የህዝቦችን የጤና ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

Source: https://fanabc.com/2019/12/%E1%8B%A8%E1%88%85%E1%8B%9D%E1%89%A6%E1%89%BD%E1%8A%95-%E1%8B%A8%E1%8C%A4%E1%8A%93-%E1%89%B0%E1%8C%A0%E1%89%83%E1%88%9A%E1%8A%90%E1%89%B5-%E1%89%A0%E1%8B%98%E1%88%8B%E1%89%82%E1%8A%90%E1%89%B5/

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 4፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዝቦችን የጤና ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ።

በባህርዳር ለ ሁለት ቀናት የሚቆይ የወረዳ ትራንስፎርሜሽን እና የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የዕውቅና አሰጣጥ የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡

መድረኩ በአማራ ክልል ጤና ቢሮ አዘጋጅነት “በአመራር ቁርጠኝነት  ለህዝባችን ተጠቃሚነት” በሚል መሪ ቃል ነው  እየተካሄደ  የሚገኘው።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ላቀ አያሌው ÷የህዝባችንን የጤና ተጠቃሚነት በጥራት ፣በፍትኃዊነትና በዘላቂነት ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ባለፉት ጊዜያት በጤናው ዘርፍ በተሰሩ ስራዎች የዜጎችን ጤና በመጠበቅና ንቃተ ጤናውን በማሻሻል ወደ ልማቱ እንዲያተኩር ከማድረግ አኳያ መልካም ውጤቶች የተገኙ ቢሆንም የጤና አገልግሎት ጥራትና ሽፋን በማሳደግ ረገድ አሁንም ትኩረት ሰጥተን ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ  በበኩላቸው፥ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ከመከላከልና ከመቆጣጠር እንዲሁም የእናቶችንና የህጻናት ጤናን ከማሻሻል አንጻር ለውጦች መኖራቸውን  ገልጸዋል፡፡

በክልሉ በሚገኙ በርካታ ወረዳዎች ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተግባራዊ በመደረጉ የህብረተሰቡ  የጤና አገልግሎት ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያደገ  መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በመለየትና በመፍታት ህብረተሰባችን ጥራት ያለው ጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት  እንሰራለን  ሲሉ አክለዋል፡፡

በመድረኩ ላይ በ2011 ዓ.ም በወረዳ ትራንስፎርሜሽን እና በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ወረዳዎችና ዞኖች እውቅና  የሚሰጥ ሲሆን ለተሞክሮነትም የአፈጻጸም ልምዶችና የ2012 ዋና ዋና የዘርፉ የዕቅድ ተግባራት እንደሚቀርቡ ተገልጿል፡፡

መረጃው የጤና ሚኒስቴር ነው፤

 

 

 

 

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.