የሕንዱ ካራቱሪ ኩባንያ የሕወሃቱ አገዛዝ ካሳ እንዲከፍለው ጠየቀ

Source: http://amharic.ethsat.com/%E1%8B%A8%E1%88%95%E1%8A%95%E1%8B%B1-%E1%8A%AB%E1%88%AB%E1%89%B1%E1%88%AA-%E1%8A%A9%E1%89%A3%E1%8A%95%E1%8B%AB-%E1%8B%A8%E1%88%95%E1%8B%88%E1%88%83%E1%89%B1-%E1%8A%A0%E1%8C%88%E1%8B%9B/

(ኢሳት ዜና–መስከረም 12/2010)በኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት በጋምቤላ ክልል የወሰደውን ሰፊ መሬት የተነጠቀው የሕንዱ ካራቱሪ ኩባንያ የሕወሃቱ አገዛዝ ካሳ እንዲከፍለው ጠየቀ።

የኩባንያው ባለቤትና ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ሳይ ካራቱሪ ብሉምበርግ ለተባለው የዜና ወኪል በላኩት መግለጫ ኢትዮጵያ በነበረን ቆይታ ተሰላችተናል ደክሞናልም ብለዋል።

ሚስተር ካራቱሪ በኢትዮጵያ የነበራቸው የንግድ ፈቃድ መሰረዙንና ንብረታቸው ግን እንዳልተመለሰላቸው ገልጸዋል።

የህንዱ ኩባንያ ካራቱሪ ለኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ 3 መቶ ሺ ሔክታር መሬት በአነስተኛ የሊዝ ዋጋ በጋምቤላ ክልል ሲሰጠው የቦታው ስፋት እጅግ ከፍተኛ ስለነበር ብዙ ውዝግብ አስነስቶ ነበር።

የጋምቤላ መሬት በኢንቨስትመንት ስም ሲወረር ከፍተኛ ተቃውሞ ከሕዝቡ በኩል በመምጣቱም የኋላ ኋላም 3 መቶ ሺ ሔክታሩ ወደ አንድ መቶ ተቀንሶ ካራቱሪ በርካታ የእርሻ መሳሪያዎችን ለማስገባት ችሏል።

የሕንዱ ኩባንያ ካራቱሪ ከአገዛዙ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ባለው ቅርበት ብዙ ያላሟላቸው ነገሮች ቢኖሩም መሬቱን ተቆጣጥሮ በውጭ ሀገር የአክሲዮን ሽያጭ ሲያካሂድ እንደነበርም ሲገለጽ ቆይቷል።

ከፍተኛ የስኳር ልማትና የእርሻ ኢንቨስትመንት አካሂዳለሁ ያለው ካራቱሪ ቶሎ የሚደርሱ ሰብሎችን በመሬቱ ከፊል ቦታ ላይ ከመዝራት ያለፈ የሚጠበቅበትን ልማት እንዳላከናወነ ይነገራል።

የጋምቤላ ክልል ተወላጆች ተፈናቅለው ለካራቱሪ የተሰጠው ሰፊ መሬት በተባለው መሰረት ባለመልማቱና ከተለያዩ ወገኖች የመጣው ተቃውሞ በማየሉም በመጨረሻ የኢትዮጵያው አገዛዝ መሬቱን በመንጠቅ የንግድ ፈቃዱን ለመሰረዝ ችሏል።

ይህንኑ ተከትሎም በመሬቱ ላይ ከፍተኛ ሀብት አፍስሻለሁ የሚለው ካራቱሪ በሂደቱ ደክሜያለሁ አቅቶኛልም ሲል ኢትዮጵያን ለቆ መውጣቱን ይፋ አድርጓል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የካራቱሪ ኩባንያ ባለቤት ሚስተር ሳይ ካራቱሪ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደብዳቤ በመጻፍ ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል።

ይህ ብቻ አይደለም ለልማት ሲባል ወደ ጋምቤላ ያስገቧቸው ማሽነሪዎችና ንብረታቸው እንዲመለስላቸው በደብዳቤያቸው ጠይቀዋል።

የግብርና መሬት ልማት ኤጀንሲ ግን ካራቱሪ ከወሰደው 1 መቶ ሺ ሔክታር መሬት 1 ሺ 200 ሔክታሩን ብቻ አልምቷል በሚል አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ መወሰኑን ገልጿል።

ካራቱሪ ይህንኑ ተከትሎ ለጠየቀው ካሳና ንብርቴን መልሱልኝ ጥያቄ የአገዛዙ ባለስልጣናት መልስ አልሰጡም።

ብሉምበርግ የዜና ወኪል ያነጋገራቸው የኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚኒስትሩ አቶ ነገሬ ሌንጮ ጉዳዩ የሚመለከተው የኢንቨስትመንት ኮሚሽንን ነው በማለት ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን በበኩሉ አሁን ምላሽ አልሰጥም ማለቱን ብሉምበርግ ዘግቧል።

Share this post

Post Comment