አብረውን ከአንድ ዘመን ወደ ሌላ ዘመን እላያችን ላይ እየተንጠላጠሉ ተሻግረው እድሜያችንን እድሜያቸው አድርገው አብረውን ይኖራሉ። አንዳንዴም የእኛ እድሜም ሲያበቃም እነሱ የልጅ ልጆቻችንን ዘመን እና እድሜ ዘመናቸው አድርገው እንደ ውርስ ትውልድ እየተሻገሩ አብረውን ይዘልቃሉ።
እኛም የወላጆቻችንን ብቻ ሳይሆን የአያቶቻችንን ችግሮች እንኖራቸዋለን። ቅም ቅም አያቶቻችን በሬ ጠምደው በባዶ እግራቸው ያርሱ ነበር። ዛሬም የልጅ ልጆቻቸው በተመሳሳይ መልኩ በሬ ጠምደው እና በባዶ እግሮቻቸው ሆነው እሾህና ጋሬጣ እየወጋቸው በተመሳሳይ ሁኔታ ያርሳሉ። ትላንት ሴት አያቶቻችን ቅጠል ለቅመው፣ በጭስ ታፍነው እንጀራ እየጋገሩ እና ሽሮ አንተክትከው ያበሉን ነበር። ዛሬም የልጅ ልጆቻቸው ያንኑ ህይወት ይኖሩታል። በሌሎች ህይወታችንም እንዲሁ ነን። ትላንትን ዛሬ አድርገን የምንኖር ጉዶች። ዛሬያችን ነገን እንዲያጨልም እንቅልፍ አጥተን የምናድር ልዩ ፍጡሮች።
የአያት፣ ቅድመ አያቶቻንን እድሜ እና ጉልበት እንክት አድርገው የበሉ ችግሮች ዛሬም የእኛን እድሜ እያገባደዱና በልጅ ልጆቻችን እድሜ እየቋመጡ አዲስ ዘመን አብረውን ተሻግረዋል። በአያቶቹ ችግር የሚማቅቅ ትውልድ ካለ እሱ ከለውጥ የራቀ እና ከሳይንሳዊ እውቀት የተጣላ የስልጣኔ ድኩማን ነው። በሰለጠነው አለም በአያቶቹ አይደለም በአባት እና በእናቱ ወይም በታላላቆቹ ችግር የሚማቅቅ ሰው የለም። በካቻምና ችግር ዛሬ የሚያለቅሰ ማህበረሰብ እንደኛ ገልቱ ካልሆነ በቀር የለም። ትላንት ችግር የነበሩ ነገሮች ሁሉ በአዳዲስ መፍትሔዎች ተውጠው እድሜያቸው ባጭሩ ይቀጫል። ዘመን የሚሻገሩ ችግሮች የሏቸውም።

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.