የለዉጥ ንቅናቄዎች በዛሬይቱ ኢትዮጵያ፦ ከየት፣ ወዴትና እንዴት?

Source: http://welkait.com/?p=11202
Print Friendly, PDF & Email

ሃሳብ ወለድ የኢትዮጵያዊያን ዉይይቶች

(ተስፋዬ ደምመላሽ)

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሕወሓት አገዛዝ ጋር ዛሬ የሚያኪያሂዳቸዉ አካባባዊና ታክቲካዊ ትግሎች በምን መንገድ ነዉ ወደ ዘላቂ አገር አቀፍ ስልታዊ ንቅናቄ የሚሸጋገሩት? ከጽንሱም መሠረቱም ብልሹ የሆነዉና ዛሬ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተቀባይነቱ ጨርሶ የተሟጠጠበት ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ራሱን መለወጥ ቀርቶ መጠገን የማይፈልግ ወይም የማይችል መሆኑን ግልጽ ካደረገ ዉሎ አድሯል። ሕወሓት ሰሞኑን በዉስጡ ባኪያሄደዉ የፓርቲ አመራር ብወዛ (ሹም ሽር) ይህንኑ ግትርነቱን አባብሶና ጠባብነቱን “በአድዋ” ቅኝት ይበልጥ አጣቦ እንዳረጋገጠም ተዘግቧል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ በበኩሉ የጭቆናዉ ሥርዓት በቃ፣ አገር ከፋፋዩና ማኅበረሰቦች አጋጪዉ ዘረኛ አገዛዝ ጨርሶ ከጫንቃዬ ይዉረድ፣ ከሥር መሠረቱ ይመንገል እያለ ነዉ። አስተዉሎ ላይ በተመሠረተ ተስፋ ሳይሆን በመኞታዊ እሳቤ ብቻ ተመርተዉ ወይም ምናልባት የሥልጣን ፍርፋሪ መለቃቀም ፈልገዉ ከአገዛዙ ጋር “እርቅ” መግባት ይቻላል ባዮችን ሳይከተል የአገዛዙንም የተቃዉሞ ጐራዉንም ጐሣ ተኮር ፖለቲካ ኪሳራ እያሳየ ነዉ። ታዲያ ለዘለቄታዉ በኢትዮጵያ ሥርዓታዊ ለዉጥ የሚመጣዉና አማራጩ የሚገነባዉ በምን አይነት የትግል አነሳስና አኪያሄድ ይሆን? ጥያቄዉ ይህ ይመስለኛል።

የሙሉጌታ ኃይሉ መታሰቢያ ሆኖ በተቋቋመዉ የዉይይት መድረክ ከሁሉት አመት ተኩል በፊት በዚህ ጽሑፍ ርዕስ ዙሪያ አንዳንድ ሃሳቦች አቅርቤ ነበር። ዛሬ አገራችን ያለችበት ወቅት እርግጥ ሕዝባዊ አመጾችና እንቅስቃሴዎች እየተፋፋሙ ያሉበትና ተደጋጋፊ መሆን በጀመሩ እንቅስቃሴዎቻቸዉ የወያኔን ዘረኛ ፖለቲካ ፉርሽነት ይበልጥ ተከሳች እያደረጉ ያሉበት ወቅት ነዉ። ሆኖም የለዉጥ ትግሉን በሚመለከት ባለፈዉ ጊዜ ያቀረብኳቸዉ ሃሳቦች አሁንም አገባብ አላቸዉ። በኔ አተያይ የትግሉ አገራዊም አካባባዊም አነሳስ (ከየት ?)፣ አቅጣጫዉና መዳረሻዉ (ወዴት ?)፣ እንዲሁም አኪያሄዱ (እንዴት ?) አሁንም ዋና ጉዳዮች ናቸዉ።

እንዲያዉም ዛሬ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎች እየተጧጧፉ ባሉበት ወቅት ጉዳዮቹ ከመቸዉም ጊዜ ይበልጥ ብርቱ ሆነዋል። የዜጐች፣ የማኅበረሰቦችና የአካባቢዎች እምቢተኛነት እያየለ ሲመጣ፣ ሕዝብ በቃ ብሎ እንቅስቃሴዉን ሲያፋፍም፣ የትግሉ ስልታዊ ቅንብርና አቅጣጫ ሰጪ አገራዊ ሃይሎችም ተሰባስበዉ፣ ከሕዝባዊ ትግሉ ጋር ተመዛዝነዉ፣ ይበልጥ ድርጁና ተንቀሳቃሽ መሆን ይኖርባቸዋል።

ይህን ማድረግ ግን ቀላል አይደለም። ላለፉት ሃያ ስድስት አመታት አገር ዉስጥና ዉጭ በኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ፣ የምሁራንና የመገናኛ ብዙሃን አካባቢዎች የተደረጉት ፀረ ወያኔ እንቅስቃሴዎች ግልጽ ያደረጉት ነገር ቢኖር በስልታዊ ራዕይ የተቀረጸ፣ የተደራጀና የተመራ አገር አቀፍ የተቃዉሞ ትግል መገንባት አስቸጋሪነትን ነዉ። የተቃዋሚ ወገኖች፣ ድርጅቶችና መገናኛ ብዙሃን እጥረት ኖሮን አያውቅም፤ በተለይ በዳያስፖራዉ የተቃዉሞ ጐራ የድርጅትና ሚዲያ አርብቶ አደሮች እጥረት የለም። በሃቀኝነት ለአገር የሚቆረቆሩ ዜጐችና ስብስቦች ቁጥር አላነሰም። በአገራዊነትም ሆነ በነገዳዊነት ደረጃ የበደል ተቀባይነት ስሜት ወይም የተጐጂነት ስነልቦና አልተጓደለም።ነገር ግን አንድ ጉልህና መሠረታዊ ጉድለት ነበረ፤ አሁንም አለ። ይኸዉም የሕወሓትን አገዛዝ ተቃዋሚ የሆኑ ነገደ ብዙ አገር ወዳድ ግለሰቦችና ስብስቦች በተለያዩ ምክንያቶች እንቅስቃሴዎቻቸዉን በጋራ ኢትዮጵያዊነት አገናኝተዉ፣ አዋህደዉና አማክለዉ መመሥረት፣ ማነፅና በሂደት ማዳበር አልቻሉም።

ይህ ያፈጠጠና ያገጠጠ ክፍተት ደግሞ የአገሪቱን የተለያዩ አካባባዊና ማኅበረሰባዊ ጉዳዮች፣ ብሶቶችና እንቅስቃሴዎች ለወያኔ ደባና አፈና ያጋለጠ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች የዉስጥም የዉጭም ሰርጐ ገብ ሃይሎች ጥምዘዛ ይበልጥ ያመቻቸ ነዉ። ስለዚህም ነዉ ሃቀኛ ወይም ሙሉ (integral) ብሔራዊ ቅርጽና ይዘት ሳይኖራቸዉ ኢትዮጵያን ከመፈረካከስ እናድናለን በሚሉ የዉስጥም የዉጭም ዘር ተኮር ሃይሎችና ወገኖች እንቅስቃሴዎች የትግሉ ምህዳር የተጣበበዉ። በሻቢያ ድጋፍና ዋና ነጂነት የግንቦት ሰባት ድርጅት ለአስርተ አመት ባለበት ሲሽከረከርበት የቆየዉ የፖለቲካ ጐዳና፣ ኢትዮጵያን በአንድነትና ሉአላዊነት የትም የማይወስድ “ሁለ ገብ” የትግል መንገድ፣ በዚህ አገባብ የሚታይ ነዉ። በተጨማሪ ድርጅቱ ዛሬ ጥቂት የጐሣ ቡድኖች አሰባስቦ የሚነዳዉ አገራዊ ህልዉናችንንና ንቃተ ህሊናችንን ፈጽሞ የማይመጥን “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ” እንዲሁ የምንገነዘበዉ ነዉ።

በኔ ግምት ይህ ኢትዮጵያ ዛሬ የምትገኝበት ዉስብስብ ዉጥረት ለነገደ ብዙ ለዉጥ ፈላጊ አገር ወዳድ ዜጐች፣ የጐበዝ አለቆች፣ አርበኖች፣ ምሁራንና የፖለቲካ ወገኖች የደቀነዉ ዋና ጉዳይ የትግሉ ሙሉ አገራዊ አነሳስና አቅጣጫ የሚረጋገጠዉ እንዴት ነዉ የሚል ነዉ። በሌላ አባባል፣ የኢትዮጵያ ሉአላዊ ብሔራዊነት የዛሬዉ የለዉጥ ትግል መነሻም መድረሻም የሚሆነዉ በምን መንገድ ነዉ? በቀጥታና ባንዳፍታ ከረቂቅ አለም አቀፍ የፖለቲካ ሃሳቦች (በተለይ “ዲሞክራሲ” ከምንለዉ) ብድግ ተብሎ ይሆን? ከግዛታዊ/አካባባዊ ምንነት (ከጐንደር፣ ጐጃም፣ ወሎ፣ ሽዋ) ተነስቶ ወይም የዘር መለዮን አስቀድሞ (በኦሮሞነት፣ በአማራነት፣ ወዘተ) ነዉ? ወይስ ደግሞ በዘመናዊ የስቪክ ብሔርተኝነት ጽንሰሃሳብ ብቻ ተንደርድሮ? ኢትዮጵያዊነት እንደ እሴት መሃል (value center) እነዚህን ግብአቶች አገናኝቶ፣ አሸጋሽጐና አዋህዶ የአንድ ሕዝብና የአንድ አገር ትግል አካላት ማድረግ አይችልም ወይ?

ኢነዚህን ጥያቄዎች አማክዬ ነዉ ይችን ጽሑፍ በሃሳብ ፈጠር ዉይይት መልክ ያቀረብኩት። አቀራረቡ በንጹሁ ፈጠራ ሳይሆን እውን አመለካከቶችና አቋሞች ላይ የተመሠረተ ነዉ። የሚከተሉት ገጾችና ተከታይ ጽሑፎች የያዙትን ሃሳብ ወለድ ዉይይቶች ያዘጋጀሁት ከተዉኔት ወይም ሥነ ጽሑፋዊ አላማ ተነስቼ ሳይሆን ወሰብሰብ ያሉ የአገር ጉዳዮችንና ከጉዳዮቹ የፖለቲካ ቀረጻ ጋር የተያያዘ ጽንሳዊ ሃሳብን (conceptual thought) ቀለል ላለ ግንዛቤ ለማመቻቸት ነዉ። ይህ አቀራረብ ብዙዉን ጊዜ በድፍኑ ወይም በድብስብሱ መነጋገሪያ የሆኑ ጉዳዮችን፣ እንዲሁም ሰፋና ጠለቅ ባለ (ምሁራዊ) የዕዉቂያ ጉጉት ሳይፈተሹ ያአነጋገር ዘይቤ ሆነው ብቻ የሚዘዋወሩ “ሃሳቦችን” በጥይይቅና ምልልስ ከፈትፈት በማድረግ የላቀ ትርጉማዊ ይዘት ሰጥቶና አጣርቶ መጨበጥ ያስችለናል የሚል ግምት አለኝ። ….. (Read more, pdf)

Share this post

Post Comment

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.