የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን ማጠናከር እንደሚገባ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ

Source: https://fanabc.com/2019/04/%E1%8B%A8%E1%88%85%E1%8B%9D%E1%89%A5-%E1%88%88%E1%88%85%E1%8B%9D%E1%89%A5-%E1%8C%8D%E1%8A%95%E1%8A%99%E1%8A%90%E1%89%B6%E1%89%BD%E1%8A%95-%E1%88%9B%E1%8C%A0%E1%8A%93%E1%8A%A8%E1%88%AD-%E1%8A%A5/

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 16 ፣ 2011 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አስታወቀ።

የክልሉ መንግስት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጠው መግለጫ የአማራና ኦሮሞ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከሌሎች ህዝቦች ጋርም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብሏል።

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን በማጠናከርም የህዝቡን መሰረታዊ አጀንዳዎች ተግባራዊ ለማድረግ መረባረብ እንደሚገባም አንስቷል።

የአማራ ሕዝብን ትግል ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ ለመምራት በተደረገው እንቅስቃሴ የሕዝብ አጀንዳዎች መንግስታዊ ባለቤት አግኝተው ከህዝቡ ጋር የመቀራረብ ዕድል በመፍጠር ለጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሄ መስጠት የሚያስችል አጋጣሚ መፈጠሩንም መግለጫው አስታውሷል።

በሃገር ግንባታ ሂደቱም በሕዝቦች መካከል መከፋፈልና መጠራጠር እንዲሰፋ የተሰራውን ሴራ በማክሸፍ ሂደት፥ የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች ትስስር እና ግንኙነትን ማጠናከር የመፍትሄ ሃሳብ ተደርጎ ይወሰዳልም ነው ያለው መግለጫው።

በዚህ ሳምንት በአምቦ ከተማ በተካሄደው የሁለቱ ህዝቦች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መድረክ የታየው አዎንታዊ ምላሽም ትልቅ ፖለቲካዊና ሕዝባዊ ድል መሆኑንም ጠቅሷል።

በቀጣይም ይህን መሰሉ ግንኙነት ይበልጥ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር እየሰፋና እየተጠናከረ መሄድ ይኖርበታልም ነው ያለው።

 

 

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.