የህወሃት አገዛዝ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ብዛት ያላቸው የታጠቁ ወታደሮችን እያጓጓዘ መሆኑ ታወቀ

Source: http://amharic.abbaymedia.com/archives/30711

በአራቱም ማዕዘን በውጥረት ተወጥሮ ያለው የህወሃት አገዛዝ ከትናንት በስቲያ ሃሙስ ብዛት ያላቸው ወታደሮችን ወደ ደቡብ የአገራችን ክፍል እንዳጓጓዘ ለማወቅ ተችሎአል።

ህወሃት ወደ ደቡብ የአገራችን ዳር ድንበር በአርባምንጭ እና በጎፋ በኩል  በኩል ያጓጓዛቸው እነዚህ  የመከላኪያ ሠራዊት አባላት ከባድ መሳሪያ ጭምር የታጠቁ እንደሆነ የአይን እማኞች ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል። በአርባምንጭ በኩል ያለፈው ሠራዊት በአሥር ትላልቅ ወታደራዊ መጓጓዣ እንደሆነ የገለጹት አይን እማኞች በጎፋ በኩል 6 የጭነት መኪና ሙሉ ወታደር ሲያልፍ መመልከታቸውን አረጋግጠዋል።

ይህን ያህል ብዛት ያላቸው ወታደሮች ለምን ወደ ክልሉ እንደተጓጓዙ በአገዛዙ በኩል የተሰጠ መግለጫ ስለሌለ የአካባቢው ህብረተሰብ በድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች ሳይኖሩ እንዳልቀረ ግምታቸውን መስጠት ጀመረዋል።

ይህ በዚህ እንዳለ በደቡብ ክልል የማንነት ጥያቄ በማንሳታቸው ብቻ በህወሃት ኮማንድ ፖስት በጅምላ ታስረው የተለቀዉ የቁጫ ወጣቶች ምንም አይነት ሥራ ሠርተው እንዳይኖሩ ተጸእኖ እየደረሰባቸው መሆኑን የበደሉ ሰለባ የሆኑ ዜጎች ለትንሳኤ ሬዲዮ ክፍል ገልጸዋል።

መንግሥትን ተቃውመዋል ተብለው ምንም አይነት ሥራ እንዳይሰሩ እየተደረጉ ካሉ በርካታ ወጣቶች መካከል ቀደም ሲል የመንግሥት ሥራ የነበራቸው እና በተቃውሞ በመሳተፋቸው ወደ ሥራቸው እንዳይመለሱ የተከለከሉ ከአንድ መቶ ሃያ በላይ የተለያየ ሙያ ያላቸው ሠራተኞች እንዳሉም ለማወቅ ተችሎአል።

የቁጫ ህዝብ ባነሳው የማንነት ጥያቄ ተሳትፈዋል የተባሉ በርካታ አርሶ አደሮችም የማዳበሪያ አገልግሎት እንዳያገኙ አለያም ወደድ ያለ ዕዳ እንዲከፍሉ እንደሚደረግ ይነገራል። ከዚህ በተጨማሪ የእራሻ መሬታቸውን የተቀሙና ለአመታት ከኖሩበት መሬት በግፍ እየተባረሩ ያሉም እንዳሉ ይነገራል።

የህወሃት አገዛዝ የተቃወሙትን ዜጎች ከማሠርና ከማሰቃየት አልፎ ከሥራ በማፈናቀል ለረሃብና ለችግር እንደሚዳርጋቸው ይታወቃል።

Share this post

Post Comment